ከደብረ ሲና አቅራቢያ በሬክተር ስኬል 4.9 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

በአማራ ክልል ከሚገኘው ደብረ ሲና አቅራቢያ በሬክተር ስኬል 4.9 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ዛሬ እሁድ ጥቅምት 16፤ 2018 መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት ገለጸ። ንዝረቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የተሰማው ርዕደ መሬት የተከሰተው ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከ24 ደቂቃ ላይ ነው።

የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተበት ቦታ ከደብረ ሲና 30.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑን የአሜሪካው የአሜሪካው ተቋም አስታውቋል። ርዕደ መሬቱ የደረሰበት ስፍራ ከደብረ ብርሃን 38.8 ኪሎ ሜትር፣ ከአቦምሳ 44.5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑን የጠቆመው መረጃው፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲያስተናግድ ከቆየው አዋሽ 75.5 ኪሎ ሜትር እንደሚርቅ አመልክቷል።

የመሬት መንቀጥቀጡ በኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት የተመዘገበ ሁለተኛው ርዕደ መሬት ሆኗል። በትግራይ ክልል ከሚገኘው አዲግራት ከተማ 43 ኪሎ ሜትር በሚርቅ ቦታ ላይ፤ ባለፈው ሰኞ በሬክተር ስኬል 4.5 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ ነበር። 

በጥቅምት ወር መጀመሪያ በተከታታይ በተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች ሳቢያ በአፋር እና በትግራይ ክልል ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ ቤቶች እና አገልግሎት መስጪያ ተቋማት ፈራርሰዋል።  በአፋር ክልል፣ በኪልበርቲ ረሱ ዞን፣ በርሃሌ ወረዳ የነበረው ርዕደ መሬት ባደረሰው ጉዳት 43 ሺህ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት በወቅቱ አስታውቀው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]