ከትላንት በስቲያ ሰኞ 100 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንዲፈቱ በፍርድ ቤት የተበየነላቸው ዶ/ር ሲሳይ አውግቼው፤ በዛሬው ዕለት ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በመውጣት ላይ እንዳሉ “በር ላይ ሲጠብቋቸው በነበሩ ፖሊሶች ተይዘው መወሰዳቸውን” ጠበቃቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ተከሳሹ “ወደ ፌደራል ፖሊስ” እየተወሰዱ መሆኑን፤ ሊቀበሏቸው ሲጠብቋቸው ለነበሩ ቤተሰቦቻቸው አሳውቀዋል ተብሏል።
ዶ/ር ሲሳይ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሰው የፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋራ በመሆን “የአማራ ክልልን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በመግደል የክልሉን ቀጥሎም የፌዴራሉን መንግሥት ስልጣን በኃይል ለመቆጣጠር በማሰብ የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል” በሚል ክስ ከቀረበባቸው 51 ተከሳሾች ውስጥ አንዱ ናቸው። በዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ስር የሚገኙት እነዚህ ተከሳሾች “የሽብር ክስ” የቀረበባቸው በሰኔ 2015 ዓ.ም ነበር።
አምስት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተካተቱበት በዚህ ክስ ስር ካሉ ተከሳሾች ውስጥ በቅርቡ “የሰላም አማራጭ መቀበላቸውን” ያሳወቁትን ኮሎኔል ፋንታሁን ሙሃባውን ጨምሮ የሃያ ስምንቱ ጉዳይ ሲታይ የቆየው በሌሉበት ነበር። የተከሳሾቹን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ህገ መንግስታዊ እና የሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
ፍርድ ቤቱ ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ባስቻለው ችሎት፤ ከተከሳሾቹ ውስጥ ስድስቱ በነጻ እንዲሰናበቱ ብይን ሰጥቶ ነበር። በዚህም መሰረት ዮርዳኖስ አለሜ፣ ተስፋዬ መኩሪያ፣ ዳዊት እባቡ፣ አብርሃም ጌትነት፣ ማስረሻ እንየው እና ቢሰጥ ተረፈ የተባሉት ተከሳሾች መፈታታቸውን ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በዚሁ ችሎት ዶ/ር ሲሳይ እና አቶ ሞላልኝ ሲሳይ የተባሉ ሌላ ተከሳሽ፤ የተከሰሱበት የህግ ድንጋጌ ተቀይሮ የዋስትና ክርክር እንዲያደርጉ ውሳኔ ተላልፎ ነበር። በዚህም መሰረት የተከሳሾቹ ጠበቆች እና አቃቤ ህግ የዋስትና ክርክር ማድረጋቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።
ሁለቱ ወገኖች በጹሁፍ ያቀረቡትን ክርክር የመረመረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ዶ/ር ሲሳይ የ100 ሺህ ብር ዋስትና በማስያዝ ከእስር እንዲለቀቁ ከትላንት በስቲያ ሰኞ የካቲት 16፤ 2018 ብይን መስጠቱን ጠበቃው አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱ በዚሁ የችሎት ውሎው፤ የሌላኛው ተከሳሽ አቶ ሞላልኝን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ማድረጉንም አክለዋል።

የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ፤ ለዋስትና የተጠየቀውን ገንዘብ የዶ/ር ሲሳይ ቤተሰቦች በዚያኑ ቀን ረፋድ ላይ “እዚያው በሞባይል ባንኪንግ” መክፈላቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን፤ ችሎቱም ተከሳሹ የሚፈቱበትን ትዕዛዝ ፈርሞ ሰጥቷቸው ወደ ማረሚያ ቤት ይዘውት ሄደው እንደነበር አብራርተዋል። የእስረኛ መፍቻ ትዕዛዙ የደረሰው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት፤ ለፍርድ ቤት “የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ” ለሁለት ቀናት ሳይፈታቸው መቆየቱን ጠበቃቸው ተናግረዋል።
የዶ/ር ሲሳይ ጠበቆች በማረሚያ ቤቱ የቀረቡትን ምክንያቶች ተከላክለው፤ ጉዳዩ በዛሬው ዕለት በፍርድ ቤት እልባት አግኝቶ እንደነበር አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። የተከሳሹ ቤተሰቦች የዋስትናው ብይን እንዲፈጸም የሚያዝ የፍርድ ቤት ደብዳቤ በመያዝ ዛሬ ከሰዓት ወደ ማረሚያ ቤት ሄደው እንደነበር ጠበቃው አመልክተዋል።
በዚህ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ ከእስር የተለቀቁት ዶ/ር ሲሳይ፤ ቤተሰቦቻቸውን አግኝተው፣ ከማረሚያ ቤት ይዘው የወጡትን ልብስም አቀብለዋቸው እንደነበር አቶ ሰለሞን አስረድተዋል። ሆኖም ተከሳሹ ወደ ቤታቸው ለመሄድ በመዘጋጀት ላይ ሳሉ፤ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በር ላይ የነበሩ “ፌዴራል ፖሊሶች መኪና ውስጥ አስገብተው እንደወሰዷቸው” ቤተሰቦቻቸውን ዋቢ በማድረግ ጠበቃቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል።

ዶ/ር ሲሳይ በፖሊስ መኪና ውስጥ ከገቡ በኋላ “እጃቸውን በመስኮት አውጥተው”፤ ቤተሰቦቻቸውን “በሉ ቻው ወደ ፌዴራል ፖሊስ ይዘውኝ እየሄዱ ነው” ማለታቸውን እህታቸው እንደነገሯቸው አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። ሆኖም ተከሳሹ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ መልኩ እስረኞች ወደሚወሰዱበት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የእስረኞች ማቆያ መወሰዳቸውን ጠበቃው ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ማረጋገጥ አልቻሉም።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበሩት ተከሳሹ፤ በማረሚያ ቤት ሳሉ የፒ.ኤች.ዲ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው የዶክትሬት ዲግሪ ማግኘታቸውን ከጠበቃቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ዶ/ር ሲሳይ ከኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው፤ በአማራ ክልል ደብረብርሃን ከተማ እና በሌሎች አካባቢዎች ለነበሩ ተፈናቃዮች ድጋፍ በማሰባሰብ እና በማድረስ የበጎ አድራጎት ስራዎችን ይሰሩ የነበሩ ናቸው።
በዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸውን እንደ ዶ/ር ሲሳይ ሁሉ በአካል ሲከታተሉ ከቆዩ 23 ተከሳሾች መካከል አራቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ናቸው። ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ የቆዩት ጎበዜ ሲሳይ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ገነት አስማማው እና መስከረም አበራ፤ በሞት ወይም በዕድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ ክስ የቀረበባቸው ናቸው።
የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት (ሲፒጄ) በትላንትናው ዕለት በኤክስ ገጹ ባሰራጨው መልዕክት፤ እነዚህ አራት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች “ፍትሃዊ እና ግልጽ” የፍርድ ሂደት ማግኘታቸውን እንዲያረጋግጡ ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጥሪ አቅርቧል። የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ የተወሰነባቸው አራቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፤ በመጪው ሚያዝያ መጨረሻ ገደማ የመከላከያ ማስረጃቸውን እንዲያሰሙ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)






























