በሃሚድ አወል
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የቆጠራቸውን ምስክሮች ማቅረብ ባለመቻሉ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 8፤ 2013 ይጀመራል ተብሎ የነበረው የምስክር መስማት ሂደት ሳይካሄድ ቀረ። ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ለቆጠራቸው 16 ምስክሮች ጥበቃ ለማድረግ ጊዜ ስለሚያስፈልገው፤ ምስክሮቹን ማቅረብ አለመቻሉን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።
ዐቃቤ ህግ ‛‛በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርጎ በተቋማችን ሥር የወደቀውን የምስክሮች ደህንነት እና ጥበቃ ለማረጋገጥ ጊዜ ስለሚያስፈልግ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጥልን’’ ሲል የእነ እስክንድርን ጉዳይ ለሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3ኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ጥያቄውን አቅርቧል።
ለምስክሮች ጥበቃ ሳይደረግ ምስክሮችን መስማት በፍትህ ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ መዛባትን እና አሉታዊ ተጽዕኖን ያሳርፋል ያለው ዐቃቤ ህግ፤ ለምስክሮች ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ በጀት እንደሌለውና ሌሎች ተቋማትን ጠይቆ የተቋማቱን ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት ገልጿል። ‛‛ለምስክሮች ጥበቃ ለማድረግ ከዐቃቤ ህግ ውጭ ያሉ የሶስተኛ አካላትን ተሳትፎ ይጠይቃል’’ ሲልም ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥቷል።
የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ዐቃቤ ህግ ምስክሮችን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ቢያዝም፤ ዐቃቤ ህግ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አላከበረም ብለዋል። ስለሆነም ‛‛ዐቃቤ ህግ ያቀረባቸው ምክንያቶች በቂ ስላልሆኑ ክሱ ተቋርጦ ደንበኞቻችን በነፃ ይሰናበቱ’’ ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
አንድ ተከራካሪ ወገን ቀጠሮ ይቀየር ስላለ ብቻ ቀጠሮ አይለወጥም ያሉት ከተከሳሽ ጠበቆች አንዱ የሆኑት ቤተማርያም አለማየሁ ‛‛[የዐቃቤ ህግ] ጥያቄው ስነ ስርዓታዊ አይደለም። [ፍርድ ቤቱ] መዝገቡን እንዲያቋርጥልን እንጠይቃለን’’ ሲሉ ለችሎቱ አመልክተዋል። ከጠበቆች በተጨማሪ አራቱም ተከሳሾች ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን ማቅረብ አለመቻሉን በመጥቀስ፤ መዝገባቸው ተዘግቶ በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።
“በህወሓት ዘመን 10 ዓመት አሁን ደግሞ አመት፤ በድምሩ 11 ዓመታትን ታስሬያለሁ” ያሉት አንደኛ ተከሳሽ አቶ እስክንድር ነጋ፤ “በእስር ቤት ቆይታዬ ልጄን አጥቼዋለሁ” ሲሉ ዓመታትን እስር ቤት ውስጥ በማሳለፋቸው ልጃቸው ሊያውቃቸው እንዳልቻለ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። አስር ዓመታትን በእስር ቤት ያሳለፉት በሃሰተኛ ምስክሮች መሆኑን እና ይሄንንም መንግስት ራሱ ማመኑን የተናገሩት ተከሳሹ፤ አሁንም ተመሳሳይ ስህተት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ስንታየሁ ቸኮል በበኩላቸው፤ ክርክሩ የህግ ክርክር ሳይሆን የፖለቲካ ክርክር ነው ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። “ክሳችን የውሸት ነው። ምስክሮቹ የውሸት ናቸው። ዐቃቤ ህግ የሚያቀርበው [ማስረጃ] ውሸት ነው። ውሸት ሰልችቶናል። ፍርድ ቤቱስ ይኼን ውሸት ይታገሰዋል ወይ?” ሲሉ ጥያቄ አዘል አቤቱታቸውን ሰንዝረዋል።
የአቶ ስንታየሁ “ዐቃቤ ህግ በውሸት ስላሳሰረን እናመሰግናዋለን” የሚለው ገለጻቸው ግን ፍርድ ቤቱን እና ዐቃቤ ህግን አስቆጥቷል። “እንደተቋምም፤ እንደግለሰብም በየችሎቱ መዘለፍ የለብንም” ያለው ዐቃቤ ህግ፤ ችሎቱ “ዘለፋውን” በመዝገብ ላይ መዝግቦ ተከሳሹ ላይ የቅጣት ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቋል።
“በተከሳሾች በኩል ጉዳዩን ከህግ ይልቅ ፖለቲካዊ የማድረግ እና ዐቃቤ ህግን ጭራቅ አድርጎ የማቅረብ ሙከራዎች አግባብ አይደሉም” ሲልም ለፍርድ ቤቱ አቤት ብሏል። የችሎቱ ታዳሚዎች ተከሳሾችን እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር ሊያውቋቸው ይችላሉ ያለው ዐቃቤ ህግ፤ “ጀርባቸውን ግን አያውቁም” ሲል አክሏል።
“በተከሳሾች በኩል ጉዳዩን ከህግ ይልቅ ፖለቲካዊ የማድረግ እና ዐቃቤ ህግን ጭራቅ አድርጎ የማቅረብ ሙከራዎች አግባብ አይደሉም”
– የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከተናገረው የተወሰደ
ለዚህ የዐቃቤ ህግ አቤቱታ ከፍርድ ቤቱ ፍቃድ ሳያገኙ ምላሽ የሰጡት አንደኛ ተከሳሽ አቶ እስክንድር ነጋ ናቸው። አቶ ስንታየሁ የተናገሩት “የራሳቸው ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ሀሳብ ነው” ያሉት አቶ እስክንድር፤ ዐቃቤ ህግ የጠየቀው “የቅጣት ውሳኔ” አራቱም ተከሳሾች ላይ እንዲወሰን ጠይቀዋል።
ጠበቃ ቤተማርያም አለማየሁ በበኩላቸው “በክርክር ሂደቱ ወቅት የሚሰነዘሩ ትችቶች የማያስቀጡ ናቸው። አቶ ስንታየሁ የሰነዘሩት ዘለፋ ሳይሆን ትችት ነው” በማለት ዐቃቤ ህግ “ይቀጡልኝ” ማለቱ አግባብ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። “ዐቃቤ ህጉ ተከሳሾች ‘አደገኛ ናቸው’ ብለዋል” ያሉት ቤተማሪያም፤ “ከስንታየሁ ይልቅ ዐቃቤ ህጉ ተከሳሾችን ‘አደገኛ ናቸው’ በማለት ህገ መንግስቱን ጥሰዋል፤ ችሎቱንም አላከበሩም” በማለት ወቅሰዋል።
የግራ ቀኙን አስተያየት ያደመጠው ፍርድ ቤቱ “በክርክር መሃል አላስፈላጊ ንግግሮችን መወራወር በሁለቱም ተከራካሪዎች በኩል አለ” ብሏል። ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ወገኖች ነጻነት ተሰምቷቸው እንዲከራከሩ ፍላጎቱ መሆኑንም አስታውቋል። ችሎቱ ይህን ቢልም ተከሳሾች እና ጠበቆቻቸው‛‛ክሱ ይቋረጥ’’ በሚል ባነሱት መከራከሪያ ላይም ሆነ፤ ዐቃቤ ህግ በአቶ ስንታየሁ ቸኮል ላይ “የቅጣት ውሳኔ” እንዲተላለፍኝ በሚል ያቀረበው ጥያቄ ላይ ምንም አይነት አስተያየትም ሆነ መልስ ሳይሰጥ ቀርቷል።
የምስክሮች ደህንነት በተመለከተ ለአንድ አመት ክርክር መካሄዱን ያስታወሰው ፍርድ ቤቱ፤ “ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ምክንያት ቀጠሮ የሚያስቀይር ሆኖ አላገኘሁትም” በሚል የዐቃቤ ህግን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ ውድቅ አድርጓል። በዚህ ላይ ተመርኩዞም ዐቃቤ ህግ አሉኝ የሚላቸውን ምስክሮች ነገ ሐምሌ 9፤ 2013 እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 22፤ 2013 በዋለው ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ የቆጠራቸው ምስክሮች በዝግ ችሎት ከመጋረጃ ጀርባ እንዲመሰክሩ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም። ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ባስተላለፈው ውሳኔም የምስክር መስማት ሂደቱ ከዛሬ ሐምሌ 8 ጀምሮ ለአምስት ቀናት በግልጽ ችሎት እንዲከናወን ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)