የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሽብር ተከሳሹ ዶ/ር ሲሳይ አውግቼው የፈቀደውን የ100 ሺህ ብር ዋስትና፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጊዜያዊነት አገደ። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ዋስትናውን ያገደው፤ የፌደራል ዐቃቤ ህግ ለይግባኝ ሰሚ ችሎት ባቀረበው አቤቱታ ላይ ብይን እስኪሰጥ ድረስ ነው።
የአማራ ክልልን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት “በመግደል”፤ የክልሉን ቀጥሎም የፌዴራሉን መንግሥት ስልጣን “በኃይል ለመቆጣጠር” በማሰብ “የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል” በሚል ክስ ከቀረበባቸው 51 ተከሳሾች ውስጥ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ፤ ዋስትና የተፈቀደላቸው ባለፈው ሰኞ ዕለት ነበር። ተከሳሹ የዋስትናውን ሂደት አጠናቅቀው ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተለቀቁት ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ከሰዓት 10 ሰዓት ገደማ ነው።
ሆኖም በዚሁ ዕለት ዶ/ር ሲሳይ ሊቀበሏቸው ሲጠብቋቸው ከነበሩ ቤተሰቦቻቸው ጋር ሳይገናኙ፤ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት “በር ላይ ሆነው በጠበቋቸው” ፖሊሶች ተይዘው መወሰዳቸውን ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር። ተከሳሹ “ወደ ፌደራል ፖሊስ እየተወሰዱ” መሆኑን ለቤተሰቦቻቸው እንደተናገሩም በወቅቱ ተገልጿል።
ዶ/ር ሲሳይ በእርግጥም በዕለቱ የተወሰዱት፤ በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አደባባይ አቅራቢያ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ የእስረኞች ማቆያ መሆኑን ጠበቃ ሰለሞን አረጋግጠዋል። ደንበኛቸው በትላንትናው ዕለት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በአካል ቀርበው እንደነበርም አመልክተዋል።
የሽብር ተከሳሹ በችሎቱ የቀረቡት፤ የስር ፍርድ ቤት ለዶ/ር ሲሳይ የሰጠውን የዋስትና ብይን በመቃወም ዐቃቤ ህግ የይግባኝ አቤቱታ በማቅረቡ እንደሆነም አስረድተዋል። በትላንቱ ውሎው የዐቃቤ ህግን የይግባኝ አቤቱታ የሰማው ችሎቱ፤ ጉዳዩ “ያስቀርባል፣ አያስቀርብም” የሚለውን ለመወሰን ለዛሬ ቀጠሮ መስጠቱንም ጠበቃው አክለዋል።
በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ዐቃቤ ህግ እና የተከሳሹ ጠበቃ/ጠበቆች የቃል ክርክር ማድረጋቸውን አቶ ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዶ/ር ሲሳይን “ማህበራዊ ኃላፊነት እና የቤተሰብ አስተዳዳሪነት” ተመልክቶ ዋስትናውን መፍቀዱን የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ፤ ይህ “ተገቢ አይደለም” የሚል መከራከሪያ በዛሬው ችሎት ማቅረቡን ጠበቃው ጠቅሰዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት ዶ/ር ሲሳይ፤ ከኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ደብረብርሃን ከተማ እና በሌሎች አካባቢዎች ለነበሩ ተፈናቃዮች ድጋፍ በማሰባሰብ እና በማድረስ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ይሰሩ የነበሩ ናቸው። የተከሳሹ “ማህበራዊ እና የቤተሰብ ኃላፊነት”፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋስትና ለማስፈቀድ በተደረገው ክርክር ወቅት በደጋፊ ማስረጃነት የቀረበ ነበር።
ይህ ደጋፊ ማስረጃ መቅረብ ያለበት “ለቅጣት ማቅለያ” እንጂ ለዋስትና ክርክር አለመሆኑን ዐቃቤ ህግ በወቅቱ ገልጾ እንደነበር ጠበቃው አስታውሰዋል። ይህንኑ የዐቃቤ ህግ ሙግት፤ በዛሬው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ችሎት ላይ ማንሳታቸውን አቶ ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
ዐቃቤ ህግ ሌላው ለይግባኝ ሰሚ ችሎት ያቀረበው መከራከሪያ፤ ዶ/ር ሲሳይ በዋስ ቢወጡ በክሳቸው ላይ የተጠቀሰውን “የወንጀል ድርጊቱን ይፈጽማሉ” የሚል እንደነበር ጠበቃቸው ገልጸዋል። ዶ/ር ሲሳይ በተከሰሱበት ወንጀል “ይከላከሉ መባሉ ወደ ጥፋተኝነት ሊያመዝን ስለሚችል የዋስትና ግዴታቸውን አክብረው አይቀርቡም” በማለትም ዐቃቤ ህግ የስር ፍርድ ቤት ዋስትናው ውድቅ እንዲደረግ መጠየቁን አክለዋል።

የተከሳሹ ጠበቃ በበኩላቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋስትናውን የፈቀደው ደንበኛው የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት “ቀላል ስለሆነ ነው” በሚል በዛሬው ችሎት ላይ ተከራክረዋል። ዶ/ር ሲሳይ በተከሰሱበት ወንጀል “ተከላከሉ” መባላቸው “ወደ ጥፋተኝነት ሊያመዝን” እንደሚችል የሚያመለክት እንደሆነ በአቃቤ ህግ የቀረበው መከራከሪያ፤ ከፍርድ በፊት “ንጹህ ሆኖ የመገመት መብታቸውን የሚጥስ ነው” ሲሉም ጠበቃው ተችተዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ህገመንግስታዊ እና የሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት፤ ዶ/ር ሲሳይ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠው በክሳቸው ላይ በማስረጃነት ከቀረቡባቸው ስምንት የድምጽ ቅጂዎች መካከል አንዱን ብቻ በመቀበል መሆኑንም ጠበቃው በምላሻቸው አብራርተዋል። ይህ የድምጽ ቅጂ “ስልጠናችሁን ውሰዱ ከመንግስት ኃይል ጋር ግን አትጋጩ” የሚል መልዕክት ያለው መሆኑንም አቶ ሰለሞን ለችሎቱ አስረድተዋል።
ተከሳሹ ይህንን ንግግር ያደረጉት “ከሚሊሺያ አመራሮች ጋር” መሆኑን በመጥቀስ፤ ማስረጃውን “በአግባቡ መከላከል እንደሚችሉ” ለችሎቱ መናገራቸውንም ጠበቃቸው አክለዋል። ዐቃቤ ህግ በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ዶ/ር ሲሳይ “መርሃ ቤቴ አካባቢ ለፋኖ ስልጠና ሲሰጡ እንደነበር እና ስትራቴጂካዊ አመራር” እንደነበሩ ማንሳቱንም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

የፌደራል ዐቃቤ ህግ ዛሬ ለፍርድ ቤት ባሰማቸው ውንጀላዎች፤ “ክስም፣ ማስረጃም” እንዳልቀረበባቸው ጠበቃው ተናግረዋል። በዐቃቤ ህግ የቀረቡት ውንጀላዎች “አዲስ መከራከሪያ” እና “በክስ ሰነዱ ላይ ያለተካተተ” መሆኑን በማንሳትም መከራከራቸውን አብራርተዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ሰሚ ችሎት፤ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን የዋስትና ብይን ለጊዜው “ማገዱን” አቶ ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በተከሳሽ የዋስትና ጥያቄ ላይ የቀረቡትን መከራከሪያዎች መርምሮ ብይን ለመስጠት ለቀጣዩ ሳምንት አርብ የካቲት 27፤ 2018 ቀጠሮ መስጠቱንም አክለዋል።
ፍርድ ቤቱ ብይኑን እስኪሰጥ ድረስ፤ ተከሳሹ ቀድሞ ወደ ነበሩበት ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንዲዘዋወሩም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው፤ ተከሳሹ ከትላንት በስቲያ ምሽት ጀምሮ ተይዘው ያሉበት የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የእስረኞች ማቆያ “ምቹ አለመሆኑን” በማንሳት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት መሆኑን ጠበቃው አስረድተዋል።

በዛሬው የችሎት ውሎ፤ ዶ/ር ሲሳይ ዋስትና ተፈቅዶላቸው ከማረሚያ ቤት ሲወጡ “በህገወጥ መንገድ” ተይዘው ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸው “አግባብ አለመሆኑን” በመጥቀስ ተጨማሪ አቤቱታ ማቅረባቸውን ጠበቃቸው ተናግረዋል። ተከሳሹ ተይዘው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ አለመስጠቱን ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ማስታወቁንም ገልጸዋል።
ችሎቱ ይህን መሰሉ አቤቱታ በህጉ መሰረት መቅረብ ያለበት፤ የዋስትና ብይኑን ለሰጠው የከፍተኛው ፍርድ ቤት እንደሆነ ምላሽ መስጠቱንም አቶ ሰለሞን አመልክተዋል። ዶ/ር ሲሳይ የተያዙበትን ሁኔታ በተመለከተ በችሎቱ ጥያቄ የቀረበለት ዐቃቤ ህግ፤ ተከሳሹ ከእስር ቤት ሲወጡ ስለመያዛቸው “በሚዲያ ከመስማት ውጪ የማውቀው ነገር የለም” ማለቱን ጠበቃው ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























