በሃሚድ አወል
ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን በመግደል ጥፋተኛ የተባለው አንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ በሞት እንዲቀጣ ዐቃቤ ህግ ጠየቀ። ዐቃቤ ህግ የሞት ፍርዱን የጠየቀው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ባቀረበው የቅጣት አስተያየት ነው።
ዐቃቤ ህግ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 8 ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው የቅጣት ማክበጃ፤ ተከሳሹ ከዚህ በፊት በባጃጅ እና የባቡር ሃዲድ ስርቆት ተከስሶ እንደነበረ እና በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ክሱ መቋረጡን አንስቷል። ተከሳሹ ‛‛ነውጠኛ ባህሪ እንዳለው ከምስክር መሰማቱን’’ በተጨማሪ የቅጣት ማክበጃነትም ጠቅሷል። በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን የቅጣት ማቅለያ ሳይመለከት የሞት ፍርድ ብያኔ እንዲሰጥ ዐቃቤ ህግ ጠይቋል።
ሁለተኛ ተከሳሽ ከበደ ገመቹን በተመለከተ ለቤት መስሪያ በተሰጠው ገንዘብ “ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ መግዛቱን” የተከሳሽ እናት መመስከራቸውን ያስታወሰው ዐቃቤ ህግ፤ ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ ላይ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ መሰረት እንዲወስንለት ጠይቋል።
ሶስተኛ ተከሳሽ አብዲ አለማየሁን በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በራሱ የቅጣት ውሳኔ እንዲሰጥ ዐቃቤ ህግ ጥያቄ አቅርቧል። ፍርድ ቤቱ የሶስተኛ ተከሳሽን የቅጣት ማቅለያ ቢቀበለው ተቃውሞ እንደሌለውም ገልጿል። ለሶስቱም ተከሳሾች በመንግስት በኩል የተመደቡት ተከላካይ ጠበቃ “ተከሳሾች የቀድሞ ባህሪያቸው ታይቶ ማቅለያ ይያዝላቸው” ሲሉ የቅጣት ማቅለያ አስተያየት አቅርበዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት የቅጣት አስተያየቱን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 20፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ተከሳሾች ተጨማሪ የቅጣት ማቅለያ ካላቸው ከቀጠሮው ቀን በፊት በፍርድ ቤት ሬጅስትራር በኩል እንዲያቀርቡም ፍርድ ቤቱ አዝዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)