ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን የሚነካውን የቅኝ ግዛት ውል እንደማትቀበል ለጸጥታው ምክር ቤት አስታወቀች

በሐይማኖት አሸናፊ

ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በግብፅ ለቀረበባት ሁለተኛ ክስ በሰጠችው መልስ ግብጽ የምታቀርባቸው ወቀሳዎች፤ ኢትዮጵያ በቀጣይ በአባይ ላይ ልማት እንዳታካሂድ ለማደናቀፍ በማሰብ፤ በተለይም “የውሃ ክፍፍል እና የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ለማስቀጠል በማሰብ ነው” ስትል አጣጣለች።

“ኢትዮጵያ እንዲህ ያሉ ሃሳቦችን አትቀበልም፤ ይህም በአባይ ላይ ያለንን ህጋዊ እና ሉዓላዊ መብቶች የሚጋፋ ብሎም ለወደፊት በወንዙ ላይ ለምናካሂደው ልማት እንቅፋት ነው” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ትላንት ሰኞ ሰኔ 15፤ 2012 በላኩት ጠንከር ያለ የመልስ ደብዳቤ አስታውቀዋል። 

ለጸጥታው ምክር ቤት የተላከው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከታማኝ ምንጮቿ ያገኘችው ይሄው ባለ 78 ገፅ ምላሽ፤ በተለይም በድርቅ ቅነሳ እርምጃዎች ስም በግብጽ እየተሞከረ ያለው የቅኝ ግዛት ውሎችን አጠናክሮ በኢትዮጵያ ላይ የመተግበር አዝማሚያ መሆኑንም ገልጿል። “በተባበሩት መንግስታት ቻርተር መርሆዎች እና ህግ የሚገዛ የትኛውም ነጻ አገር እንዲሁም አለማቀፍ ተቋም ይህንን ጠበኛ እና ህገወጥ አካሄድ አይደግፍም” ሲል ኢትዮጵያ ለጸጥታው ምክር ቤት የላከችው አቤቱታ አባሪ ያስረዳል።

ለምክር ቤቱ በሚያዚያ 2012 ቀድማ አቤት ያለችው ግብጽ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት በወርሃ ሐምሌ 2012 ያለስምምነት የሚካሄድ ከሆነ “ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ይሆናል” ብላ ነበር። ግብጽ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለምክር ቤቱ ባስገባችው ሁለተኛው ማመልከቻዋ ደግሞ ስጋቱን ወደ ዓለማቀፍ ደረጃ ከፍ አድርጋ አቅርባለች። 

ግድቡ ያለ ስምምነት የሚሞላ ከሆነ “ዓለማቀፍ ሰላም እና ደህንንነትን አደጋ ውስጥ ሊጥሉ የሚችሉ አጸፋዊ እርምጃዎች ልትወሰድ እንደምትችል” አስጠንቅቃለች። ለዚህ ምላሽ የሰጠችው ኢትዮጵያ “በእርግጥ ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ የትኛውም አይነት የሰላም እና የጸጥታ ስጋት ካለ፤ የጦርነት ነጋሪት ስትጎስም እና ስትፎክር የነበረችው ግብጽ ኃላፊነቱን ትወስዳለች” ስትል አጽንኦት ሰጥታለች። 

ድርድሮቹ በፍጥነት እንዳይከናወኑ ግብጽ የምታነሳው የታሪካዊ እና አሁናዊ አጠቃቀም መብት (historic rights and current use) እንቅፋት መፍጠሩንም በምላሿ ላይ ገልጻለች። “ግብጽ ይህንን መብት በ1951 ከሱዳን ጋር ባሰረችው የቅኝ ግዛት ውል አግኝቼዋለሁ የምትል ሲሆን ይህ ስምምነት ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ አግልሎ የአባይ ወንዝ የአንበሳ ድርሻን ለግብጽ የሰጠ የቅኝ ግዛት ስምምነት ነው” ስትል ኢትዮጵያ ሞግታለች። ኢትዮጵያ ከግብጽ የሚቀርብባትን ለብቻዋ የመወሰን ወቀሳንም “ከልክ ያለፈ ግብዝነት” ስትል ጠርታዋለች። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ “ከዚህ ቀደም በላኩት ደብዳቤ ላይ አንደገለፅኩት ግብጽ ናት ኢትዮጵያን ሳታማክር የአስዋን ሃይ ግድብን የገነባቸው። ግብፅ ናት ከኢትዮጵያ ዘንድ በተደጋጋሚ ‘የውሃ መስረተ ልማቶችሽ ለእኛም ሆነ ለሌሎች የአባይ ተፋሰስ አገራት ጉልህ ጉዳት ያመጣል’ የሚል ተቃውሞ ሲነሳባት ወደ ኋላ ያለችው። ግብጽ ናት የናይል ወንዝን የተፈጥሮ ፍሰት በፒስ እና ቶሽካ ቦዮች በኩል የቀየረችው። በተጨማሪም ግብጽ ናት በናይል ወንዝ ዙሪያ በቀጠናው ከተፋሰሱ አገራት ጋር ለ10 ዓመታት ንግግር እና ድርድር ቢደረገም የትብብር ማዕቀፉን በሂደት ውድቅ ያደረገቸው” ሲሉ በደብዳቤያቸው ጠንካራ ሙግት አቅርበዋል።

የሶስትዮሽ ድርድሩ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ሶስቱ አገራት የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት በሁለት ክፍል እንዲካሄድ መስማማታቸውን የሚገልጸው ደብዳቤው በመጀመሪያው ክፍል ግድቡ በ4.9 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር (ቢሲኤም) እና በሁለተኛው ደግሞ በ13.5 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር እንዲሞላ መታቀዱን ያስረዳል። “የመጀመሪያው ከፍል የውሃ ሙሌት ያለ ቅድመ ሁኔታ መካሄድ ነበረበት” የምትለው ኢትዮጵያ በሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ላይ መለሳለስ አሳይታለች። 

ወደ ግድቡ የሚገባው የወንዝ ፍሰት ከ31 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር በታች ከሆነ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌቱን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ መስማማቷን በደብዳቤው አባሪ ላይ ተጠቅሷል። ኢትዮጵያ በዚህ አካሄድ ላይ ለመስማማት የወሰነችው ትብብርን ለማጎልበት እና ለጥሩ ጉርብትና ስትል እንደሆነም በአባሪው ላይ አብራርታለች።  

“የታላቁን ህዳሴ ግድብ ለመሙላት ከያዝነው አመት የተሻለ ወቅት የለም” የምትለው ኢትዮጵያ ሳይንሳዊ ማስረጃዎችን ለጸጥታው ምክር ቤት አቅርባለች።  ለዚህም የጥቁር አባይ እና የነጭ አባይ ከመደበኛ ፍሰታቸው በላይ የሚሆኑበት አመት መሆኑን የጠቀሰችው ኢትዮጵያ የቪክቶሪያ ሃይቅም በታሪኩ ትልቁ ከፍታ ላይ መገኘቱንም አንስታለች። የግብጹ የአስዋን ሃይ ግድብም ቢሆን ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከአጠቃላይ የመያዝ አቅሙ ሁለት ሜትር ብቻ ዝቅ ብሎ ከባህር ጠለል በላይ በ180 ሜትር ላይ መገኘቱንም በተጨማሪ ማስረጃነት አያይዛለች።   

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ኢትዮጵያ ከህዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ ለጸጥታው ምክር ቤት ሌላ ደብዳቤ በመፃፏ እንደሚያዝኑ ገልጸው ሆኖም ሀገራቸው ያንን ያደረገችው በግብጽ ምክንያት አስገዳጅ ሁኔታ በመፈጠሩ ነው ብለዋል። ግብጽ አርብ ሰኔ 12፤ 2012 የህዳሴ ግድቡን የአለማቀፍ ፀጥታ ስጋት አድርጋ በማቅረቧ እና ምክር ቤቱም ጣልቃ እንዲገባ መጠየቋ ኢትዮጵያን ምላሽ እንድትሰጥ እንዳስገደዳት አብራርተዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት የተደረጉ የሶስትዮሽ ድርድሮች ለውጥ እያሳዩ ባሉበት፤ ግብጽ ያንን ወደ ጎን በማለት ጉዳዩን ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ማምጣቷ  “አያስገርመኝም” ብላለች ኢትዮጵያ። የጸጥታው ምክር ቤት “ፍትሃዊ እና ሁሉንም ተጠቃሚ እና አሸናፊ የሚያደርግ ውጤትን” የተጸረረ አገርን እንዳይደገፍም ጥሪዋን አቅርባለች።

በግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌት ቴክኒካዊ ጉዳዮች እና የግድቡ የዓመታዊ የዕለት ተዕለት ተግባርን በተመለከተ እየተደረገ የነበረው ድርድር የተቋረጠው የሱዳን ልዑክ ከሀገራቸው መሪ ጋር ለመማከር በመጠየቁ መሆኑን ኢትዮጵያ ገልፃለች። ሀገራቸው ቀሪዎቹን ሂደቶች በሰላማዊ ድርድር በመመፍታት እንደምታምንም ገዱ በደብዳቤያቸው ላይ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)