በአማኑኤል ይልቃል
በትግራይ ክልል የሚገኙ ነዳጅ አዳዮች ከጅቡቲ ነዳጅ እንዲጫንላቸው ውሳኔ ተላለፈ። ውሳኔውን ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 19፤ 2015 ያስተላለፈው የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ነው።
የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ተከትሎ ወደ ትግራይ ክልል ነዳጅ መጫን ተከልክሎ መቆየቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት የባለስልጣኑ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ በቀለች ኩማ፤ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከዛሬ ጀምሮ የኩባንያዎችን ትዕዛዝ እየተቀበለ ነዳጅ መጫን እንዲጀምር ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል። ይህንንም ተከትሎም ድርጅቱ፤ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ የሚፈልጉትን የነዳጅ መጠን እንዲያሳውቁ ጠይቋል ተብሏል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ሽሬ ከተማ ነዳጅ ማጓጓዝ እንዲጀምሩ ፈቃድ ሰጥቶ እንደነበር የተናገሩት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ፤ የዛሬው ውሳኔ ግን ሁሉንም የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሚመለከት መሆኑን አስታውቀዋል። ሽሬን ጨምሮ “በተወሰኑ” የትግራይ አከባቢዎች የሚገኙ የነዳጅ መሰረተ ልማቶች ያሉበትን ሁኔታ የሚያጠና ቡድን አሰማርቶ የነበረው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ ከዳሰሳው በኋላ በሽሬ የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ወደ ስራ መመለስ እንደሚችሉ ማረጋገጡንም አክለዋል።
ወደ ሽሬ ከተማ ነዳጅ እንዲጓጓዝ የተሰጠውን ፈቃድ ተከትሎ፤ ነዳጅ የጫነ አንድ ተሽከርካሪ ከትላንት በስቲያ ከጎንደር ተነስቶ ወደ ስፍራው ማምራቱን የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር የስራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ንብረትነቱ የብሔራዊ ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) ኩባንያ የሆነ አንድ ተሽከርካሪም፤ በተመሳሳይ ዛሬ ጠዋት ነዳጅ ጭኖ ወደ ሽሬ ከተማ ጉዞ መጀመሩን ጨምረው ገልጸዋል።
ከሽሬ ከተማ በተጨማሪ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎች የነዳጅ አቅርቦት እንዲያገኙ ዛሬ ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ፤ ወደ መቐለ እና ዛለምበሳ ከተሞች የሚጓጓዝ ነዳጅ ዛሬ ምሽት ከጅቡቲ እንደሚጫን አቶ ኤፍሬም ጠቁመዋል። ዛሬ ከጅቡቲ የሚጫነውን ነዳጅ ጨምሮ፤ ካለፉት ሁለት ቀናት ወዲህ ወደ ትግራይ ክልል እየገባ ያለው የነዳጅ መጠን 184 ሺህ ሊትር ገደማ መሆኑን የማህበሩ የስራ አመራር ቦርድ አባሉ አብራራተዋል።
በትግራይ ክልል ያሉ ነዳጅ ማደያዎች ስራ የሚጀምሩበትን ጊዜ በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኤፍሬም፤ “ነዳጅ እንደደረሳቸው ወዲያው ነው የሚጀምሩት” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የነዳጅ ማደያዎቹ ስራ መጀመር፤ በትግራይ ክልል ባለውን ከፍተኛ የነዳጅ ዋጋ ላይ ለውጥ ያስከትላል የሚል እምነት በዘርፉ ሰዎች ዘንድ አሳድሯል።
በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከመፈረሙ በፊት፤ በትግራይ ክልል አንድ ሊትር ነዳጅ “በኮንትሮባንድ” እስከ 800 መቶ ብር ድረስ ይሸጥ እንደነበር አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ አንድ ሊትር ነዳጅ እስከ 450 ብር እንደሚሸጥ የጠቆሙት አቶ ኤፍሬም፤ የዛሬው ውሳኔ “ዋጋውን ያረጋጋዋል” የሚል ግምታቸውን አጋርተዋል።
የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖስ ወርቁ፤ የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች በክልሉ ለሚገኙ ማደያዎች የሚያሰራጩት ነዳጅ ለተጠቃሚዎች የሚሸጠው፤ በሌላው የአገሪቱ ክፍል እየተተገበረ ባለው የመሸጫ ዋጋ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በትግራይ ክልል ውስጥ ነዳጅ ማደያ ያላቸው 14 የነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች እንዳሉ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” ሃሚድ አወል ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]