በሃሚድ አወል
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ የቆጠራቸው ምስክሮች የመስማት ሂደትን በተመለከተ የስር ፍርድ ቤት የሰጠው ብይን ታግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ችሎቱ ትዕዛዙን የሰጠው ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 14፤ 2013 ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በላከው ባለ ሁለት ገጽ የእግድ ደብዳቤ ነው።
የእነ እስክንድር ነጋን ጉዳይ የሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ፤ 1ኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በነበረው ውሎው፤ ዐቃቤ ህግ ምስክሮቹን ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ሶስት ቀናት እንዲያሰማ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። “የምስክሮችን ደህንነት እና ጥበቃ ለማረጋገጥ ጊዜ ያስፈልገኛል” በሚል ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው ለችሎቱ ጥያቄ ሲያቀርብ የነበረው ዐቃቤ ህግ፤ ትዕዛዙን በመቃወም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከትላንት በስቲያ ሰኞ አቤቱታ አስገብቷል።
አቤቱታው የቀረበለት ሰበር ሰሚ ችሎት፤ የስር ፍርድ ቤት “የዐቃቤ ህግ ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ የወሰነበት አግባብነት፤ ከምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ዓላማና አዋጁን ለማስፈጸም ፍርድ ቤት ካለው ሚና አንፃር መጣራት ያለበት መሆኑ ታምኖበታል’’ ሲል ጉዳዩ ለችሎቱ እንዲቀርብ ውሳኔ ሰጥቷል። ዐቃቤ ህግ ይህኑን ውሳኔ ዛሬ ለተሰየመው የስር ፍርድ ቤት ችሎት አቅርቧል።
በውሳኔው መሰረትም፤ ከሰበር ሰሚ ችሎት ተለዋጭ ትዕዛዝ እስኪሰጥ ድረስ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች አሰማም ሂደትን በተመለከተ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 22 የሰጠው ብይን ታግዶ እንዲቆይ ታዝዟል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 22 በዋለው ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ በተከሳሾች ላይ የቆጠራቸውን ምስክሮች በሐምሌ 8፣ 9፣ 14፣ 15 እና 16 በግልጽ ችሎት እንዲያሰማ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።
ሰበር ሰሚ ችሎት ያስተላለፈው የዚህ ውሳኔ ግልባጭ ለተከሳሾች ደርሷቸው መልስ እና የመልስ መልስ ለመቀበል ለሐምሌ 26 ቀጠሮ መሰጠቱ ለስር ፍርድ ቤት በቀረበው ደብዳቤ ላይ ተገልጿል። የተከሳሽ ጠበቆች ግን ለከፍተኛው ፍርድ ቤት የቀረበው ይህ ደብዳቤ ማህተም እንዳልሰፈረበት በመጥቀስ፤ ሰነዱ “ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም” ሲሉ በዛሬው የችሎት ውሎ ተከራክረዋል።
ከተከሳሾች ጠበቆች አንዱ የሆኑት ቤተማርያም አለማየሁ “ዐቃቤ ህግ ያቀረበው የእግድ ደብዳቤ ተቀባይነት የሚኖረው ከሆነ ተከሳሾቹ በምን አግባብ ነው የሚቀጥሉት? ታስረው ነው ወይስ እንዴት ነው የሚሆነው?’’ ሲሉ ለችሎቱ የአካሄድ ጥያቄ አቅርበዋል። ሰበር ሰሚ ችሎት “ተከሳሾች በእስር ላይ እንዲቆዩ አላለም” ሲሉ ደብዳቤውን በማስረጃነት የጠቀሱት ጠበቃው፤ ደብዳቤው “ይህን ባላለበት ሁኔታ ተከሳሾች በእስር መቆየት የለባቸውም” በማለት እግዱ እስኪነሳ ተከሳሾች ከእስር እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
ሌላኛው የተከሳሽ ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ “ቀሪ የምስክር መስሚያ ሁለት ቀናትን ውድቅ በማድረግ መዝገቡ ተዘግቶ ተከሳሾች ከእስር ይፈቱ” ሲሉም የባልደረባቸውን ሀሳብ ደግፈዋል። የእግድ ደብዳቤው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሬጂስትራር ቲተር እንዳለው ዛሬ ረፋድ በነበረው የችሎት ውሎ ላይ ያስታወቀው ዐቃቤ ህግ፤ የደብዳቤውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ ማህተም አስመትቶ ማምጣት እንደሚችል ተናግሯል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ “የእግድ ደብዳቤው ክብ ማህተም የለውም። በትክክል ከዚያ [ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት] መጥቷል የሚለው መረጋገጥ አለበት’’ በማለት ዐቃቤ ህግ ዛሬውኑ ከሰዓት ማህተም አስመትቶ በጽህፈት ቤት በኩል እንዲያቀርብ ትዕዛዝ አስተላልፏል። በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሰረት በእግድ ደብዳቤው ላይ ማህተም ተመትቶ ለ1ኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች መቅረቡን ዐቃቤ ህግ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።
ማህተም የሰፈረበት ደብዳቤ በትክክልም ለችሎቱ መቅረቡን ጠበቃ ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። የከፍተኛው ፍርድ ቤት በጽህፈት ቤት በኩል በሰጠው ትዕዛዝም የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔን ለመጠባበቅ ለሐምሌ 29፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል ብለዋል። እስከ ቀጠሮው ቀን ድረስም ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ፍርድ ቤቱ መወሰኑንም ጠበቃው አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)