በድሬዳዋ ከተማ አቅራቢያ በደረሰ የባቡር አደጋ ቢያንስ 15 ሰዎች ሞቱ  

በሶማሌ ክልል፣ ሽንሌ ከተማ ትላንት ሰኞ ጥቅምት 11፤ 2018 ለሊት በደረሰ የባቡር ግጭት እና የመገልበጥ አደጋ ቢያንስ 15 ሰዎች ሞተው፤ በ29 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የሽንሌ ወረዳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታወቀ። በተገለበጠው ባቡር ስር ያሉ ሰዎች ለማውጣት ጥረት እየተደረገ በመሆኑ፤ የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሏል። 

የትላንቱ የባቡር አደጋ የተከሰተው ከድሬዳዋ እስከ ደወሌ የባቡር አገልግሎት በሚሰጠው የህዝብ እና የጭነት ማጓጓዣ ላይ ነው። አደጋ የደረሰባቸው ባቡሮች እና ፉርጎዎች በድሬዳዋ ደወሌ የምድር ባቡር ድርጅት ስር የሚተዳደሩ ናቸው። 

የድሬድዋ ደወሌ የምድር ባቡር ድርጅት ለ25 ዓመታት ያቋረጠውን መንገደኞችን የማጓጓዝ ስራ እንደገና የጀመረው በ2014 ዓ.ም ነው። በድርጅቱ ስር ያሉ ባቡሮች በሳምንት ሁለት ጊዜ፤ ከድሬዳዋ ወደ ደወሌ እና ከደወሌ ወደ ድሬዳዋ ሰዎችን እና ሸቀጦችን ሲያጓጉዙ ቆይተዋል። 

ትላንት ከለሊቱ ስምንት ሰዓት ገደማ አደጋ የደረሰበት ባቡር፤ መነሻውን ከደወሌ አድርጎ ወደ ድሬዳዋ ይጓዝ የነበረ መሆኑን በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ዘይት፣ ስኳር እና ዱቄት የተጫነባቸው የባቡሩ ሁለት ፎርጎዎች ተንሸራትተው ከመስመር በመውጣት፤ ከድሬዳዋ አቅራቢያ በምትገኘው በሽንሌ ከተማ ለአስቸኳይ ስራ ከቆመ ባቡር ጋር በመጋጨታቸው መገልበጣቸውን የዓይን እማኞቹ አስረድተዋል። 

በግጭቱ እና ይህንን ተከትሎ በደረሰ የባቡር መገልበጥ በአስቸኳይ ስራ ላይ የነበሩ ሰራተኞች እና ከደወሌ ይመጣ በነበረው ባቡር ላይ የነበሩ መንገደኞች መሞታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል። በትላንቱ አደጋ 15 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን እና በ29 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል ጉዳት መድረሱን የሽንሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጀብሪል ኡመር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል።

በተገለበጡት የባቡር ፎርጎዎች ስር ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች እንዳሉ የገለጹት የዓይን እማኞች፤ ይህም የሟቾቹን ቁጥር ሊጨምረው እንደሚችል አብራርተዋል። ከፍተኛ ክሬኖችን በመጠቀም የተገለበጡ ባቡሮችን የማንሳት ስራ ዛሬ ረፋዱን ሲከናወን መቆየቱንም አክለዋል። 

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ድሬዳዋ ወደሚገኘው የኢትዮ ፈረንሳይ ድንገተኛ ህክምና መስጫ ማዕከል ተወስደው፤ በሆስፒታሉ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)