የመንግስት እና የግል ባንኮች ለተለያዩ ዘርፎች የሚሰጧቸውን ብድሮች፤ ለአምራች ኢንዱስትሪዎችም “ፍትሃዊ በሆነ መንገድ” እንዲያከፋፍሉ ግዴታ የሚጥል አዲስ ህግ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ እንደሚወጣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። በሀገሪቱ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር በመተባበር፤ ለአፍሪካ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ማከፈፈል የሚያስችሉ ኩባንያዎችን “መፍጠር” እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ይህን ያሉት፤ ለአራተኛ ጊዜ የተዘጋጀውን “ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ” በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው። ዛሬ እሁድ ሚያዝያ 25፤ 2018 በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል የተከፈተው እና ለተከታታይ አምስት ቀናት ለጎብኚዎች ክፍት ሆኖ በሚቆየው በዚህ ኤክስፖ “ከአምስት ቢሊየን ብር በላይ ግብይት ይፈጸማል ተብሎ እንደሚጠበቅ” የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሁለት ምዕራፎች ክፍሎች ሲተገብረው በቆየው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ “ምሰሶ ናቸው” ከሚላቸው አምስት ዘርፎች ኢንዱስትሪ አንዱ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚህ ዘርፍ ተመዝግበዋል ያሏቸውን እድገቶች፤ በቅርብ ጊዜ በተሳተፉባቸው መድረኮች እና ባገኟቸው አጋጣሚዎች ላይ በተደጋጋሚ ሲያነሱ ተደምጠዋል።

በዛሬው የኤክስፖ መክፈቻ ንግግራቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ አስተጋብተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በአምራች ኢንዱስትሪዎች ያሉ ችግሮች ለመፍታት “የኢንዱስትሪ ስትሪንግ ኮሚቴ” አቋቁሞ ላለፉት ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት አብይ፤ ይህን ተከትሎም “በመሬት፣ በኃይል እና በፋይናንስ” አቅርቦት ረገድ “መሻሻሎች” መታየታቸውን አስገንዝበዋል።
ይሁንና በመንግስታቸው በቅርቡ በተደረገ ግምገማ፤ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ለኢንዱስትሪ የሚያቀርቡት የብድር ድጋፍ “አነስተኛ ሆኖ እንዳገኙት” በዘርፉ ለተሰማሩት የኤክስፖው ተሳታፊዎች ተናግረዋል። በ2018 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት በአጠቅላይ በባንኮች የተሰጠ ብድር 2.42 ትሪሊዮን ብር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ አስታውቆ ነበር።
በሀገሪቱ ካሉ ባንኮች የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተመሳሳይ ወር ባወጣው መግለጫ፤ ባንኩ በግማሽ ዓመቱ የሰጠው 321 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጿል። ከዚህ የገንዘብ መጠን ውስጥ ለግሉ ዘርፍ የተሰጠው ብድር 91 በመቶውን የሚሸፍን መሆኑን የገለጸው ባንኩ፤ ከተበዳሪዎቹ ውስጥ ነጋዴዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎች እና አምራቾች እንደሚገኙበትም በወቅቱ ይፋ አድርጓል።

ባንኩ ባለፈው ሐሙስ ባወጣው መረጃ ደግሞ በዘንድሮው ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ያቀረበው የብድር መጠን 514.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን አመልክቷል። ከዚህ የብድር መጠን ውስጥ ለመንግስት ዘርፍ የቀረበው 42.6 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን እና ቀሪው ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ መሆኑንም ባንኩ አክሏል።
የማዕከላዊው ባንክ እና ዋነኛው የመንግስት ባንክ መረጃዎች በብድር አቅርቦት ረገድ እድገቶች መመዝገባቸውን ቢገልጹም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ግን አምራች ኢንዱስትሪው ከሌሎች ዘርፎች ጋር ሲነጻጸር “ፍትሃዊ የሆነ የብድር ክፍፍል እያገኘ አይደለም” የሚል ግምገማ አላቸው። አብይ ይህንኑ አቋማቸውን፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ ቃለ ምልልሳቸው ላይ በምሳሌ አስደግፈው አቅርበው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ንግግራቸው “ሀብትን ለሁሉም ዘርፍ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ክፍፍል መፍጠር” የሚያስችል ህግ በመንግስታቸው በኩል እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል። “በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ይወጣል” የተባለው ይኸው ህግ፤ በመንግስትም ሆነ በግል ባንክ ያለው “የኢትዮጵያ ሀብት ምን ያህል ፐርሰንቱ ወደ ኢንዱስትሪ መፍሰስ እንዳለበት” ግዴታ የሚጥል እንደሆነ አስረድተዋል።

“ኢንዱስትሪው ሊያገኝ የሚገባውን ድርሻ እንዲያጣ ያደረጉ ሰው ፈጠር ችግሮች የሚቀረፉበት ህግ ለማውጣት የኢትዮጵያ መንግስት በስራ ላይ ስለሆነ፤ ይህ ለእናንተ ትልቅ ብስራት ስለሆነ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለሁ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው የ“ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ” መክፈቻ ለታደሙ ተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሆኖም አብይ አዲሱ ህግ ከፋይናንስ ጋር በተያያዘ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚገጥማቸውን “ተግዳሮት” “እንዳለ ይቀርፋል ብዬ መናገር ያስቸግረኛል” ሲሉ ተደምጠዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ በምክንያትነት ያስቀመጡት ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ያለው ሀብት፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን “ፍላጎት ሊመልስ አይችልም” የሚል ነው።
“መቶ ፐርሰንት ያለንን ሀብት ለኢንዱስትሪ ማበደር ብንወስን፤ እዚህ ውስጥ ካላችሁ 20፣ 30 ሰዎች አያልፍም። ብዙ ሃብት ካልፈጠርን በቀር፤ አሁን ያለው ሀብት በቂ አይደለም። ያ ያለው ሀብት ግን በትክክለኛው መንገድ፣ ለሁሉም ሴክተር ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ክፍፍል መፍጠር እንዲቻል፣ ሁሉ ነገር ንግድ፣ ሁሉ ነገር ኮንትሮባንድ ብቻ እንዳይሆን፤ በህግ የሚቀየር ይሆናል” ሲሉ አብይ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ንግግራቸው፤ በኢትዮጵያ ያሉ አምራቾች “ማምረት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ገበያ ለመሻማት በሚያስችል መንገድ ማዘጋጀት” እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝበዋል። “የኢትዮጵያ አምራቾች ‘አምርቱ…አምርቱ’ ስትባሉ ነበር። አሁን ደግሞ ውጡ” ሲሉ የሀገሪቱ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን ለአፍሪካ ገበያ እንዲያቀርቡ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።
“አምስት፣ አስር፣ 15 ኩባንያ፤ ከቻለ በግል፣ ካልቻለ በህብረት፣ አልያም ከመንግስት ጋር እየተቀናጀ ቢያንስ በተመረጡ አምስት፣ አስር አፍሪካ ሃገራት የእኛ ኩባንያዎች መሄድ አለባቸው” ያሉት አብይ፤ እርሳቸው የሚመሩት መንግስትም በዚህ ረገድ የራሱን የቤት ስራ እንደሚያከናውን ገልጸዋል። በአፍሪካ ሀገራት ገበያዎች የሚሰማሩ ኩባንያዎችን “መፍጠር”፤ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር “በትስስር ሊሰራ” የሚገባው “ወቅታዊ ጉዳይ” መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)































