ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባት መድረክ በሁለት ወር ውስጥ ሊካሄድ ነው

በተስፋለም ወልደየስ 

በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባት ለማምጣት ያለመ መድረክ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ሊካሄድ ነው። መድረኩን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ዴስትኒ ኢትዮጵያ እና የሃሳብ ማዕድ የተባሉ ተቋማት በጋራ የሚያዘጋጁት እንደሆነ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

የብሔራዊ ምክክር ሂደቱ ዓላማ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወይይቶ ችግሮችን የመፍታት ባህል መገንባት መሆኑን ተቋማቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ አመልክተዋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአስቸኳይ የሚያስፈልጋት “የተቀናጀ ብሔራዊ ምክክር ነው” የሚል እምነት ያላቸው ሶስቱ ተቋማት፤ “ልዩነቶችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት ስምምነት የሚደረስበት መድረክ ለማመቻቸት” መነሳታቸውን ገልጸዋል። 

ተቋማቱ ተባብረው ለመስራት ከመወሰናቸው በፊት ወራትን የፈጀ ጥልቅ ውይይት ማድረጋቸውንና ከሰላም ሚኒስቴርም ለስራው ይሁንታ እና እውቅና ማግኘታቸውን በመግለጫቸው አንስተዋል። ሚኒስቴሩ ይህን ውጥን ለማስፈጸም አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊና የደህንነት ድጋፍ ለማድረግ መስማማቱን እና የሂደቱ አካል ለመሆንም የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን በመግለጫቸው ይፋ አድርገዋል።    

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም፤ በሀገሪቱ “የምርጫ ጉዳዮችን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ትኩሳቶች አሉ” ብለዋል

ከውይይቱ አመቻች ተቋማት አንዱ የሆነውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ ሙሳ አደም፤ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ከታሰበው ምርጫ በፊት መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች እንዲመለሱ መድረኩ የራሱን ሚና እንደሚጫወት በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። በሀገሪቱ “የምርጫ ጉዳዮችን ጨምሮ የተለያዩ የፖለቲካ ትኩሳቶች አሉ” ያሉት አቶ ሙሳ፤ እነዚህ ጉዳዮች በመድረኩ ላይ ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ጠቁመዋል።  

“የፌደራል እና የክልል መንግስታት ግንኙነቶች፣ የክልል እና የክልል መንግስታት ግንኙነቶች መሻከር እና የመሳሰሉት በጣም አንገብጋቢ ጉዳዮች፤ ሀገራችን ላይ በየጊዜው፣ እንደየቦታው፣ በተለያዩ ጊዜያቶች እየተነሱ ይገኛሉ። እነዚህን በተቻለ ፍጥነት ቶሎ ወደ መድረክ ማምጣትና ወደ አንድ አቅጣጫ ሰብስቦ ዋናውን መድረክ ማስጀመር ነው” ብለዋል።  

“በሀገሪቱ የሚስተዋለው የልሂቃን አለመስማማት ተቋማቱ ለማምጣት ለሚፈልጉት ብሔራዊ መግባባት ተግዳሮት አይሆንም ወይ?” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበ ጥያቄ አቶ ሙሳ በሰጡት ምላሽ፤ የልሂቃን ግጭት፣ የታሪክ አለመስማማት እና የሀገረ መንግስቱ አወቃቀር ቀደም ካሉ ጊዜያት አንስቶ እየተንከባለሉ የመጡ መሆናቸውን ተቋማቱ እንደሚገነዘቡ አስረድተዋል።

የፖለቲካ እስረኞችን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች በሀገሪቱ እንዳሉ የሚቀበሉት አቶ ሙሳ፤ አሁን ያለው የተቋማት ስብስብ፣ ወደፊት ይህንኑ ቡድን ከሚቀላቀሉ አካላት ጋር በመሆን ለእነዚህ ችግሮች “መቋጫ የማበጀት” ሀሳብ እንዳለው ተናግረዋል። 

የብሔራዊ መግባባት መድረኩ እስካሁን በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሲደረጉ ከነበሩት ውይይቶች የተለየ መሆኑን የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ ተናግረዋል

“እኛ ለእነዚህ መሰረታዊ፣ ሀገራዊ ጥያቄዎች መልስ የምንሰጥ ሰዎች አይደለንም። የእኛ ስራ ምንድነው? እነዚህ ጥያቄዎች የሚመለሱበትን መድረክ ማመቻቸት እና በተለያዩ ጥግ ላይ ያሉ ግለሰቦች እና አስተሳሰቦች በአንድ መድረክ ላይ፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ጉዳዮቻቸውን አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት፣ አራት እያሉ አንስተው፤ ወደ አንድ አቅጣጫ መሄድ እንዲቻል ነው” ሲሉ በተቋማቱ ተነሳሽነት የሚዘጋጀውን የውይይት መድረክ ዋና ዓላማ አብራርተዋል። 

የምክክር መድረኩ እስካሁን በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሲደረጉ ከነበሩት ውይይቶች የተለየ መሆኑን የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ዋና አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ ተናግረዋል። የብሔራዊ መግባባት መድረኩ የሚለየው በተሳታፊዎቹ አይነት መሆኑንም ጠቁመዋል። 

“የፖለቲካ ፓርቲዎች በእርግጥ ይሳተፋሉ። ከዚያ በተጨማሪ ግን በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት ነው። ምሁራን፣ የሚዲያ ባለሙያዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አርብቶ አደሮች፣ በሌላም ሙያ ያሉ አካላት የሚሳተፉበት ነው። ለዚህም ነው ሁሉን አቀፍ ብለን የሰየምነው” ሲሉ ልዩነቱን አስረድተዋል። 

የብሔራዊ መግባባት መድረኩ በአንድ ጊዜ ብቻ የሚከውን ሳይሆን ቀጣይነት ያለው ሂደት እንደሆነ የሚናገሩት የተቋማቱ ተወካዮች ምክክሩ በምዕራፍ ተከፋፍሎ በየጊዜው እንደሚካሄድ አመልክተዋል። ምክክሩ ከታየዘለት የጊዜ ገደብ በፈጠነ ጊዜ እንዲካሄድ ጥረት ይደረጋልም ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)