በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡለን ከተማ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ 

በቤርሳቤህ ገብረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በመተከል ዞን፣ በቡለን ከተማ ዛሬ ንጋት ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ቢያንስ 10 ሰላማዊ ሰዎች እና የጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የመተከል ዞን እና የቡለን ወረዳ አስተዳደር በከተማይቱ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን፣ ባንክ ቤትን ጨምሮ በተቋማት ላይ ዝርፊያ እና ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል።

ጥቃቱ በቡለን ከተማ ላይ የተሰነዘረው፤ ዛሬ አርብ ግንቦት 29፤ 2017 ከንጋቱ 12 ሰዓት ገደማ ጀምሮ እንደነበር ነዋሪዎቹ እና የቡለን ወረዳ አስተዳደር ገልጸዋል። ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሶስት የቡለን ከተማ ነዋሪዎች ጥቃቱ እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት ገደማ ድረስ የቆየ እንደነበር አመልክተዋል።

ታጣቂዎቹ ዛሬ ንጋት ላይ ወደ ከተማ ሲገቡ መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የዓይን እማኝነታቸውን የሰጡ አንድ ነዋሪ፤ መቶ ገደማ የሚሆኑ ታጣቂዎች በአንድ መስመር ሲጓዙ ማየታቸውን ተናግረዋል። ከታጣቂዎቹ ውስጥ ገሚሶቹ ቡላ ቀለም ያለው የደንብ ልብስ እንደለበሱ እና የተቀሩት ግን የሲቪል ልብስ መልበሳቸውን መመልከታቸውን አክለዋል።

ነዋሪው “ክላሽ እና ብሬል የያዙ ነበሩ” ያሏቸው ታጣቂዎች ጥቃት መሰንዘር ሲጀምሩ በቤታቸው እንደነበሩ ገልጸዋል። በጥቃቱ አስር ሰዎች መገደላቸውን፣ የባንክ እና ፖሊስ ጣቢያ መዘረፉን መስማታቸውንም አስረድተዋል። “መከላከያ ካምፕ አለ። ልዩ ኃይል አለ። እዚያ ሰባት ነው የሚሉት የሞተው። ከተማ ውስጥ [የሞተው] ሶስት ነው” ሲሉ ነዋሪው በሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት አብራርተዋል። 

እኚሁ የከተማይቱ ነዋሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቃለመጠይቁን እየሰጡ ባለበት ወቅት፤ በጥቃቱ ህይወታቸው ያለፈ ሁለት ሰዎች ቀብር እየተፈጸመ ነበር። በዛሬው ጥቃት የቆሰሉ “ብዙ ሰዎች” መሆናቸውን የገለጹት ነዋሪው፤ ተጎጂዎቹ በጤና ተቋማት ህክምናቸውን እየተከታተሉ መሆኑን አስረድተዋል።

በዛሬው ጥቃት ከቆሰሉ ሰዎች ነዋሪዎች መካከል ወደ ፓዌ ሆስፒታል የተወሰዱ እንዳሉም ነዋሪው አክለዋል። “[ታጣቂዎቹ] ከዘረፉ፣ ሁሉንም ነገር ከያዙ በኋላ ለቅቀው ወጡ። ምንም የደረሰ ኃይል የለም። እዚህ የነበሩ ልዩ ኃይሎች ነበሩ። ብዙ ጥቃት አደረሱ። እነሱም ከአቅማቸው በላይ ሲሆን ሲሸሹ፣ ታጣቂዎቹ ከተማው ውስጥ ገቡ” ሲሉ ነዋሪው የዛሬውን ሁኔታ ገልጸዋል። 

“በአደባባይ ነው እየሄዱ የነበሩት። ተደብቀው አይደለም። ይተኩሱብናል ብለው እንኳን ስጋት የላቸውም። እስከንጋቱ ሶስት ሰአት ድረስ በግልጽ ነው [ጥቃቱን የፈጸሙት]። ምክንያቱም እኛም ሰግተን ስለነበር፤ ከቤት አልወጣንም። መስኮት ከፍተን፣ ድምጻችንን አጥፍተን እያየናቸው ነበር”

– የቡለን ከተማ ነዋሪ

የቡለን ከተማ ነዋሪ የሆኑ ሌላኛው የዓይን እማኝ ጥቃቱ በተባለው ሁኔታ መድረሱን፣ ዝርፊያ መካሄዱን እና ሰዎች መሞታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ታጣቂዎቹ በከተማው “በአደባባይ ነው እየሄዱ የነበሩት። ተደብቀው አይደለም። ይተኩሱብናል ብለው እንኳን ስጋት የላቸውም። እስከንጋቱ ሶስት ሰአት ድረስ በግልጽ ነው [ጥቃቱን የፈጸሙት]። ምክንያቱም እኛም ሰግተን ስለነበር፤ ከቤት አልወጣንም። መስኮት ከፍተን፣ ድምጻችንን አጥፍተን እያየናቸው ነበር” ሲሉ ነዋሪው ሁኔታውን አስረድተዋል። 

“አማራጭ አልነበረንም። በቦታው ምንም ኃይል የለም። መንግስት ባለበት ሀገር፤ እስከሚዘርፉ፣ እስከሚገድሉ ድረስ [ቆይተዋል]። ዛሬ በጣም ዘግናኝ ቀን ነው ያሳለፍነው። [ታጣቂዎቹ] ዓላማቸው ግልጽ አይደለም። ለዝርፊያ ይሁን ሰው ለመግደል የመጡት” ሲሉም ታጣቂዎቹ ወደ ከተማው የገቡበት ምክንያት ግልጽ እንዳልሆነላቸው እኚሁ ነዋሪ ተናግረዋል። ታጣቂዎቹ ረፋድ ላይ ከተማዋን ለቅቀው ሲወጡ፤ አምስት ሰዎች አግተው እንደወሰዱ መስማታቸውንም ነዋሪው አክለዋል።

የዛሬውን ሁኔታ “ከባድ ነገር ነው የደረሰብን” ሲሉ የገለጹት ሶስተኛ የከተማይቱ ነዋሪው፤ በከተማይቱ ላይ ጥቃቱ እየበረታ ሲመጣ የተወሰኑ ሰዎች “ወደ ዱር ወጥተዋል” ብለዋል። ሁለት “ኦራል” ተሽከርካሪዎች የተጫኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ዛሬ ከሰዓት ወደ ቡለን ከተማ መግባታቸውን ተከትሎ፤ በከተማይቱ የተወሰነ መረጋጋት መታየቱን ነዋሪው ተናግረዋል። 

በዛሬው ጥቃት የአድማ በታኝ ፖሊሶች እና የሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪው ገልጸዋል። እርሳቸውን ጨምሮ ሶስቱም የቡለን ከተማ ነዋሪዎች የዛሬውን ጥቃት የፈጸሙትን ታጣቂዎች “የሸኔ ታጣቂዎች ናቸው” ባይ ናቸው። 

የዛሬውን ጥቃት በተመለከተ ማምሻውን አጭር መረጃ ያወጣው የቡለን ወረዳ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት፤ በከተማይቱ በዛሬው ዕለት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰው “ጽንፈኛ ቡድን ነው” ብሏል። የቡለን ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ማሩ፤ ጽንፈኛው ቡድን ወደ ከተማይቱ በመግባት “የሰው ህይወት ማጥፋት ድርጊቶች መፈጸሙን” ለጽህፈት ቤቱ ገልጸዋል። 

አቶ ነመራ በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ባይገልጹም፤ ጥቃቱን የፈጸመው ቡድን በቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ በቡለን ከተማ በሚገኝ የንግድ ባንከ እና በመንግስት ተቋማት ላይ ጉዳት ማድረሱን እና ዝርፊያ መፈጸሙን አስታውቀዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሽቱ፤ ጥቃቱ መፈጸሙን አረጋግጠው የደረሰው ጉዳት ገና እየተጣራ መሆኑን አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ የመተከል ዞን ኮምዩኒኬሽን መምሪያ

“የጉዳት መጠኑ አይታወቅም። በርበር ቀበሌ እና ቡለን ከተማ ጥቃት አድርሰዋል። የጉዳት መጠኑን አላወቅንም። የጸጥታ ኃይል ወደ ቦታው ሄዷል” ሲሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ወደ ቦታው ያቀናው የጸጥታ ኃይል ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ እና ከክልሉ የአድማ ብተና ኃይል የተውጣጣ እንደሆነ አቶ አትንኩት አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)