እናት ፓርቲ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለመፍታት በርካታ አካላትን ያካተተ ስብስብ እንዲቋቋም ጥሪ አቀረበ

እናት ፓርቲ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ “እየተባባሰ መጥቷል” ላለው ግጭት ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች እና ሌሎችንም በጎ ሀሳብ ያላቸውን አካላት ያካተተ ስብስብ እንዲቋቋም ጥሪ አቀረበ። ፓርቲው በክልሎች መካከል የሚነሱ የወሰን ግጭቶችን በዘላቂነት መፍትሔ እንዲያገኙ ለማስቻል፤ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ ከወዲሁ እንቅስቃሴ እንዲጀመርም አሳስቧል።

ተቃዋሚ ፓርቲው ይህን ያለው የሰሜን ኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 14፤ 2013 ባወጣው መግለጫ ነው። “ለሰላም የሚዘረጉ እጆች አይዛሉ” በሚል ርዕስ ስር የወጣው የፓርቲው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ አለ ላለው “የእርስ በእርስ ግጭት እንዲሁም ግድያ እና መፈናቀል” መፍትሔ ለማበጀት የተለያዩ አካላት ሊያደርጓቸውን የሚገቧቸውን ተግባራት በምክረ ሀሳብ ደረጃ የዘረዘረ ነው። 

በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ነው ያለውን ግጭት፣ ግድያ እና መፈናቀል “ዘር ተኮር እና እጅግ ፈታኝ” ሲል የጠራው እናት ፓርቲ፤ የፌደራል መንግስት እና ህወሓትን ጨምሮ በስምንት ምድብ ተከፋፈለው በመግለጫው ለቀረቡ አካላት ጥሪዎችን አቅርቧል። ፓርቲው ለችግሩ እልባት ለመጠት በሚል ለፌደራል መንግስቱ ያቀረባቸው ጥሪዎች እና ማሳሰቢያዎች ለሌሎቹ አካላት ከቀረበው ጋር ሲነጻጸር በርከት ብሎ ታይቷል። 

የሀገሪቱን የሰሜን ድንበር ለመጠበቅ በተመደበው የመከላከያ ሰራዊት ላይ “ዘግናኝ ተግባር ተፈጽሟል” ሲል በመግለጫው ያስታወሰው እናት ፓርቲ፤ “ይህንን ተግባር ለመመከት የተወሰደው የህግ ማስከበር ዘመቻ እና መንግስት ለሰብዓዊ እርዳታ የሰጠው ትኩረት” ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት አሳስቧል። በክልሎች መካከል የሚነሱ የወሰን ግጭቶችን በዘላቂነት መፍትሔ እንዲያገኙ ለማስቻል ሁሉን አቀፍ ውይይት መካሄድ እንደሚኖርበትም ፓርቲው ጠቁሟል። 

ይህ ውይይት እስከ ሕገ መንግስት ማሻሻያ ማድረግ ድረስ የሚሻገር መሆን እንዳለበትም የእናት ፓርቲ መግለጫ አስገንዝቧል። የሕገ መንግስት ማሻሻያው፤ “ጎሳ ተኮር” በሚል በፓርቲው የተገለጸውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ አካሄድ “በመሰረታዊ መልኩ ለመለወጥ የሚያስችል” እንደሆነም በመግለጫው ተብራርቷል።

እናት ፓርቲ ጥሪ ካቀረበላቸው አካላት አንዱ የሆነው “ህወሓት”፤ በሀገር ወዳድ ሽማግሌዎች በተደጋጋሚ የቀረቡለትን የማወያየት እና የማቀራረብ ሂደት “እንዳይሳካ” አድርጓል በማለት መግለጫው ኮንኗል። ድርጅቱ ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልል በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ላይ “ግፍ በመፈጸም ታሪካዊ ስህተት ሰርቷል” ሲል ወንጅሏል። ይህንን የህወሓት ተግባርም ፓርቲው “በእጅጉ እንደሚያወግዘው” አስታውቋል። 

“በትግራይ ያለ ማኅበረሰባችን ከጦርነት ተላቆ በሰላም ሠርቶ እንዲገባ እንዲሁም የተፈጠሩ ችግሮችን ከተቀረው የሀገራችን ሕዝብ በተለይም ከወንድሙ የአማራ ማኅበረሰብ ጋር በመመካከርና በውይይት ለችግሮች እልባት እንዲሰጥ፤ አሁንም በታሪክ ፊት ይቅርታን የሚያስገኝላችሁን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ በማቆም ዜጎቻችንን ከባሰ መከራና እንግልት እንድትታደጉ እናሳስባለን” ሲልም ፓርቲው “የህወሓት ቡድን” ሲል ለጠራው አካል ጥሪ አቅርቧል።

እናት ፓርቲ ለትግራይ እና አማራ ሕዝቦች በጋራ ባስተላለፈው መልዕክቱ፤ “ሁለቱ ማኅበረሰቦች ፖለቲከኞች በቆሰቆሱት እሳት መማገድ የለባችሁም” ሲል በአጽንኦት አሳስቧል። በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭትም “አንዱም አሸናፊ ሳይሆን ሁለቱንም ማኅበረሰቦች ብሎም ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ተሸናፊ የሚያደርግ የውርደት አቅጣጫ” መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም ጠቁሟል። 

“ለግጭቱ ሀገር በቀል መፍቻ መንገዶች የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ምሑራንን፣ ወጣቶችንና ሌሎችንም በጎ ሀሳብ ያላቸውን አካላት ያካተተ ስብስብ ተቋቁሞ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲያፈላልግ ስንል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን”

– እናት ፓርቲ

የትግራይ እና የአማራ ሕዝቦች “ነገሩን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨትና ግጭቱ ሕዝባዊ ቁመና እንዳይኖረው እንደ ሕዝብ ድርሻችሁ የጎላ ነው” ያለው የፓርቲው መግለጫ፤ በመሆኑም ሁለቱ ማኅበረሰቦች ይህን ታሪካዊ ሃላፊነት ለመወጣት ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማፈላለግ እንዲተጉ ጠይቋል። 

“ታሪክ እንደሚያስተምረን በመላው ዓለም የተከሰቱ ጦርነቶች ሁሉ መቋጫቸው ድርድርና ውይይት ስለሆነ ለግጭቱ ሀገር በቀል መፍቻ መንገዶች የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ምሑራንን፣ ወጣቶችንና ሌሎችንም በጎ ሀሳብ ያላቸውን አካላት ያካተተ ስብስብ ተቋቁሞ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲያፈላልግ” ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)