የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በግማሽ ዓመት ብቻ 104 የፖሊስ አባላትን በከባድ የዲሲፕሊን ጥፋት ማሰናበቱን ገለጸ

“ከስነ ምግባር ብልሽት” እና “ከሰብዓዊ መብት ጥሰት” ጋር በተያያዘ 104 የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት፤ “በከባድ የዲሲፕሊን” ጥፋት መሰናበታቸውን የከተማይቱ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጌቱ አርጋው አስታወቁ። “ብዙ እድል እና ተደጋጋሚ ትምህርት ተሰጥቷቸው” ባልታረሙ የፖሊስ አባላት ላይም “ከባድ የዲሲፒሊን እርምጃ” እንደሚወሰድ ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ ይህንን የገለጹት፤ ዛሬ አርብ ጥር 29፤ 2018 በተካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ለተነሳ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው። ዶ/ር ኢቲሳ ደሜ የተባሉ የከተማይቱ የምክር ቤት አባል፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚነሳባቸው መስማታቸውን ገልጸዋል። 

“ታች ያሉ የፖሊስ ኦፊሰሮች አካባቢ ላይ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች አሉ” ያሉት ዶ/ር ኢቲሳ፤ “አንድ ሁለት ቦታ ላይ በሚፈጠረው ችግር” የፖሊስ “አጠቃላይ ስም” እንደሚጎድፍ ተናግረዋል። በህብረተሰቡ መካከል “ፖሊስ እንዲህ እየሆነ ነው። ፖሊስ እንዲህ እያደረገ ነው” የሚሉ ሰዎች መኖራቸውን የጠቀሱት የምክር ቤት አባሉ፤ ይህ አይነቱ አስተያየት የሚሰጠው “ከግንዛቤ ችግር ሊሆን እንደሚችል” ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

“መንደር ውስጥ ገብተው የሚሰሩ የሚመሰገኑ ፖሊስ ኦፊሰሮች እንዳሉ ሁሉ፤ ቅሬታ የሚነሳባቸው መኖራቸውንም ግን በተደጋጋሚ ሰምቻለሁ” ሲሉም ዶ/ር ኢቲሳ በጸጥታ አስከባሪዎች ላይ ህብረተሰቡ የሚሰጠውን አስተያየት አጋርተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባሉ በፖሊሶች ላይ “በተለይ ከስነ ምግባር አንጻር እንዴት ነው ክትትል የሚደረገው?”፣ “ታች ድረስ ቁጥጥሩ እና ክትትሉ እስከ ምን ድረስ ነው?” ሲሉም ጠይቀዋል።  

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የከተማይቱ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ፖሊስ ከሚሰጠው አገልግሎት “ተቃራኒ በሆነ” ሁኔታ “የስነምግባር ብልሽት ያሳዩ” እንደዚሁም “ከሰብዓዊ መብት ጥሰት” ጋር የተያያዙ 104 ፖሊሶች እንዲሰናበቱ መደረጉን ገልጸዋል። ሆኖም ከስራቸው የተሰናበቱት ፖሊሶች የትኞቹን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደፈጸሙ ኮሚሽነሩ አላብራሩም።  

ኮሚሽነር ጌቱ ህዝብን “ፍጹም ስነ ምግባር በተሞላው መንገድ እንዲያገለግሉ” “ብዙ እድል እና ተደጋጋሚ ትምህርት” ተሰጥቷቸው ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት “ያልታረሙ” የፖሊስ አባላት እንዳሉ በዛሬው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። በእነዚህ የፖሊስ አባላት ላይ የከተማይቱ ፖሊስ ኮሚሽን “ከባድ የዲሲፒሊን እርምጃ” እንደሚወሰድም አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ዋና ቅድሚያ የሚሰጠው “ለህዝብ” እንደሆነ የገለጹት ኮሚሽነር ጌቱ፤ ለፖሊስ አባላቱ ስልጠና ሲሰጣቸውም ሆነ “ለህገ መንግስቱ ታማኝ ሆነው” ቃለ መሃላ ፈጽመው ተቋሙን ሲቀላቀሉ “ህዝብን እንዲያገለግሉ” እንደሆነ አስገንዝበዋል። 

“በየአካባቢው የሚገኙ እንደዚህ አይነት በጥፋት ውስጥ የሚሳተፉ አባላት ሲኖሩ፤ በአመት የምንሰራው የማጥራት ስራ እንዳለ ሆኖ ተከታታይ በሆነ መንገድ ጠንካራ የሆነ አስተዳደራዊ እርምጃ እና ህጋዊ እርምጃ የምንወስድበት ስርዓት አለን” ሲሉም ኮሚሽኑ እንዲህ አይነት ችግሮችን የሚከታተልበትን አሰራር አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)