በሃሚድ አወል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ በከተማይቱ ትራንስፖርት ለመጠበቅ የሚባክነውን የቆይታ ጊዜ ያቃልላሉ ያላቸውን 110 አውቶብሶች ግዢ መፈጸሙን አስታወቀ። ሃያ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገባቸው እነዚህ የከተማ አውቶብሶች በዚህ ዓመት መጨረሻ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ገልጿል።
የከተማ አስተዳደሩ የአውቶብሶቹን ግዢ ያከናወነው ከዓለም ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው። የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የትራንስፖርት ስርዓቶች ለማሻሻል ከአምስት ዓመት በፊት ይፋ ባደረገው ፕሮጀክት ውስጥ ለአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ አስተዳደር እና የመንገድ ደህንነት የሚውል 190.1 ሚሊዮን ዶላር መድቦ ነበር።
የዓለም ባንክ በሰጠው በዚህ ድጋፍ እንዲገዙ ለተወሰነው 110 አውቶብሶች ዓለም አቀፍ ጨረታ የወጣው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር። በዓለም ባንክ የሚደገፈው የትራንስፖርት ስርዓት ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ በኃይሉ ገብረየሱስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት የጨረታው ሂደት ብቻ ስምንት ወራት ፈጅቷል።
አስር ድርጅቶች ተሳታፊ በሆኑበት በዚህ ዓለም አቀፍ ጨረታ በስተመጨረሻ አሸናፊው የሆነው የቻይናው ዩቶንግ የአውቶብስ አምራች ድርጅት መሆኑን አስተባባሪው ገልጸዋል። ሰባ ሰዎችን የመጫን አቅም ያላቸው የ110 አውቶብሶች የጨረታ ሂደት ተጠናቅቆ፤ አሁን የቀረው የፊርማ ስነ ስርዓት ብቻ መሆኑን አቶ በኃይሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አካሉ አሰፋ አውቶብሶቹን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ወደ አምስት ወር ገደማ እንደሚፈጅ ይናገራሉ። “የተገጣጠሙ አውቶብሶች ናቸው የሚገቡት። እዚህ መጥተው ገና ጣጣ ያለባቸው አይደሉም። ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው” ሲሉ የከተማይቱ አስተዳደር በዚህ ዓመት መጨረሻ ስለሚረከባቸው አውቶብሶች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
በአውቶብስ ማምረት ስራ ከሃምሳ ዓመት በላይ እድሜ ያስቆጠረው ዩቶንግ ኩባንያ የሚያቀርባቸው አውቶብሶች፤ የአዲስ አበባ ከተማን ትራንስፖርት እንደሚያዘምኑት አቶ አካሉ ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአውቶብስ ኪራይ የሚያወጣውን ወጪ እንደሚቀንሱትም ምክትል የቢሮ ኃላፊ አክለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከጥቅምት 2013 ጀምሮ 560 አውቶብሶችን ተከራይቶ ወደ ስራ ማስገባቱ ይታወሳል። የከተማ አስተዳደሩ ከአንድ ዓመት በፊት ከተከራያቸው አውቶብሶች ውስጥ አሁን በስራ ላይ ያሉት 400 ገደማ አውቶብሶች መሆናቸውን አቶ አካሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
“ከተማ አስተዳደሩ በየወሩ ከፍተኛ ወጪ ነው እያወጣ ያለው። በቀን እስከ አራት ሺህ ብር ነው ለአንድ አውቶብስ [ኪራይ] የሚያወጣው” ያሉት ምክትል ኃላፊው፤ የአዳዲሶቹ አውቶብሶች ግዢ ይህን ወጪ በመቀነስ አኳያ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል። አዳዲሶቹ አውቶብሶች ተጠሪነቱ ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በሆነው አንበሳ አውቶብስ ስር እንደሚተዳደሩም አቶ አካሉ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ይህን ቢሉም፤ የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ግን አውቶብሶቹ በድርጅቱ ስር የሚተዳደሩ ስለመሆናቸው የሚያውቀው ነገር አለመኖሩን አስታውቋል። የድርጅቱ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ዳይሬክተር አቶ ምስክር ማንደፍሮ፤ ድርጅታቸው ስለ አውቶብሶቹ ግዢም ሆነ በአንበሳ አውቶብስ ስር ይሆናሉ ስለመባሉ ዝርዝር መረጃ እንደሌለው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የአንበሳ አውቶብስ በቀን በአማካኝ ከ630 እስከ 650 አውቶብሶችን በ125 መስመሮች የሚያሰማራ አገልግሎ ሰጪ ድርጅት ነው። ከጠዋቱ 12 እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅቱ በቀን 650 ሺህ ሰዎችን እንደሚያመላልስ ከድርጅቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአዲስ አበባ ከተማ 11,044 የብዙሃን ትራንስፖርት እና ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች እንዳሉ የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በየካቲት ወር መጀመሪያ ባቀረቡት የግማሽ ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርታቸው አመልክተዋል። ከእነዚህ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ውስጥ ከ10 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች በየቀኑ ወደ ስምሪት ገብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አስታውቀው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)