የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ “አስቸኳይ የሰላም ጥሪ” ሊያቀርቡ የነበሩ የሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች፤ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጡ ተከለከሉ። ድርጅቶቹ ዛሬ ማክሰኞ ጷጉሜ 1፤ 2014 ጋዜጣዊ መግለጫውን ሊሰጡ የነበረው በአዲስ አበባው ኢንተርሌግዠሪ ሆቴል ነበር።
ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጡ የነበሩት ድርጅቶች የተሰባሰቡት፤ የሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ስላሳሰባቸው መሆኑን ለመገናኛ ብዙሃን አስቀድመው በላኩት ደብዳቤ ገልጸው ነበር። ጋዜጣዊ መግለጫው ሊሰጥ በታቀደበት ሆቴል የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ እና ሲቪል የለበሱ የጸጥታ አካላት ነበሩ።
ሲቪል ከለበሱ የጸጥታ አካላት መካከል “ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ነው የመጣሁት” ያለ አንድ ግለሰብ፤ መግለጫውን ለመዘገብ በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞችን ለማናገር ሙከራ ሲያደርግ ተስተውሏል። ይኸው ግለሰብ ጋዜጠኞችን ለምን በሆቴሉ እንደተገኙ እና ከየትኛው መገናኛ ብዙሃን እንደመጡ ሲጠይቅ ነበር።
ግለሰቡ ጋዜጠኞችን ካነጋገራቸው በኋላ የሆቴሉ ሰራተኞች “የአሁኑ ስብሰባ አይኖርም” በማለት ለጋዜጠኞቹ አስታውቀዋል። መግለጫውን ሊሰጡ የነበሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ተወካዮች በተመሳሳይ ጋዜጣዊ መግለጫውን እንዳያደርጉ መከልከላቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ሆኖም ጋዜጣዊ መግለጫውን “ማን እንደከለከለው ሊነግሩን አልፈለጉም” ሲሉ የክልከላውን ውሳኔ ያስተላለፈው አካል ማን እንደሆነ አለማወቃቸውን አስረድተዋል። (በሃሚድ አወል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)