አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በአንድ ወር ውስጥ እንዲያካሄዱ የተቀመጠውን ቀነ ገደብ ተቃወሙ

በሃሚድ አወል

ሁለት ሀገር አቀፍ እና ሶስት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያካሄዱ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጣቸውን ቀነ ገደብ ተቃወሙ። ፓርቲዎቹ ተቃውሟቸውን ያሰሙት፤ ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ “አስቻይ ሁኔታዎች የሉም” በሚል ነው። 

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 26 ሀገር አቀፍ እና ክልላዊ ፓርቲዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያካሄዱ ቀነ ገደብ ያስቀመጠው ትላንት ረቡዕ ባወጣው ማስታወቂያ ነበር። የቦርዱ አመራሮች ዛሬ የካቲት 10፤ 2014 ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ፤ ጠቅላላ ጉባኤ የማካሄድ ጉዳይ ነው።

አሁን በሀገሪቱ ያለው “የጸጥታ ሁኔታ” ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ አያስችልም በሚል በዛሬው ስብሰባ ላይ ተቃውሟቸውን ካሰሙ ፓርቲዎች መካከል፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ይገኙበታል። ክልላዊ ፓርቲ የሆኑት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)፣ የአፋር ህዝብ ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አህዴፓ) እና የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ)  በስብሰባው ላይ ተመሳሳይ አቋም አራምደዋል። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ፤ ፓርቲያቸው በስፋት በሚንቀሳቀስበት የኦሮሚያ ክልል ያለውን ችግር በማስረዳት የክልሉ ጉዳይ “በተለየ ሁኔታ” እንዲታይ ጠይቀዋል። “[በኦሮሚያ] አሁን ስብሰባ ለማካሄድ ግዴታ መታጠቅ ያስፈልጋል። [መሳሪያ] ያልታጠቀ ኃይል በሰላም ስብሰባ ለማድረግ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ አስቸጋሪ ነው” ያሉት አቶ ሙላቱ፤ ፓርቲው ከአቅሙ በላይ ችግሮች እየገጠሙት እንደሆነ አብራርተዋል። 

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግን ወክለው በስብሰባው ላይ የተገኙት አቶ ጀቤሳ ጋቢሳም በተመሳሳይ ኦነግ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ እንደማይችል ለቦርዱ አመራሮች አስረድተዋል። አቶ ጀቤሳ “የፓርቲው ሊቀመንበር በቁም እስር ላይ እያሉ፤ የፓርቲው አባላት እና አመራሮች በእስር ቤት ውስጥ እያሉ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ ይቸግረናል” ብለዋል። 

እንደ ኦፌኮ ሁሉ የጸጥታ ስጋትን በምክንያትነት የጠቀሰው ትዴፓ፤ ቦርዱ ውሳኔውን በድጋሚ እንዲያጤነው ጠይቋል። አስራ ስድስት ወራትን ያስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተቀሰቀሰበት የትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰው ትዴፓን ወክለው በስብሰባው ላይ የተገኙት አቶ ተሻለ ንጉሴ፤ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ የሚችልበት ቁመና ላይ አለመሆኑን ተናግረዋል። 

አብዛኞቹ የፓርቲው አባላት በህወሓት ቁጥጥር ስር በሚገኘው የትግራይ ክልል እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ተሻለ፤ ከክልሉ ውጭ የሚገኙት የፓርቲው አባላትም ቢሆኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና በጦርነቱ ምክንያት “የስነ ልቦና ህክምና የሚጠይቅ የስነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል” ሲሉ ፓርቲው የገጠመውን ችግር አስረድተዋል። 

የትግራይ ክልልን በሚያዋስነው አፋር ክልል የሚንቀሳቀሰው የአፋር ህዝብ ፍትሃዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲም በጦርነቱ ምክንያት ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ እንደማይችል አስታውቋል። የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ መሐመድ አይዳሂስ “በአሁኑ ጊዜ ያለንበት ሁኔታ፤ ጉባኤ ማካሄድ ቀርቶ አስር ሰው ማሰባሰብ እንኳን የማንችልበት ነው” ሲሉ በአፋር ክልል ያለውን ሁኔታ አጽንኦት ሰጥተዋል።፡  

የህወሓት ኃይሎች በፈጸሙት “ወረራ” በክልሉ “ከፍተኛ የጸጥታ ችግር” መኖሩን የጠቆሙት አቶ መሐመድ፤ ምርጫ ቦርድ የፓርቲያቸውን “ችግር” ከግንዛቤ ውስጥ እንዲያስገባላቸው ጠይቀዋል። ሌላኛው ክልላዊ ፓርቲ የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ጋዴፓ) በበኩሉ፤ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በመላው ኢትዮጵያ ተግባራዊ ሲደረግ በቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ እንደሚያዳግተው ገልጿል።  

የጋዴፓ ሊቀመንበር አቶ ዳሮት ጉምአ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት አባላቶቻችን ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና እና ችግር ውስጥ ይገኛሉ። ይኼንን አባል ይዞ ጠቅላላ ጉባኤ መሰብሰብ አይቻልም፤ የማገገሚያ ጊዜ ስለሚያስፈልግ። ቦርዱ ይኼንን ታሳቢ ማድረግ አለበት” ብለዋል። በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ያለውን የጸጥታ ስጋት በተጨማሪነት ያነሱት አቶ ዳሮት፤ በእነዚህ ምክንያቶች ፓርቲያቸው በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ እንደሚቸገር አብራርተዋል።  

ከአምስቱ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች የቀረበውን ተቃውሞ እና የቀነ ገደብ ይራዘምልን ጥያቄን ያደመጡት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ፤ በጉዳዩ ላይ የቦርዱ አቋም ምን እንደሆነ ምላሽ ሰጥተዋል። ቦርዱ ውሳኔውን የወሰነው የፓርቲዎችን ሀሳብ መነሻ በማድረግ መሆኑን ተናግረዋል። ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ “እንደ ፓርቲ መደረግ የሚገባው አስፈላጊ ስራ ነው” ያሉት ብርቱካን፤ ፓርቲዎች ሞክረው ችግሮች ሲገጥሟቸው ለቦርዱ ቢያሳውቁ እንደሚሻል ገልጸዋል።

“የምታነሷቸው ችግሮች በእርግጥ ጠቅላላ ጉባኤን ከማድረግ የሚያስቆሙ ናቸው ወይ? የሚለውን ነገር እንዲሁ በግርድፉ ልናየው እና ልንወስደው አንችልም። እያንዳንዱ ፓርቲ ያደረገውን እና የሄደበትን ሂደት አሳይቶ፤ ተቸገርኩ ሲል ጉዳያችሁን አንድ በአንድ እንመለከታለን። ‘አቃተኝ’ የሚል ፓርቲ ‘ለምንድን ነው ስብሰባውን ማድረግ ያቃተው?’ የሚለውን ዝርዝሩን ሲያመጣ በተናጠል የምናየው ይሆናል” ብለዋል የቦርዱ ሰብሳቢ በምላሻቸው። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ የማካሄድ ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተነሳው ከአንድ አመት በፊት ነበር። ከምርጫ ህግ መሻሻል በኋላ በአዲስ መልክ የተመዘገቡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያደርጉ ምርጫ ቦርድ የመጀመሪያውን ውሳኔ ያሳለፈው በታህሳስ ወር 2013 ነበር። 

ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ግን በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ተቀባይነት አላገኘም። ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ መቃረቡን በምክንያትነት ያነሱት ፓርቲዎቹ፤ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ እንዲሆን ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበዋል።

ምርጫ ቦርድ፤ “ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ በምርጫ እንቅስቃሴ ዝግጅት ላይ ጫና ይፈጥርብናል” የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲዎቹን መከራከሪያ በጥር 2013 ባካሄደው ስብስባ ከመረመረ በኋላ ውሳኔ አሳልፏል። ቦርዱ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን ጥያቄ ከግምት ውስጥ ማስገባቱን ጠቅሶ፤ ፓርቲዎቹ ሀገራዊ ምርጫው በተጠናቀቀ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሄዱ ቀነ ገደብ ሰጥቶ ነበር። 

ነገር ግን ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ያካሄዱት ሁለት ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ብቻ ናቸው። ጠቅላላ ጉባኤውን ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጨረሻ በማካሄድ ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (አብአፓ) ነው። ከአብአፓ አንድ ወር ዘግይቶ በመስከረም ወር ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሄደው ሌላው ፓርቲ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ባልተካሄደባቸው ቦታዎች በመስከረም ወር ምርጫ አከናውኗል። ይህ ምርጫ በተካሄደ በወሩ በኢትዮጵያ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።  ምርጫ ቦርድ ባለፈው ህዳር ወር ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ውይይት፤ ሀገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ባለችበት ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ለማካሄድ እንደሚያዳግታቸው መረዳቱን ገልጾ ነበር።

ቦርዱ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባትም፤ ጠቅላላ ጉባኤ ያላደረጉ ሁሉም ፓርቲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተጠናቀቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ በዚያኑ ወር ውሳኔ አስተላልፏል። ለሶስት ወራት  ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ የተፈጻሚነት ጊዜው እንዲያጥር ተደርጎ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ የካቲት 8 መነሳቱ ይታወሳል።

ምርጫ ቦርዱ አዋጁ በተነሳ ማግስት ባወጣው ማስታወቂያ፤ የ26 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስም ዘርዝሮ ጠቅላላ ጉባኤያቸው እንዲያካሄዱ የአንድ ወር ቀነ ገደብ ሰጥቷል። የአንድ ወር ቀነ ገደብ ከተሰጣቸው ፓርቲዎች መካከል ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ይገኝበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)