የመከላከያ ሰራዊት “ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘርበትን ጥቃት” ለመመከት “ዝግጁ” መሆኑን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት “ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዘርበትን ጥቃት” ለመመከት፤ ዝግጁ የሆነበት “ደረጃ” ላይ እንደሚገኝ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ። ኢትዮጵያ “በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት ጥረት እያደረገች ያለችበት ነው” ባሉት በዚህ ወቅት፤ የሀገሪቱ “ታሪካዊ ጠላቶች” የውስጥ ችግሮችን ለማባባስ “የቋመጡበት እና የቆረጡበት” መሆኑንም አስታውቀዋል። 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ይህን ያሉት፤ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ለ24ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን መኮንኖች ትላንት ቅዳሜ ጥር 25፤ 2016 ባስመረቀበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው። “አንድነት” የሚል ስያሜ የተሰጠው የዘንድሮ ተመራቂዎች ስብስብ፤ “የካበተ የውጊያ ልምድ እና ተሞክሮ ያላቸውን” መኮንኖች የያዘ መሆኑ ከዚህ ቀደም ከነበሩት “ልዩ” የሚያደርገው መሆኑ በስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

እነዚህ ተመራቂዎች ከተጨማሪ ስልጠና በኋላ ወደ መከላከያ ሰራዊቱ የሚመለሱበት የአሁኑ ወቅት፤ ኢትዮጵያ “ከቀይ ባህር ተገፍታ በመቆየቷ የደረሰባትን የኢኮኖሚና የጸጥታ ተግዳሮቶችን እና ስብራቶችን” ለመቅረፍ “እየሞከረች” ያለችበት መሆኑን ልብ ሊሉት እንደሚገባ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ አሳስበዋል። ይህ ሙከራ እንዳይሳካ፤ የኢትዮጵያ “ታሪካዊ ጠላቶች” የሀገሪቱን የውስጥ ችግር “ለማባባስ” “የቋመጡበት እና የቆረጡበት ጊዜ [ነው]” ሲሉም ተደምጠዋል። 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የኢትዮጵያን ዕድገት “በበጎ የማይመለከቱ” እና “ታሪካዊ ጠላቶቻችን” ሲሉ የጠሯቸውን ኃይሎች በስም ባይጠቅሱም፤ “አሁንም ኢትዮጵያን ለማዳከም የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ግልጽ [ሊሆንላቸው] ይገባል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። እነዚህ ኃይሎች “ከማንኛውም የኢትዮጵያ ጠላት ጋር ከመሰለፍ ወደ ኋላ የማይሉ የውስጥ ባንዳዎችን በማጠናከር” ኢትዮጵያን “ለማተራመስ ሲንቀሳቀሱ” መቆየታቸውንም በንግግራቸው አስታውሰዋል።

ኢትዮጵያ “የባህር ወደብን ለማልማት እና በቀይ ባህር ላይ የራሷን የጦር ሰፈር እንድትገነባ የሚያስችላትን” የመግባቢያ ስምምነት ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር መፈራረሟን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር በገባችበት ውዝግብ፤ ሌሎች ሀገራት ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል። የመግባቢያ ስምምነቱን “ሉዓላዊነቴን የሚጻረር” ነው በሚል አጥብቃ የምታወግዘው ሶማሊያ፤ ስምምነቱ ውድቅ እንዲደረግ ድጋፍ የማሰባሰብ ዘመቻ የጀመረችው በአባይ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር አሁንም በውዝግብ ውስጥ ካለችው ከግብጽ ነው። 

ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ፤ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ መሐሙድ የዛሬ ሁለት ሳምንት ወደ ካይሮ ተጉዘው ከግብጹ አቻቸው አብዱልፈታ አልሲሲ ጋር በአካል ተገናኝተው መክረዋል። ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ከውይይታቸው በኋላ በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ግብጽ የሶማሊያን ሉዓላዊ ግዛት የማስከበር እንስቃሴ እንደምትደግፍ አስታውቀዋል። ሶማሊያንም ሆነ ጸጥታዋን የሚያሰጋ ማንኛውንም አይነት ወገን ሀገራቸው እንደማትታገስም ፕሬዝዳንት አልሲሲ በወቅቱ አስጠንቅቀው ነበር። 

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በትላንቱ ንግግራቸው፤ ኢትዮጵያ “አንድ ሆና ቆማ ከውጪ የሚመጣ [ጥቃት] ካለ ለመመከት የሚያስችል ቁመና እንድትይዝ” ተመራቂ መኮንኖቹ “ኃላፊነት” እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በዚህ ረገድ መኮንኖቹ የሀገሪቱን “ጸጥታ የማስተካከል” ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። 

በመከላከያ ሰራዊት በኩል “ከየትኛውም አቅጣጫ የሚሰነዝርን ጥቃት” ለመመከት፤ “ዝግጁ የሆነበት” እና “እየሆነ ያለበት ደረጃ ላይ” እንደሚገኝ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በትላንቱ ንግግግራቸው አስታውቀዋል። ሰራዊቱ “ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ” ራሱን ማጠናከሩንም አክለዋል። የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሀገሪቱ ከዚህ ቀደም ያልነበራትን ራሺያ ሰራሽ “ሱ- 30” የተሰኘ ተዋጊ ጄት  እና  ከቱርክ የመጡ ስትራጄቴካዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) መረከቡን ከሶስት ሳምንት በፊት አስታውቆ ነበር።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በርክክብ ስነ ስርአቱ ላይ ለመንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ በወቅቱ ለዕይታ የበቁት “ሱ- 30” ተዋጊ ጄቶች “የመጀመሪያ ደራሾች” መሆናቸውን እና ተመሳሳይ አውሮፕላኖች “ቀስ እያሉ” እንደሚገቡ ገልጸዋል። የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው፤ አውሮፕላኖቹ የፌደራል መንግስት ተቋሙን ለመገንባት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት “የታዘዙ እና ውል የተገባባቸው” እንደሆነ አስረድተዋል። 

“እነኚህ አውሮፕላኖች በከፍተኛ ደረጃ የአየር ኃይልን የውጊያ አቅም የሚጨምሩ ናቸው። አንደኛ ይህ አውሮፕላን ሁለቱንም ውጊያ በአንድ ጊዜ መፈጸም የሚችል ነው። አየር በአየር ይዋጋል፤ በተመሳሳይ ጊዜ ከአየር ወደ ምድርም ይተኩሳል። ይሄ ቀላል አይደለም…ሁለተኛ አውሮፕላኑ የሚታጠቃቸው መሳሪያዎች፤ በረጅም ርቀት የጠላትን፣ የምድር ላይ፣ የሰማይ ላይ እና የባህር ላይ ኢላማዎችን መደምሰስ የሚችል አቅም ያለው [ነው]” ሲሉ ሌተናል ጄነራል ይልማ ስለ ሱ-30 “ብቃት” በወቅቱ አብራርተው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)