ራስ ገዝ አስተዳደር የሚኖራቸው የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች፤ ፕሬዝዳንቶቻቸውን በዓለም አቀፍ ውድድር ሊመርጡ ነው 

በአማኑኤል ይልቃል

ራስ ገዝ ሆነው የሚደራጁ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች፤ በዓለም አቀፍ ውድድር አዲስ ፕሬዝዳንቶችን እንደሚመርጡ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ይህ አሰራር በአገር ውስጥ ማስታወቂያ እና ውድድር የተወሰነውን የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች ቅጥር ሂደት በማስፋት፤ የውጭ ዜጎችም ጭምር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሪነት እንዲወዳደሩ እድል የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

ትምህርት ሚኒስቴር በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ 10 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ እቅድ ይዟል። በዚህ እቅድ ውስጥ ከተካተቱት ውስጥ፤ የባህርዳር፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና መቐለ ዩኒቨርስቲዎች ይገኙበታል። ከተቋቋመ ሰባ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ በተያዘው በጀት ዓመት የ“ራስ ገዝ” አስተዳደርን ተግባራዊ በማድረግ የመጀመሪያው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የዩኒቨርስቲዎች “ራስ ገዝ” መሆን፤ የአካዳሚ፣ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የሰው ሀብት አስተዳደራቸው ላይ ነጻነት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደር እና መሰረተ ልማት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰለሞን አብርሃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አስተዳደራዊ ነጻነቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የራሳቸውን አደረጃጀት እና መዋቅር የመዘርጋት ስልጣን እንደሚሰጣቸው የሚገልጹት ዶ/ር ሰለሞን፤ በዚህ መሰረት ዩኒቨርስቲዎቹ ከፍተኛ አመራሮቻቸውን ጨምሮ በመዋቅራቸው ውስጥ የሚያስፈልጓቸውን የአመራር እና የአስተዳደር አካላትን በራሳቸው መመደብ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ራስ ገዝ እንደሚሆኑ የሚጠበቁ ዩኒቨርስቲዎች፤ ፕሬዝዳንቶቻቸውን የሚመርጡበትን መስፈርት፣ የአገልግሎት ዘመን እና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚወስኑ ዝርዝር ድንጋጌዎች እንደሚኖራቸው ዋና ስራ አስፈጻሚው አስረድተዋል። እነዚህ ድንጋጌዎች፤ የዩኒቨርስቲዎቹን ራስ ገዝነት ለመወሰን በሚወጡ መተዳደሪያ ቻርተሮች እና ይህን ተከትሎ ተግባራዊ በሚደረጉ መመሪያዎች የሚካተቱ እንደሚሆኑም አብራርተዋል። 

አሁን ባለው አሰራር፤ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች የሚመረጡበት ሂደት የሚመራው የቀድሞው የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው “የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራር ምልመላ እና መረጣ” መመሪያ መሰረት ነው። በ2011 ዓ.ም የወጣው በዚህ መመሪያ መሰረት፤ የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶችን ለመቅጠር “የውስጥ እና የውጭ ግልጽ ማስታወቂያ” መውጣት አለበት።

ይህን አሰራር ሲከተሉ የቆዩት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፤ ፕሬዝዳንቶቻቸውን ለመቅጠር ማስታወቂያ ሲያወጡ የቆዩት “በሀገር ውስጥ” ብቻ እንደነበር ዶ/ር ሰለሞን አስታውሰዋል። ውድድሩ የሚካሄደው “በብሔራዊ ደረጃ” በመሆኑም በዕጩነት የሚቀርቡት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች መሆናቸውን አክለዋል። የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችን በዓለም አቀፍ ውድድር መቅጠር ያስፈለገው፤ ለውድድር የሚቀርቡት ግለሰቦች ተቋሞቹን “ለመለወጥ እና ለማሻገር” የሚያስችል ልምድ እስካላቸው ድረስ “ከየትኛውም ቦታ መጥተው ፕሬዝዳንት መሆን ይችላሉ” በሚል እሳቤ መሆኑን ዶ/ር ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

አዲሱ አሰራር የውጭ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦችንም ጭምር ዩኒቨርሲቲዎችን እንዲመሩ ዕድል እንደሚሰጥ የሚያነሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ “መስፈርቱን እስካሟላ ድረስ ማንም ሰው መጥቶ ተቋሙን የመምራት ስልጣን ሊኖረው ይችላል” ብለዋል። በተለያዩ አገራት በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚያስተምሩ እና በአመራርነት የሚሰሩ ዳያስፖራዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ቢመሩ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ “የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይችላሉ” ሲሉም አክለዋል። 

የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዝዳንቶቻቸውን ከሀገር ውስጥ ካሉ ምሁራን አወዳድረው ሲቀጥሩ ቢቆዩም፤ በሁለት ዩኒቨርስቲዎች ግን ለተወሰኑ ዓመታት የተለየ አሰራር ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት፤ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር መሀመድ በዳሶ ነበሩ። ይህንን የከፍተኛ ትምህርት ተቋም  የመምራት ኃላፊነት በመስከረም 1999 ዓ.ም የጀመሩት ፕሮፌሰር መሀመድ፤ በፕሬዝዳትነታቸው የቆዩት ለዘጠኝ ወራት ብቻ ነው።

የእርሳቸውን መልቀቅ ተከትሎ ዩኒቨርስቲውን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ጀርመናዊው ዶ/ር ሔርበርት አይሼለ ናቸው። ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ለሶስት ዓመታት ዩኒቨርስቲውን ከመሩ በኋላ ኃላፊነታቸውን ለደቡብ ኮርያዊው ፕሮፌሰር ጃንግ ግዩ ሊ አስረክበዋል። ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ለሰባት ዓመታት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ጃንግ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙን ለረጅም ዓመታት በመምራት አሁንም ድረስ ስማቸው የሚጠቀስ ነው። 

በሚስትሮች ምክር ቤት አማካኝነት በ1992 ዓ.ም በወጣ ደንብ የተቋቋመው መቐለ ዩኒቨርስቲም፤ የውጭ ዜጋን በፕሬዝዳትነት ቀጥሮ አሰርቷል። የመቐለ ዩኒቨርስቲን በፕሬዝዳንትነት ለሁለት ዓመታት ያህል የመሩት ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ዮአኺም ሔርዚግ፤ በጤናቸው ላይ አጋጠማቸው በተባለ እክል ምክንያት ከኃላፊነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው የለቀቁት በየካቲት 2005 ዓ.ም ነበር። 

እነዚህን የውጭ ዜጎች የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን እንዲመሩ የተደረገው “ሙከራ”፤ ያለ ውድድር የተካሄደ እንደነበር የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሰለሞን አስታውሰዋል። የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶችን አመራረጥ የሚወስነው መመሪያ፤ ለውድድር የሚቀርቡ ግለሰቦችን በተመለከተ ካስቀመጣቸው የውድድር መስፈርቶች ውስጥ አንዱ የትምህርት ደረጃቸው ነው። ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ ዕጩዎች ያላቸው የትምህርት ደረጃ “ዶክትሬት ዲግሪ ወይም የእዚህን ተመጣጣኝ የሚወክል ትምህርት እና ልምድ” መሆን እንዳለበት በመመሪያው ሰፍሯል። ሆኖም የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ግለሰቦች “በልዩ ሁኔታ” ሊመረጡ እንደሚችሉ በመመሪያው ተቀምጧል። 

የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ለመሆን በመስፈርትነት ከተቀመጡ ጉዳዮች ውስጥ ሌላኛው የስራ ልምድ ነው። መመሪያው “በከፍተኛ የትምህርት ወይም ከዚህ ውጪ ባለ መስክ በከፍተኛ አመራርነት የተረጋገጠ የስራ ልምድ” መኖርን በመስፈርትነት ጠቅሷል። በተጨማሪም ተወዳዳሪዎች ቢመረጡ ለዩኒቨርስቲው ያላቸውን ራዕይ የተመለከተ ስትራጂያዊ እቅድ በጽሁፍ የማቅረብ እና ከ200 ያላነሱ ሰዎች በተገኙበት ስለዚሁ ራዕይ ገለጻ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። 

በዩኒቨርስቲዎቹ የሚቋቋሙ የምልመላ እና ምርጫ ኮሚቴዎች፤ ለውድድር የሚቀርቡ ዕጩዎች በመመሪያው ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶችን ስለማሟላታቸው ግምገማ እንደሚያካሄዱ መመሪያው ይገልጻል። በግምገማው ውጤት መሰረትም ኮሚቴዎቹ አምስት ዕጩዎችን ለዩኒቨርስቲው ቦርድ ያቀርባሉ። የዩኒቨርስቲው ቦርድ ከሚቀርቡለት አምስት እጩዎች ውስጥ በቅደም ተከተል ሶስቱን መርጦ ለትምህርት ሚኒስቴር ካቀረበ በኋላ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አንዱን ዕጩ በፕሬዝዳንነት እንደሚሾም በመመሪያው ላይ በዝርዝር ተብራርቷል።

በትምህርት ሚኒስቴር ሹመት የሚያገኙ ፕሬዝዳንቶች የስራ ዘመናቸው ስድስት ዓመት ሲሆን ለአንድ ተጨማሪ ጊዜ ሊመረጡ ይችላሉ። ምክትል ፕሬዝዳንቶች በአንጻሩ ሹመታቸው የሚጸድቀው በዩኒቨርስቲዎች ቦርድ ሲሆን አራት ዓመት የስራ ዘመን ይኖራቸዋል። ዩኒቨርስቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ ያለ ትምህርት ሚኒስቴር ጣልቃ ገብነት ፕሬዝዳንቶቻቸውን በቦርድ ማጽደቅ እንደሚችሉ ዶ/ር ሰለሞን ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)