የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው

የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ላንዳው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአራት የአፍሪካ ሀገራት ከነገ ጀምሮ ጉብኝት ሊያደርጉ  ነው። ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር “በቀጠናዊ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳዮች” ላይ እንደሚወያዩ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።

ምክትል ሚኒስትሩ በዚሁ ጉብኝታቸው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ግብጽ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ ይጓዛሉ። የአሜሪካ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በመጋቢት 2017 ዓ.ም የተሾሙት ክሪስቶፈር ላንዳው፤ ወደ ካይሮ እና አዲስ አበባ የሚጓዙት የሀገራቸው ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ እና ግብጽ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት የገቡበትን ውዝግብ ለመፍታት እንደሚሹ ባስታወቁ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነው። 

የላንዳው የመጀመሪያ መዳረሻ በሆነችው ግብጽ፤ ላንዳው “በአካባቢያዊ ተግዳሮቶች” ላይ ስለሚደረግ ትብብር ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚወያዩ መስሪያ ቤታቸው ገልጿል። በእነዚህ ውይይቶች የአሜሪካ እና የግብጽ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን ማጠናከርን የተመለከቱ ጉዳዮች እንደሚነሱም መስሪያ ቤቱ አመልክቷል። 

የአሜሪካው ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከካይሮ ወደ አዲስ አበባ ሲያቀኑ፤ በዩናይትድ ስቴትስ ጦር የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን አብረዋቸው ይጓዛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ጄኔራል ዳግቪን አንደርሰን ባለፈው ህዳር በአዲስ አበባ ተገናኝተው ነበር። 

የአሜሪካው የጦር መኮንን ወደ አዲስ አበባ ብቅ ያሉት “በቀጠናዊ ጸጥታ እና ለተሻሻሉ የትብር ዕድሎች” ላይ ለመወያየት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ገልጸው ነበር። የሀገሪቱ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ባሻገር ለኢኮኖሚ ጉዳዮች ትኩረት እንደሚሰጡ ተገልጿል።    

ላንዳው ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት እና ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር በአዲስ አበባ በሚያደርጉት ውይይት፤ ለዩናይትድ ስቴትስ “የንግድ ተሳትፎ የሚሆኑ ዕድሎችን ያስታዋውቃሉ” ተብሏል። ላንዳው በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር የመገናኘት ዕቅድም ይዘዋል።

በዚህ ውይይት አሜሪካ እና የአፍሪካ ህብረት ቅድሚያ የሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚነሱ ተገልጿል። ሁለቱ ወገኖች ከሚወያዩባቸው አጀንዳዎች መካከል “ሰላምን ማስፈን፣ የንግድ ትብብርን ማስፋት እና ሰብአዊ ቀውሶችን መፍታት” የሚሉት እንደሚገኙበት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)