የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ በመስከረም አበራ ላይ 14 የምርመራ ቀናት ፈቀደ

በሃሚድ አወል

ከትላንት በስቲያ ታህሳስ 4 በቁጥጥር ስር የዋለችው የ“ኢትዮ ንቃት” የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት መስከረም አበራ ላይ 14 የምርመራ ቀናት ተፈቀደ። የምርመራ ቀናቱን ዛሬ ሐሙስ የፈቀደው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው። 

የፌደራል ፖሊስ ዛሬ የምርመራ ቀናቱን በጠየቀበት ወቅት መስከረም በተጠረጠረችበት “የሽብር ወንጀል ድርጊት” መነሻነት “የተሰባሰቡ መረጃዎች መኖራቸውን” ለችሎቱ አስታውቋል። የምርመራ ስራውን በሰው እና በሰነድ ማስረጃ አጣርቶ ለሚመለከተው የፍትህ አካል ለመላክ 14 የምርመራ ቀናትን እንደሚያስፈልጉትም ገልጿል። 

በጽህፈት ቤት በኩል በሁለት ዳኞች የተሰየመው ችሎት፤ ፖሊስ “የሰው ምስክሮችን እንዲያሰባስብ” የጠየቀውን የምርመራ ቀናት ፈቅዷል። ሰነዶች ከመንግስት ተቋማት እንደሚመጡ የገለጸው ችሎቱ “የሰው ማስረጃዎችን አሰባስባችሁ አጠናቅቃችሁ እንድትቀርቡ” ሲል ከብይኑ ጋር ለፖሊስ  ማሳሰቢያ ሰጥቷል። ብይኑን ለተከራካሪዎች በቃል ያሰሙት ዳኛ “ስራዎች በጥራት እና በትጋት ሊሰሩ ይገባል። [የምርመራ ቀናት] የተሰጣችሁ የሰው ምስክር እንድታሰባስቡ ነው” ሲሉ ጠንከር ባሉ ቃላት ለፖሊስ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። 

ችሎት የመስከረም ጠበቆች የዋስትና ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል። ችሎቱ የዋስትና ጥያቄውን ያልተቀበለው፤ ፖሊስ ተጠርጣሪዋ በውጭ ብትሆን “ምርመራው ላይ የምትፈጥረው ተጽዕኖ ያለ መሆኑን” በመጥቀስ ያቀረበውን መከራከሪያ በመቀበል ነው።

የ37 ዓመቷ መስከረም አበራ ለእስር ስትዳረግ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከስድስት ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ግንቦት ላይ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር ውላ ነበር። በምታቀርባቸው የፖለቲካ ትንታኔዎች ይበልጥ የምትታወቀው መስከረም፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት በሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ 23 ቀናትን በእስር ላይ ካሳለፈች በኋላ በ30 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር የተለቀቀችው ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)