ከ30 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊነት በጎደለው እና አስከፊ በሆነ ሁኔታ ውስጥ በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች እንደሚገኙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ። የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት “ኢ-ሰብዓዊ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ላልተወሰነ ጊዜ በዘፈቀደ አስረው ያቆዩዋቸውን” በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በግዳጅ ወደ አገራቸው እየመለሱ መሆኑንም ገልጿል።
መቀመጫውን በለንደን ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ይህን ያስታወቀው ዛሬ አርብ ታህሳስ 7፤ 2015 ይፋ ባደረገው ሪፖርት ነው። ይህ ሪፖርት “አል-ኻርጅ” እና “አል-ሹማይሲ” በተባሉ ሁለት የተጨናነቁ የሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች፤ በአስከፊ ሁኔታ በእስር ላይ የቆዩ ኢትዮጵያውያን ወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት ያለፉበትን ስቃይ የሰነደ ነው። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ከሰኔ 2013 ዓ.ም እስከ ግንቦት 2014 ዓ.ም በግዳጅ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ የተደረጉ ናቸው።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመካከለኛው ምስራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ሔባ ሞራዬፍ፤ ሳዑዲ አረቢያ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በዘፈቀደ እያሰረች እና በግዳጅ ወደ አገራቸው እየመለሰች እንደምትገኝ አስታውሰዋል። ኢትዮጵያውያኑ ላልተወሰነ ጊዜ ታስረው የሚቆዩበትን ሁኔታ “አስከፊ” እና “ኢ-ሰብዓዊ” ሲሉ የጠሩት ዳይሬክተሯ፤ አያያዛቸው “የረዥም ጊዜ አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት” ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
“በአሁኑ ወቅት ከ30,000 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ ሁኔታ ታስረው ይገኛሉ” ያሉት ሔባ ሞራዬፍ፤ በግዳጅ ወደ አገራቸው የመመለስ ስጋት እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያኑ ላይ እነዚህን እርምጃዎች የምትወስደው፤ ሰነድ በሌላቸው ስደተኛ ሰራተኞች ላይ በጀመረችውን ዘመቻ አማካኝነት ነው።
“ካፋላ” ተብሎ በሚጠራው ስርዓት፤ ሰነድ የሌላቸው ስደተኛ ስራተኞች የመኖሪያ ፍቃዳቸውን ሕጋዊ የማድረግ እድል በአብዛኛው የላቸውም። ሰነድ ያላቸው ሰራተኞችም ቢሆኑ በደል ከሚፈጽሙባቸው ቀጣሪዎች ከተለያዩ፤ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃዳቸውን የማጣት ስጋት እንዳለባቸው የአምነስቲ ሪፖርት አመልክቷል።
ላልተወሰነ ጊዜ፣ በአስከፊ ሁኔታ በዘፈቀደ የመታሰር እጣ የገጠማቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤ እስራቸውን የሚሟገቱበት ዕድል እንደሌላቸው ሪፖርቱ ጠቁሟል። በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ በግዳጅ ወደ ኢትዮጵያ መመለስን ከመቀበል ውጪ አማራጭ እንደሌላቸው እንደሚሰማቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል። ስደተኞቹ በመረጃ ላይ ተመስርተው፣ በነጻነት ዕጣ ፈንታቸውን በፈቃደኝነት መወሰን ባለመቻላቸው፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱበት አግባብ “ግዳጅ ሊባል የሚችል ነው” ብሏል አምነስቲ።
የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋም ለሪፖርቱ ዝግጅት ካነጋገራቸው ውስጥ በሳዑዲ አረቢያ በእስር ላይ የነበሩ 11 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንደሚገኙበት ገልጿል። እነዚህ የቀድሞ ታሳሪዎች በሪያድ ከተማ የሚገኘው “አል-ኻርጅ” እስር ቤት የተጨናነቀ፣ ንጽህና የጎደለው እንደነበር ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያኑ ከጅዳ አጠገብ የሚገኘውን “አል-ሹማይሲ” እስር ቤት “ኢሰብዓዊ” ሲሉ ገልጸውታል።
ስደተኞቹ በእስር ቤት ቆይታቸው ወቅት “ስቅየት እና ድብደባ እንደገጠማቸው” መናገራቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል። ስድስት የቀድሞ እስረኞች በብረት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ መደብደባቸውን፤ በጥፊ እና በቦክስ መመታታቸውን እንዲሁም ከፍተኛ ሙቀት ባለበት ቆዳቸው እስኪቃጠል አስፓልት ላይ እንዲቆሙ መደረጋቸውን እንደተናገሩ አምነስቲ ገልጿል። ኢትዮጵያውያኑ ለስቅየት የዳረጋቸው፤ የእስር አያያዛቸውን በመቃወማቸው አሊያም የታመሙ ታሳሪዎች ህክምና እንዲያገኙ በመጠየቃቸው መሆኑ በሪፖርቱ ሰፍሯል።
በሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች የቆዩት እነዚህ ኢትዮጵያውያን በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ መኝታ አለመኖሩን ለዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቋሙ አጋልጠዋል። በእስር ቤቶቹ ውስጥ ለልጆች፣ ለነፍሰ ጡሮች እንዲሁም በጠና ለታመሙ ሰዎች በቂ የህክምና አገልግሎት እንደማይገኝም አክለዋል።
ሁሉም የቀድሞ እስረኞች ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደተናገሩት፤ እስር ቤቶቹ ቅማል እና የቆዳ በሽታ በሰፊው የተሰራጩባቸው ናቸው። የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት አማራጭ መከላከያ ባለማቅረባቸው፤ ስደተኞቹ የቅማል ስርጭቱን ለመከላከል የቆሻሻ መጣያ ፕላስቲክ ገዝተው እንደ ብርድልብስ ለመጠቀም እና የጭንቅላታቸውን ጸጉር ለማቃጠል መገደዳቸውን ተናግረዋል።
ከሳዑዲ አረቢያ እስር ቤት ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ እስረኞች ውስጥ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት፤ ሳንባ ነቀርሳን በመሳሰሉ የመተንፈሻ አካል ህመም እና ተላላፊ በሽታዎች የሚሰቃዩ እንደነበር አምነስቲ ሁለት የግብረ ሰናይ ሰራተኞችን ጠቅሶ በሪፖርቱ አስፍሯል።
አምነስቲ በዚሁ ሪፖርቱ ከሚያዝያ 2013 እስከ ግንቦት 2014 ባሉት ጊዜያት ብቻ፤ 10 ስደተኞች በአል-ኻርጅ እና አል-ሹማይሲ እስር ቤቶች መሞታቸውን ይፋ አድርጓል። በሪፖርቱ መሰረት አንድ በድብደባ በደረሰ ጉዳት የሞተ ስደተኛን ጨምሮ አብዛኞቹ ሕክምና በመከልከላቸው ሕይወታቸውን አጥተዋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ፤ በእስር ላይ የሞቱ 10 ስደተኞችን ጉዳይ የሳዑዲ አረቢያ ባለስልጣናት እንዲያጣሩ ጥሪ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)