በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶች ቆመው የእርቅ ንግግር እንዲጀመር 35 ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጠየቁ

በሃሚድ አወል

ሰላሳ አምስት ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች “በአስቸኳይ ቆመው ሐቀኛ እና ሰላማዊ” የእርቅ ንግግሮች እንዲጀመሩ ጥሪ አቀረቡ። ድርጅቶቹ በትግራይ እና ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የተቋረጡ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ አገልግሎቶች “በአፋጣኝ እንዲጀመሩ” ጠይቀዋል።

የሲቪል ማህበራት ድርጅቶቹ ይህን ጥሪ ያቀረቡት በ“በይነ መረብ” አማካኝነት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የሰላም ጥሪውን ያቀረቡት በሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋትና በግጭት አፈታት እና ሰላም ግንባታ ስራ ላይ የተሰማሩ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ናቸው። 

ድርጅቶቹ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ያዘጋጁትን መግለጫ ጋዜጠኞች በተገኙበት ዛሬ ረፋድ ላይ ሊያቀርቡ የነበረው በአዲስ አበባው ኢንተርሌግዠሪ ሆቴል ነበር። ሆኖም ጋዜጣዊ መግለጫው እንዳይደረግ “ተከልክሏል” በመባሉ በተባለው ሰዓት ሳይካሄድ ቀርቷል። ሁነቱ የተስተጓጉለው “ማንነታቸውን ባልገለጹ የመንግስት አካል ነን ባሉ ግለሰቦች” መሆኑን የጋዜጣዊ መግለጫው አዘጋጆች ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ዛሬ ረፋድ ሊሰጥ የታሰበው ጋዜጣዊ መግለጫ በማን እንደተከለከለ መረጃው እንዳላቸው ከጋዜጠኞች ለሲቪል ማህበራቱ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። ጥያቄው ምላሽ የሰጡት፤ ጥሪውን ካቀረቡት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ዳይሬክተር ሌንሳ ቢዬና ናቸው።

ጋዜጣዊ መግለጫውን ማካሄድ እንደማይቻል የተናገሩት ግለሰቦች፤ ክልከላውን የወሰነው “ይሄኛው አካል ነው ብለው ለመግለጽ ፈቃደኞች አይደሉም” ሲሉ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። የሰላም ጥሪውን ያዘጋጁት ድርጅቶች ክልከላውን በተመለከተ “የተሟላ የሆነ ምላሽ” እንዲሰጣቸው አሁንም እንደሚጠይቁ ገልጸዋል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዛሬው መግለጫቸው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተሳተፉ ወገኖች ለሰላም ድርድር ፍላጎት ማሳየታቸው “ትልቅ ተስፋ” እንዲሰንቁ አድርጓቸው እንደነበር ጠቅሰዋል። በተፋላሚ ወገኖች መካከል አዲስ ጦርነት መቀስቀሱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

ከሰሜኑ ጦርነት ባሻገር በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ ግጭቶች “በርካታ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፉ እና የአካል ጉዳት እያስከተሉ ነው” ብለዋል። ግጭቶቹ የዜጎችን መብቶች ከመንፈጋቸውም ባሻገር “የአገርን ህልውናን የሚፈታተኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል” ያሉት ድርጅቶቹ፤ “እነዚህ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ካልተፈቱ አገራችን መወጣት የማትችልበት ቀውስ ውስጥ ትገባለች የሚል ስጋት አለን” ሲሉ የሚያሳስባቸውን ጉዳይ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ያሉ ፈተናዎች ይቀረፉ ዘንድ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶቹ “አስቸኳይ” ያሉትን “የሰላም ጥሪ” በዛሬው መግለጫቸው አቅርበዋል። ድርጅቶቹ በዚሁ ጥሪያቸው የእርቅ ንግግሮች እንዲጀመሩ የጠየቁ ሲሆን፤ ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የተቋረጡ አገልግሎቶችም “በአፋጣኝ” እንዲጀመሩ ጠይቀዋል። ጾታዊ ጥቃትን የፈጸሙ “ተዋጊ አካላትን” ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላት ላይ ምርምራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ድርጅቶቹ ጥሪ አቅርበዋል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ፤ ተፋላሚ አካላትና ደጋፊዎቻቸው “ከማንኛውም የጦርነት ፕሮፓጋንዳ እና የግጭት አባባሽ ንግግሮች እንዲሁም ድርጊቶች እንዲቆጠቡ” በዛሬው የሰላም ጥሪያቸው አሳስበዋል። የመገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና አክቲቪስቶች ድምጻቸውን ለሰላም እና ለእርቅ እንዲያውሉ ድርጅቶቹ ተማጽነዋል። 

የፌደራል እና የክልል መንግስታት በቁጥር አነስተኛ ለሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎች እና ግፉዓን “የልዩ ጥበቃ ስርዓት” እንዲዘረጉ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶቹ ጠይቀዋል። የሀገራዊ ምክክር ሒደቱ “ሁሉን አካታችና አሳታፊ፣ ግልጽ እንዲሁም የአገሪቱን የአጭርና የረዥም ጊዜ ችግሮች ለመፍታት” ያስችል ዘንድም “የብዙሃንን ይሁንታ ያገኘ አካሄድ እንዲከተል” ድርጅቶቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። 

“የተጀመረው የአገራዊ ምክክር ሒደት ሁሉን አካታችና አሳታፊ፣ ግልጽ እንዲሁም የአገሪቱን የአጭርና የረዥም ጊዜ ችግሮች ለመፍታት የብዙኃንን ይሁንታ ያገኘ አካሔድ እንዲከተል ጥሪ እናቀርባለን”

ሰላሳ አምስት አገር በቀል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ካቀረቡት የሰላም ጥሪ የተወሰደ  

በአንድ ጥላ ስር በመሰባሰብ የዛሬውን የሰላም ጥሪ ካቀረቡ 35 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል 13 ያህሉ በሴቶች እና ስርዓተ ጾታ ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ሴታዊት ንቅናቄ፤ የኢትዮጵያ ሴቶችና ህፃናት ማህበራት ህብረት እና የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ይገኙበታል። ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ውስጥ አስሩ በሰብዓዊ መብት እና ዴሞክራሲ ላይ የሚሰሩ ናቸው። ሃያ አራት ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ከአንድ ዓመት በፊት ጷጉሜ 5፤ 2013 ተመሳሳይ የሰላም ጥሪ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)