በኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ያለው “የግጭት አውድ”፤ የሰብአዊ መብት ጥበቃ ስራዎችን “ፈታኝ ማድረጉን” የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። ይሁንና ሰዎች አግቶ ከመሰወር ጋር በተገናኘ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ “እየቀነሰ” መሄዱን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ገልጸዋል።
አቶ ብርሃኑ ይህን ያሉት፤ ኢትዮጵያ የምታስተናግደው 16ኛውን የአፍሪካ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ትስስር ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክቶ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 17፤ 2018 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ዋና ኮሚሽነሩ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ ሰዎችን አስገድዶ መሰወር እና ገንዘብ መጠይቅ “የተለመደ” መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን “ሰውን የሆነ ቦታ [አግቶ] አስቀምጦ ይሄን ያህል ብር አምጣ” ማለት መቀነሱን ገልጸዋል። ይህ ተግባር የቀነሰው፤ ኢሰመኮ “በግጭት ዐውድ ውስጥ እና ከግጭት ዐውድ ውጪ” ባሉ አካባቢዎች ያደረገውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ግኝቱን ይፋ ካደረገ ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ እንደሆነ አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል።
ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ከአራት ወራት በፊት ጥቅምት ይፋ ባደረገው በዚሁ ግኝት፤ በአራት ክልሎች ባሉ መንገዶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እገታዎች፣ የንብረት ዘረፋዎች እና ውድመቶች ምክንያት “የሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት መብት አደጋ ላይ መውደቁን” ገልጾ ነበር። በዚህ የኢሰመኮ ሪፖርት የተጠቀሱት ክልሎች አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ናቸው።
እነዚህ እርምጃዎች ከመዘዋወር ነጻነት መብት ባሻገር፤ በህይወት የመኖር፣ የአካል እና የንብረት ደህንነት መብቶች ላይ “ጥሰቶችን ማስከተላቸውን” ማረጋገጡን ኮሚሽኑ በወቅቱ ባወጣው ሪፖርት አመልክቶ ነበር። ኢሰመኮ መግለጫውን ካወጣ በኋላ የእገታ ዜናዎች እንደከዚህ ቀደሙ በብዛት ባይሰሙም፤ በመንገድ ላይ የሚፈጸሙ የጥቃት እና እገታ ተግባራት መቀጠላቸውን የሚገልጹ መረጃዎች በመገናኛ ብዙሃን ጭምር ተሰራጭተዋል።
ከእነዚህም መካከል ባለፈው ታህሳስ ወር 51 ሰዎችን አሳፍሮ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ደብረ ማርቆስ በሚጓዝ አውቶቡስ ላይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በታጣቂዎች የተፈጸመው እገታ ይጠቀሳል። “አሊዶሮ” በተባለው እና ተደጋጋሚ መሰል ክስተቶችን ባስተናገደው ስፍራ ላይ በተፈጸመው በዚህ የታጣቂዎች ጥቃት፤ አራት ሰዎች መታገታቸው በወቅቱ ተዘግቦ ነበር።

ከእገታ በተጨማሪ ያሉበት ሳይታወቅ የሚሰወሩ ግለሰቦችን የተመለከቱ መረጃዎችም ባለፉት ወራት ተመሳሳይ ሽፋን አግኝተዋል። ከሰሞኑ በማህበራዊ የትስስር ገጾች እና በመገናኛ ብዙሃን የተሰራጩ መረጃዎች፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ተይዘው ከተወሰዱ በኋላ ከአንድ አመት በላይ “ያሉበት ሳይታወቅ” “የተሰወሩ” ወጣቶች እንዳሉ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫም፤ ከአንድ አመት በፊት በመንግስት የጸጥታ አካላት ከአዲስ አበባ ከተማ ተይዘው የተወሰዱ “በርካታ” ወጣቶች እስካሁን ድረስ ያሉበት አድራሻና የደህንነት ሁኔታ “አለመታወቁ” እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር። የግለሰቦች እገታ እና መሰወርን በተመለከተ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው የኢሰመኮው ዋና ኮሚሽነር፤ ለጥያቄው ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጡም።
ሆኖም አቶ ብርሃኑ ጠቅለል አድርገው በሰጡት ምላሽ፤ አስገድዶ መሰወርን በተመለከተ የሚመጡ ጉዳዮችን እርሳቸው የሚመሩት ኮሚሽንም እንደሚመረምር አረጋግጠዋል። ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ ”ከተሰወሩ ሰዎች ቤተሰቦች ጋር ጭምር በመሆን” ምርመራ በሚደረግበት ወቅት ግን ኮሚሽኑ ፈተናዎች እንደሚገጥሙት አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።

ግለሰቦች በተለያዩ መንገዶች ጥቆማዎችን ካመጡ በኋላ የምርመራ ሂደቱ ሳይጠናቀቅ አመልካቾቹ እንደሚጠፉ እና “ባለቤት ነኝ የሚል ሰው እንደማያገኙ” ኮሚሽነሩ ተናግረዋል። በሚደርሳቸው ጥቆማ መሠረት ብዙ ጊዜ ስወራውን ፈጽመውታል የሚባሉት “ቀይ ቦኔት የለበሱ ናቸው” ቢባልም፤ እነዚህ አካላት “የመንግሥት አካል ይሁኑ ሌላ አካል” እንደማይታወቅም አቶ ብርሃኑ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ በዛሬው መግለጫቸው፤ ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እና የዘፈቀደ እስር ጉዳዮችንም አንስተዋል። እነዚህ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች “አሁንም” በኢትዮጵያ አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች መሆናቸውንም ገልጸዋል።
“እንደ ችግር የምናየው በግጭት አውድ ውስጥ መኖራችንን ነው” ያሉት ኮሚሽነሩ፣ በተለይም በኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች ያለው “የግጭት አውድ” የሰብአዊ መብት ጥበቃ ሥራዎችን ለማካሄድ “ፈታኝ” መሆኑን ጠቅሰዋል። እነዚህንም “እንደ ሀገር ያልተሻገርናቸው ችግሮች ሆነዋል” ሲሉ አክለዋል።

የማዕድን ማውጣት ሥራዎች ባሉባቸው በተለይም በጋምቤላ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚከሰቱ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም “አሳሳቢ” እንደሆኑም ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል። የሰዎች ሕይወት ማለፍን ጨምሮ በእነዚህ አካባቢዎች የሚደርሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፤ በማዕድን አውጭዎች እና ነባር ሕዝቦች መካከል በሚፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የሚከሰቱ እንደሆኑም አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር፤ ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጋር ተያይዞ የጸጥታ ኃይሎች “የዘፈቀደ እስሮችን” እንደሚፈጽሙም በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል። “በብሎገሮች እና ሚዲያ ስፔስ ላይ እስራት እና ተገቢ ያልሆነ መንገላታት እናያለን። ታሳሪዎችን ተከታትለን እያስፈታን ነው። በአዲስ አበባ መረጃው ቶሎ ስለሚደርሰን ከማስፈታት አንጻር የተሻለ አፈጻጸም አለ” ሲሉ አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።
ኮሚሽነሩ ይህን ቢሉም ምን ያህል እስረኞች እንዳሉም ሆነ ምን ያህሉን ማስፈታተ እንደተቻለ አሃዛዊ መረጃዎችን በመግለጫቸው አልጠቀሱም። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት አራት ጋዜጠኞች በእስር ላይ እንዳሉ የጋዜጠኞች የሰብአዊ መብት ተሟጋች (ሲፒጄ) መረጃ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)





























