በኢትዮጵያ ከመጋቢት ወር አጋማሽ እስከ ሚያዝያ ወር አጋማሽ ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብቻ 14 ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሰራተኞች ለእስር ተዳርገው እንደነበር ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) አስታወቀ። ከታሰሩት ጋዜጠኞች እና ሰራተኞች ውስጥ ሁለቱ አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኙ ሲፒጄ ገልጿል።
ሲፔጄ ይህን የገለጸው፤ በየሀገራቱ ያሉ ጋዜጠኞችን የተመለከቱ ሰሞነኛ ጉዳዮችን አጠናቅሮ ይፋ በሚያደርግበት ዘገባ ላይ ነው። ድርጅቱ ትላንት አርብ ግንቦት 8፤ 2017 ባወጣው ዘገባ፤ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠች አስታውሷል።
በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞችን በተመለከተ ድርጅቱ በየዓመቱ በሚያወጣው ዓመታዊ ሪፖርት፤ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ከኢትዮጵያ በላቀ ጋዜጠኞች የታሰሩባት ሀገር ኤርትራ መሆኗ ተመልክቷል። ዓመታዊ ሪፖርቱ እስከተጠናቀረበት እስካለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ በኢትዮጵያ የታሰሩ ጋዜጠኞች ስድስት እንደነበሩ ሲፒጄ በትላንቱ ሪፖርቱ ጠቅሷል።

ይህ ቁጥር ባለፈው መጋቢት እና ሚያዝያ ወር በተፈጸሙ እስራቶች በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቦ ነበር። በመጋቢት ወር ከተፈጸሙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እስሮች ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሰራተኞች ላይ ነው። “አዲስ ምዕራፍ” በተሰኘ የጣቢያው ፕሮግራም የሀሰት ታሪኳ ተላልፏል በተባለችው ብርቱካን ተመስገን ጉዳይ ምክንያት ሰባት የኢቢኤስ ሰራተኞች በወቅቱ ለእስር ተዳርገዋል።
በቴሌቪዥን ጣቢያው ሰራተኞች ላይ የተፈጸመውን እስር በትላንቱ ዘገባው ላይ ያካተተው ሲፒጄ፤ በአሁኑ ወቅት ሁሉም መለቀቃቸውን ገልጿል። ከታሰሩት የኢቢኤስ ሰራተኞች መካከል አራቱ ክስ ሳይቀርብባቸው ዋስትና በማቅረብ በነጻ መለቀቃቸው የሚታወስ ነው። ከጣቢያው ሰራተኞች መካከል ሶስቱ በጥላቻ ንግግር እና ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።፡
ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል ሁለቱ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው፣ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ በፍርድ ቤት ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ በዚህ ሳምንት ከእስር ተለቅቀዋል። በሲፒጄ ዘገባ ከተጠቀሱ እስሮች ሁለተኛውን ከፍተኛ ቁጥር የያዘው “አዲስ ስታንዳርድ” የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን ነው።


ሶስት ጋዜጠኞቹ እና ባለሙያዎቹ ሐሙስ ሚያዝያ 9፤ 2017 በፖሊስ የታሰሩበት “አዲስ ስታንዳርድ፤ ሰራተኞቹ የዚያኑ ዕለት ቢለቀቁም “ከፍተኛ መንገላታት” እንደደረሳባቸው በወቅቱ አስታውቆ ነበር። የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቱ በዕለቱ ፖሊስ በቢሮው ባደረገው ብርበራ፤ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች እንደተወሰዱበትም ገልጿል።
በፖሊስ የተወሰዱት ላፕቶፖች፣ ዴስክቶፕ ኮምፒዩተሮች፣ የሞባይል ስልኮች፣ ፍላሽ ዲስኮች እና ሲፒዩዎች ከቀናት በኋላ እንደተመለሱለት “አዲስ ስታንዳርድ” ከሁለት ሳምንት በፊት ለንባብ ባበቃው ርዕሰ አንቀጽ ላይ አመልክቷል። ሆኖም የድርጅቱ የአይቲ ባለሙያዎች ባደረጉት “ሙያዊ ፍተሻ”፤ በንብረቶቹ ላይ “የተራቀቀ የስለላ ሶፍትዌሮች (malware) መኖሩን የሚያሳይ ማስረጃ” ማግኘታቸውን መገናኛ ብዙሃኑ በዚሁ ርዕሰ አንቀጹ ላይ አስታውቆ ነበር።
“በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የደረሰው ጥቃት እንደ አንድ ነጠላ ክስተት ሊታለፍ አይገባም። ጥቃቱ ቀድሞውንም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚገኘው የፕሬስ ነጻነት ላይም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ የዲጂታል መብቶችና የግላዊ መረጃዎች ደህንነት የወደፊት ሰፊ ዕጣ ፈንታ ላይ የተቃጣ የጥቃት ሙከራ ነው” ሲልም መገናኛ ብዙሃኑ ድርጊቱን ኮንኗል። ፖሊስ በመገናኛ ብዙሃኑ ቢሮ ላይ ያደረገው ብርበራ “የኢትዮጵያ መንግስት ነጻ ሚዲያዎችን ዝም ለማሰኘት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያካሄደው ያለው ዘመቻ አካል ነው” ሲል ሲፒጄም በወቅቱ ተመሳሳይ አቋሙን አንጻባርቆ ነበር።
“በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የደረሰው ጥቃት እንደ አንድ ነጠላ ክስተት ሊታለፍ አይገባም። ጥቃቱ ቀድሞውንም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በሚገኘው የፕሬስ ነጻነት ላይም ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ውስጥ የዲጂታል መብቶችና የግላዊ መረጃዎች ደህንነት የወደፊት ሰፊ ዕጣ ፈንታ ላይ የተቃጣ የጥቃት ሙከራ ነው”
– የአዲስ ስታንዳርድ ርዕሰ አንቀጽ (ሚያዝያ 22፤ 2017)
ሲፒጄ በትላንቱ መግለጫው የጠቀሳቸው ሌሎች እስራቶች በሶማሌ እና በሀረሪ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ የተፈጸሙ ናቸው። ፖሊስ በመጋቢት ወር መጨረሻ በሀረሪ ክልል ያሰረው ሙሂዲን አብዱላሂ የተባለው ጋዜጠኛ፤ በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ሲሰራ የቆየ ነው። ከሁለት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ “የግዳጅ እረፍት” ከኤጀንሲው በአስተዳደር እንዲገለል መደረጉ የተነገረለት ሙሂዲን “ቢዮ ፕሮዳክሽን” የተሰኘ የራሱን ዩቲዩብ ቻናል ከፍቶ ሲሰራ መቆየቱም ተጠቅሷል።
ጋዜጠኛው በፌስቡክ ገጽ ላይ በወጡ ሁለት ጹሁፎች ሳቢያ፤ በስም በማጥፋት እና ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ወንጀሎች ክስ እንደቀረበበት ሲፒጄ በዘገባው ላይ አስፍሯል። የክስ ሰነዱን የተመለከተው ሲፒጄ፤ ጋዜጠኛው ጥፋተኛ ከሆነ በድምሩ በስድስት ዓመት እስራት ሊቀጣ እንደሚችል ጠቁሟል። ሙሂዲን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውል ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ የገለጸው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ፤ ከአሁኑ እስሩ በኋላ ከሀረሪ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ይከፈለው የነበረው ደመወዝ መቋረጡን አክሏል።
ሲፔጂ በዚሁ ዘገባው፤ ከሀረሪ ክልል አቅራቢያ በሚገኘው ሶማሌ ክልል በእስር ላይ የሚገኘውን የጋዜጠኛ አህመድ አግዋን ጉዳይም አካትቷል። “ጅግጅጋ ቴሌቪዥን ኔትወርክ” የተሰኘው መገናኛ ብዙሃን መስራች የሆነው አህመድ፤ ህዝብን በማነሳሳት ወንጀል ተጠርጥሮ በሚያዝያ ወር አጋማሽ ፍርድ ቤት እንደቀረበ ሲፒጄ በዘገባው አመልክቷል። ጋዜጠኛው የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆበት በምርመራ ላይ እንደሚገኝም ድርጅቱ ገልጿል።

አህመድ በታሰረበት ዕለት፤ በአዲስ አበባ ከተማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የጋዜጠኛ አበበ ፍቅር ጉዳይም በሲፒጄ ዘገባ ተዳስሷል። የሪፖርተር ጋዜጣ ዘጋቢ የሆነው አበበ የታሰረው፤ መረጃ ለማሰባሰብ በልደታ ክፍለ ከተማ በተገኘበት ወቅት እንደነበር ጋዜጣው በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ጋዜጠኛው ከሁለት ቀናት በኋላ ክስ ሳይቀርብበት በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተለቅቋል።
“ፈንታሌ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ፋኑኤል ክንፉም፤ ለሶስት ቀናት ከታሰረ በኋላ በተመሳሳይ መልኩ ክስ ሳይቀርብበት በ15 ሺህ ብር ዋስትና መለቀቁን ሲፒጄ በዘገባው ላይ አስፍሯል። ፋኑኤል ከመኖሪያ ቤቱ ተወስዶ የታሰረው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር እና በሚያዝያ 2015 ዓ.ም በተላለፉ ሁለት አስተያየት አዘል ቪዲዮዎቹ “ስም የማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል” በሚል ነበር።
በኢትዮጵያ በተቺ ጋዜጠኞች ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው ተደጋጋሚ እስር የሚሳየው፤ የሀገሪቱ መንግስት “ለፕሬስ ያለውን ጠበኛነት ነው” ሲሉ የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ ሙቶኪ ሙሞ መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። አስተባባሪዋ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በስራቸው ምክንያት የታሰሩ ጋዜጠኞችን እንዲለቅቁ እንዲሁም የፕሬስ ነጻነትን የሚሸረሽሩ ህጎችን እንዲያሻሽሉ አሊያም እንዲሰርዙ ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)