በትላንትናው ዕለት የምዝገባ ምስክር ወረቀቱ የተሰረዘው “አዲስ ስታንዳርድ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን፤ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን “ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ተሰጥቶታል” የሚለው ክስ “ከእውነት የራቀ ነው” ሲል አስተባበለ። የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ)፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የ“አዲስ ስታንዳርድ”ን ምዝገባ “በአፋጣኝ ወደነበረበት እንዲመልስ” እና በፕሬስ ላይ እያበረታ የመጣውን ጥቃት “እንዲያቆም” ጠይቋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን የ“አዲስ ስታንዳርድ”ን የምዝገባ ምስክር ወረቀት መሰረዙን የገለጸው ትላንት ማክሰኞ የካቲት 17፤ 2018 አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ ነው። ባለስልጣኑ መገናኛ ብዙሃን ተግባራቶቻቸውን በሕግ መሰረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ “ክትትል እና ቁጥጥር” የማድረግ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው ተቋም ነው።
ተቋሙ በትላንቱ መግለጫው፤ አዲስ ስታንዳርድ “የሚዲያ ስነ-ምግባርን፣ የኢትዮጵያን ህጎች እና የሀገርንና የህዝብን ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ዘገባዎችን በተደጋጋሚ በማሰራጨት ላይ ይገኛል” ሲል ከስሷል። የአዲስ ስታንዳርድን “ተግባር” “አደገኛ ” ያለው ባለስልጣኑ፤ ይህንንም በቁጥጥር (ሬጉላቶሪ) ስራዎቹ “ማረጋገጡን” አመልክቷል።

የመገናኛ ብዙሃኑ ዘገባዎች በዜጎች “በርካታ” ጥቆማ እና ቅሬታ ሲቀርብባቸው እንደነበረም ባለስልጣኑ ገልጿል። የመገናኛ ብዙሃኑን ድርጊት “መርምሬያለሁ” ያለው መስሪያ ቤቱ፤ አዲስ ስታንዳርድ “እንዲታረም እና ከአጥፊ አካሄዱ እንዲቆጠብ” በተደጋጋሚ “ምክር” መስጠቱን በመግለጫው አስፍሯል።
“[አዲስ ስታንዳርድ] በሚዲያ ዘርፉ ላይ የሙያ ስነምግባር እና የሀገርና የህዝብ ብሔራዊ ጥቅም አክብሮ እንዲሰራ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ እና ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ለመታረም ፈቃደኛ አልሆነም” ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ወንጅሏል።
የአዲስ ስታንዳርድ ዋና አዘጋጅ አቶ ዮናስ ከድር፤ የተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱን ውንጀላ “ውድቅ ማድረጉን” መገናኛ ብዙሃኑ ዘግቧል። “አዲስ ስታንዳርድ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ደርሰውታል የሚለው ክስ ከእውነት የራቀ ነው። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙህን ባለስልጣን ቀደም ሲል ስለነበሩ የሕግ ጥሰቶችም ሆነ ስለተወሰዱ እርምጃዎች ለአዲስ ስታንዳርድ የዜና ክፍል በይፋ ያሳወቀው ነገር የለም” ሲል ዋና አዘጋጁ መናገሩን ዘገባው ጠቅሷል።

መገናኛ ብዙሃኑ የተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱን ውንጀላ ቢያስተባብልም፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በበኩሉ የአዲስ ስታንዳርድ ምዝገባ በመሰረዙ ተቋሙ “ምንም አይነት የሚዲያ ፈቃድ እና እውቅና እንደሌለው” የሚመለከታቸው አካላት “እወቁልኝ” ብሏል። ባለስልጣኑ በበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ሲወሰድ በአንድ ወር ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
መስሪያ ቤቱ ባለፈው ጥር ወር አጋማሽ፤ “ዋዜማ” የተሰኘው የበይነ መገናኛ ብዙሃን “የስራ ፈቃድ እውቅናውን” እንዲመልስ አድርጎ ነበር። ባለስልጣኑ ለእርምጃው የጠቀሰው ምክንያት “ዋዜማ”፤ የኢትዮጵያን ህገ-መንግስት፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅን፣ መመሪያዎችን እና የሙያ ስነምግባርን “አክብሮ ለመስራት” “ፈቃደኛ አልሆነም” የሚል ነበር።
የዋዜማ ዘገባዎች፤ የኢትዮጵያን “ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረሩ”፣ “ሚዛናዊነት የሚጎድላቸው” እና “የሙያ ስነምግባርን የጣሱ” “የአንድ ወገን ዘገባ ብቻ” የተንጸባረቁባቸው ሆነው መገኘታቸውን ባለስልጣኑ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ላይ ጠቅሶ ነበር።
መስሪያ ቤቱ ከአንድ ሳምንት በፊት መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የሮይተርስ ጋዜጠኞችን የዘገባ ፍቃድ እንደማያድስ ማስታወቁን ዋና መስሪያ ቤቱን በለንደን ያደረገው ዓለም አቀፍ የዜና ወኪል ማስታወቁም ይታወሳል። ጋዜጠኞቹ ፈቃዳቸው እንደማይታደስ በተቆጣጣሪው ባለስልጣን እንደተገለጸላቸው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከራሳቸው ከሮይተርስ ባልደረቦች አረጋግጣለች።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ)፤ በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የተወሰደው እርምጃ በገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን ላይ “እየበረታ በመጣው” “አፈና” አውድ ውስጥ ሊታይ እንደሚገባ ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ላይ አስፍሯል። የሲፒጄ የአፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት አንጄላ ኩዊንታል፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን “ብሔራዊ ጥቅም” እና “የሚዲያ ስነ ምግባር”ን የሚመለከቱ “ግልጽነት የሚጎድላቸው” አንቀጾችን በመሳሪያነት በመጠቀም፤ ገለልተኛ ጋዜጠኝነትን “እያፈነ” መሆኑን ተናግረዋል። “ቁጥጥር ሳይሆን በቀል ነው” ሲሉም ተችተዋል።
“የአዲስ ስታንዳርድ ፈቃድ መሰረዝ በኢትዮጵያ ያለውን ተቺ ዘገባዎችን (critical reporting) ለማጥፋት ሆን ተብሎ እየተደረገ ያለ ዘመቻ አካል ነው። ባለስልጣናቱ የመገናኛ ብዙሃኑን ምዝገባ በአፋጣኝ ወደነበረበት መመለስ እና በፕሬስ ላይ እያበረታ የመጣውን ጥቃት ማቆም አለባቸው” ሲሉ የሲፒጄ የአፍሪካ ዳይሬክተር አሳስበዋል።

ሲፒጄ አዲስ ስታንዳርድን ጨምሮ በሌሎች ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን ላይ ከዚህ ቀደም ጫናዎች እና በጋዜጠኞቻቸው ላይ የደረሱ እስሮችን በተመለከተ ተመሳሳይ አቋሙን በተደጋጋሚ ሲያንጸባርቅ ቆይቷል። ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር አጋማሽ ሶስት ጋዜጠኞቹ ታስረውበት የነበረው አዲስ ስታንዳርድ፤ ሰራተኞቹ “ከፍተኛ መንገላታት” እንደደረሰባቸው በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
ፖሊስ በዚያን ወቅት በመገናኛ ብዙሃን ድርጅቱ ቢሮ ባደረገው ብርበራ፤ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች እንደተወሰዱበትም ገልጾ ነበር። አዲስ ስታንዳርድ በፖሊስ የተወሰዱት ላፕቶፖች፣ ዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮች፣ የሞባይል ስልኮች፣ ፍላሽ ዲስኮች እና ሲፒዩዎች ከቀናት በኋላ እንደተመለሱለት ቢገልጽም፤ የድርጅቱ የአይቲ ባለሙያዎች በንብረቶቹ ላይ ባደረጉት “ሙያዊ ፍተሻ” “የተራቀቀ የስለላ ሶፍትዌሮች (malware) መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ” ማግኘታቸውን በወቅቱ ይፋ አድርጓል።
አዲስ ስታንዳርድ በሰኔ 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን እገዳ ተጥሎበት እንደነበርም ይታወሳል። ባለስልጣኑ አዲስ ስታንዳድርን አግዶት የነበረው፤ በትግራይ ክልል ጦርነት ወቅት “የሽብርተኛ ቡድን አጀንዳዎችን ያራምዳል” የሚል ውንጀላ በማቅረብ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
































