የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ለሚገኙ ዜጎች ማስጠንቀቂያ ሰጡ

በኳታር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና መቀመጫውን በባሕሬን ዋና ከተማ ማናማ ያደረገው ቆንስላ በየሀገራቱ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የደህንነት ማስጠንቀቂያ ሰጡ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በመካከለኛው ምስራቅ ባለው “የጸጥታ ሁኔታ” ምክንያት የተወሰኑ በረራዎቹን እንደሰረዘ ይፋ አድርጓል።

የበረራ ስረዛው የተደረገው እና የደህንነት ማስጠንቀቂያው የተሰራጨው፤ እስራኤል እና ዩናይትድ ስቴትስ ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 21፤ 2018 ረፋድ ጀምሮ በኢራን ላይ ወታደራዊ ጥቃት ከጀመሩ በኋላ ነው። ኢራን በሁለቱ ሀገራት ለተፈጸመባት ጥቃት፤ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማት ወዳሉባቸው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ሚሳኤሎችን በመተኮስ አጸፋውን መልሳለች። 

በኢራን ኢላማ ከተደረጉ ሀገራት አንዷ በሆነችው ባህሬን የምትኖር አንዲት ኢትዮጵያዊት፤ “ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ” መስማቷን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጻለች። ጥቃት ስለተፈጸመበት ቦታ የምታውቀው ነገር እንደሌለ የተናገረችው በባህሬን ዋና ከተማ ማናማ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ በመስራት ላይ የምትገኘው ይህቺው ኢትዮጵያዊት፤ በሁኔታው ፍርሃት እንዳደረባት አስረድታለች። 

በባህሬን መዲና ምስራቃዊ ክፍል የምትኖረው ሁለተኛዋ ኢትዮጵያዊትም፤ ዛሬ ረፋድ ላይ የፍንዳታ ድምጽ መስሟቷን አረጋግጣለች። በከተማው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የደህንነት ስጋት እንዳለም ገልጻለች። በማናማ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል ጽህፈት ቤትም፤ ዛሬ ከሰዓት በፌስቡክ ገጹ “አስቸኳይ የደህንነት መመሪያ” በሀገሪቱ ላሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን  አሰራጭቷል።

ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ የደህንነት መመሪያ የያዘውን መግለጫ ያወጣው “በአሁኑ ወቅት በቀጠናው እየታየ ባለው ወታደራዊ ውጥረት” እና “ዛሬ በባህሬን የተፈጸመውን የሮኬት ጥቃት ተከትሎ” መሆኑን አስታውቋል። በባህሬን የሚገኙ ዜጎች “በአካባቢው መገናኛ ብዙኃን የሚወጡ ይፋዊ መግለጫዎችንና ዜናዎችን በንቃት” እንዲከታተሉም አሳስቧል።

“የባህሬን የጸጥታ ኃይሎች እና የሲቪል መከላከያ (Civil Defence) የሚሰጧቸውን ትዕዛዞች እና መመሪያዎች ያለ ምንም መዘግየት ተግባራዊ” እንዲያደርጉ ቆንስላው መክሯል። በባህሬን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን “አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር” እንቅስቃሴ እንዲቀንሱ “ሁከት ወይም ግጭት ሊኖርባቸው ከሚችሉ አካባቢዎች” እንዲርቁ አስጠንቅቋል።

በሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች የምግብ፣ የውሃ እና የመድኃኒት ክምችቶችን ለጥንቃቄ አስቀድመው እንዲይዙም ቆንስላው ምክር ለግሷል። በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በበኩሉ “ዜጎቻችን በቤታችሁ እንድትሆኑ ወይም አሁን ካላቸሁበት ስፍራ እንዳትንቀሳቀሱ” የሚል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። 

ኤምባሲው ማስጠንቀቂያውን የሰጠው የኳታር መንግስትን ማሳሰቢያ መሰረት በማድረግ ነው። የኳታር መንግስት “ለህዝብ ደህንነት ሲባል፣ ማንም ሰው ከወታደራዊ ስፍራዎች አቅራቢያ እንዲርቅ እና በቤት ውስጥ እንዲቆይ” እንዳሳሰበ ኤምባሲው አስታውቋል። በኳታር “በጣም አስፈላጊ እና አስቸኳይ ካልሆነ በስተቀር [ማንኛውም ሰው] ከመኖሪያ አካባቢ እንዳይርቅ ወይም እንዳይንቀሳቀስ” ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ኳታር በቀጠናው በተፈጠረው የጸጥታ ቀውስ ምክንያት የአየር ክልላቸውን ለበረራ ከዘጉ ሀገራት አንዷ ነች። ተመሳሳይ እርምጃ የወሰዱት ሌሎች ሀገራት፤ ኢራን፣ እስራኤል፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ባህሬን፣ ኩዌት እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ናቸው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ከሰዓት ባሰራጨው መልዕክት፤ እስካሁን በመካከለኛው ምስራቅ ወደሚገኙ አራት ከተሞች የሚያደርገውን በረራ እንደሰረዘ አስታውቋል።

አየር መንገዱ በመካከለኛው ምስራቅ ባለው “የጸጥታ ሁኔታ” ምክንያት ወደ አማን፣ ቴል አቪቭ፣ ደማም እና ቤይሩት የሚደረጉ በረራዎችን መሰረዙን ይፋ ባደረገበት መግለጫው፤ ሁኔታውን በቅርበት በመከታተል ላይ እንደሚገኝም አመልክቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሳፋሪዎችን እና የሰራተኞቹን ደህንነት እና ምቾት ለማረጋገጥ “ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ” ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)