የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከነገ በስቲያ ማክሰኞ ጥቅምት 18፤ 2018 በሚያካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ የፓርላማ አባላት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ምላሽ እና ማብራሪያ እንደሚሰጡ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የፓርላማ አባላቱ እስካለፈው ሰኞ ድረስ ጥያቄዎቻቸውን አስገብተው እንዲያጠናቅቁ የተነገራቸው ባለፈው ሳምንት እንደነበር ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመጪው ማክሰኞ የሚገኙበት መደበኛ ስብሰባ፤ በዓመት ውስጥ በፓርላማ በመገኘት ለጥያቄዎች ምላሽ ከሚሰጡባቸው ሶስት ሁነቶች የመጀመሪያው ነው። በ2008 ዓ.ም የወጣው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፤ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት የፌደራል መንግስትን ዕቅድ ካቀረቡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ በመገኘት ገለጻ ማድረግ እንዳለባቸው ይደነግጋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ የፌደራል መንግስትን የዘንድሮ ዓመት ዕቅድ ለተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች አባላት ያቀረቡት፤ የዛሬ ሶስት ሳምንት ገደማ መስከረም 26፤ 2018 ነበር። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዚህ ይፋዊ መክፈቻ በኋላ መደበኛ ስብሰባ ያካሄደው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው።

ምክር ቤቱ የአምስተኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ከነገ በስቲያ ማክሰኞ ጥቅምት 18 እንደሚያካሄድ ለፓርላማ አባላት መረጃዎችን በሚያሰራጭበት የቴሌግራም ቻናሉ በትላንትናው ዕለት ቢያስታውቅም፤ አጀንዳውን ከመግለጽ መቆጠቡን ምንጮች ገልጸዋል። ሆኖም ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አንድ የፓርላማ አባል፤ በዚሁ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡ ማረጋገጣቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ለዲፕሎማቶች እና ለተጋባዥ እንግዶች ጥሪ መዘጋጀቱን እንደተመለከቱም እኚሁ የፓርላማ አባል አክለዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሌላ የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል፤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ እንዲያቀርቡ መረጃ የተላከላቸው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ እንደነበር ገልጸዋል። ጥያቄ ለማስገባት የተሰጣቸው አምስት ቀናት ቢሆንም በእርሳቸው በኩል ጥያቄ አለማቅረባቸውን አስረድተዋል።
ለፓርላማው ጥያቄዎችን ማስገባታቸውን የገለጹ ሌላ የፓርላማ አባል በበኩላቸው፤ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያገኛል የሚል ተስፋ እንደሌላቸው ተናግረዋል። ለዚህም በማስረጃነት የሚጠቅሱት ባለፉት አራት ዓመታት ለፓርላማው ካስገቧቸው ጥያቄዎች ውስጥ ተቀባይነት ያገኙት ሁለት ጊዜ ብቻ መሆኑን ነው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ፤ መሰረት፤ “ማንኛውም የቃል መልስ የሚፈልግ ጥያቄ የሚያቀርብ አባል”፤ ጥያቄውን ለአፈ ጉባኤው በጽሁፍ ማሳወቅ ያለበት ስብሰባው ከመካሄዱ ቢያንስ አስር ቀናት በፊት ነው። ደንቡ ከፓርላማ አባላት የሚቀርቡ ጥያቄዎችን መርምረው የመቀበል ወይም ውድቅ የማድረግ ስልጣን የሰጠው ለአፈ ጉባኤው ነው።
አፈ ጉባኤው ጥያቄዎችን የመለየት ስራዎችን የሚያከናውኑት፤ በፓርላማው የመንግስት ዋና ተጠሪ ከሆኑት ግለሰብ ጋር እንደሆነ የውስጥ አሰራሩን የሚያውቁ ምንጮች ያስረዳሉ። ጥያቄዎች በዚህ መልኩ ከተለዩ በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚቀርቡም ምንጮች ይገልጻሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ለመጨረሻ ጊዜ ምላሽ የሰጡት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ማገባደጃ ላይ ነው። ሶስት ገደማ ከፈጀው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ፤ ቅድሚያውን እና ሰፊውን ጊዜ የወሰደው የኢኮኖሚ ጉዳይ ነበር። አንድ ሰዓት ያልሞላ ጊዜ በተሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ማብራሪያ፤ ትግራይ እና ኤርትራን የተመለከቱ ምላሾች መነሳታቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































