“በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ” የፖለቲካ ፓርቲ፤ ማመልከቻው በ15 ቀናት ውስጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያደርግ አዋጅ ነገ በፓርላማ ሊጸድቅ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

“በአመጽ እና በህገ-ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ” የፖለቲካ ፓርቲ፤ “በልዩ ሁኔታ” ለመመዝገብ ማመልከቻ ባቀረበ “በ15 የስራ ቀናት ውስጥ ምዝገባው እንዲፈጸም” የሚያደርግ አዋጅ በነገው ዕለት ለፓርላማ ቀርቦ ሊጸድቅ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በዚህ መልኩ የቀረበለትን ማመልከቻ ውድቅ የማድረግ አማራጭ በአዋጁ ባይሰጠውም፤ በፓርቲው ላይ ለሁለት ዓመታት “ክትትል እና ቁጥጥር” የማድረግ ስልጣንን ግን ያገኛል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩ ምዝገባ እና በዚህ ጉዳይ ላይ ምርጫ ቦርድ የሚኖረውን ስልጣን የሚወስኑ ድንጋጌዎች የተካተቱት፤ ይህንኑ በተመለከተ በ2011 ዓ.ም የጸደቀን አዋጅ ለማሻሻል በቀረበ የህግ ረቂቅ ላይ ነው። “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ” የሚያሻሽለው ይኸው የህግ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው ባለፈው አርብ ግንቦት 23፤ 2016 ነው። 

የአዋጅ ማሻሻያው የተዘጋጀው፤ “የፖለቲካ ቡድኖች በሰላማዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ መልሶ መመዝገብ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት” በማሰብ መሆኑ ከምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ መጠናቀቅ በኋላ የወጣው መግለጫ አመልክቶ ነበር። በሚኒስትሮች ምክር ቤት “በሙሉ ድምጽ” እንደጸደቀ የተነገረለት ይህ የአዋጅ ረቂቅ፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑም በወቅቱ ተገልጿል።

የተወካዮች ምክር ቤት ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራሩ ወጣ ባለ መልኩ፤ አዋጁ በተመራለት በሶስት ቀናት ጊዜ ውስጥ ለውይይት እንዲቀርብ ቀጠሮ ይዟል። ምክር ቤቱ ነገ ማክሰኞ ግንቦት 26፤ 2016 በሚኖረው መደበኛ ስብሰባው ከሚመለከታቸው ጉዳዮች አንዱ ይኸው የአዋጅ ማሻሻያ እንደሆነ፤ ፓርላማው ለመገናኛ ብዙሃን በሚልከው የስብሰባ አጀንዳ ማሳወቂያ መልዕክቱ ላይ አስፍሯል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ለፓርላማ አባላት የተሰራጨው የአዋጅ ረቂቅ፤ በነባሩ አዋጅ የተካተቱ ሶስት አንቀጾች ላይ ብቻ ማሻሻያ የሚያደርግ ነው። የመጀመሪያው አንቀጽ “የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ” የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ “በፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ ስለሚቀርብ ማመልከቻ” የሚያትት ነው። ሶስተኛው ማሻሻያ የተደረገበት አቀንጽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቶችን የሚዘረዝር ነው።

አዲሱ የህግ ረቂቅ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ ባሻሻለበት አንቀጹ፤ “አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር ውስጥ የተሳተፈ እንደሆነ እና ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ መንግስታዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱ በሚመለከተው የመንግስት አካል ከተረጋገጠ፣ የፖለቲካ ቡድኑ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሊመዘገብ ይችላል” ሲል ደንግጓል። አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ፤ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ “ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጻ ተግባር፣ ከሙስና ጋር ተያያዥነት ያላቸው የወንጀል ድርጊቶች እና የማጭበርበር ድርጊቶች የፈጸመ እንደሆነ” በቦርዱ ከምዝገባ እንደሚሰረዝ ሰፍሯል። 


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይህንን ድንጋጌ መሰረት በማድረግ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) “ህጋዊ ሰውነት” መሰረዙን በጥር 2013 አስታውቆ ነበር። ምርጫ ቦርድ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ “ፓርቲው ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሳተፉን ካረጋገጠ በኋላ” መሆኑን አስታውቋል። ቦርዱ የፓርቲውን ህጋዊ ሰውነት በሰረዘበት ውሳኔው፤ “የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉም” አግዶ ነበር። 

ህወሓት በግንቦት 2015 በጻፈው ደብዳቤ፤ “በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት በሰላማዊ እና ሕገ መንግስታዊ መንገድ እንዲፈታ በፓርቲው እና በፌደራል መንግስት መካከል የጋራ ውሳኔ ላይ ስለተደረሰ” እና “የተኩስ አቁም እርምጃ ስለተወሰደ” ቦርዱ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንዲያነሳ መጠየቁ ይታወሳል። ቦርዱ ለዚህ የህወሓት ጥያቄ በሰጠው ምላሽ ፓርቲው ያቀረበውን “የህጋዊ ሰውነት ጥያቄ የማስመለስ ጉዳይ በህግ የተደገፈ ሆኖ ባለመገኘቱ አለመቀበሉን” ይፋ አድርጎ ነበር።

ምርጫ ቦርድ ለዚህ በማስረጃነት የጠቀሰው፤ “ለህወሓት ህጋዊ ሰውነትን ለመመለስ የሚያስችሉ ድንጋጌዎች” በኢትዮጵያ የምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ “ተደንግገው አለመገኘታቸውን” ነው። ቦርዱ የጠቀሰውን አዋጅ የሚያሻሽለው አዲሱ የህግ ረቂቅ ግን “በተለያየ ምክንያት ከህጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማዕቀፍ ውጪ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖች”፤ የትኞቹን ሁኔታዎችን ሲያሟሉ መመዝገብ እንደሚችሉ ይዘረዝራል። 

የፖለቲካ ቡድኖቹ መመዝገብ የሚችሉት “በሰላማዊ መንገድ ለመቀሳቀስ” አሊያም “ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎት በሚያሳዩበት ጊዜ” መሆኑ በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ተጠቅሷል። “በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ለመመዝገብ የሚያመለክት ቡድን” ለምዝገባ ከሚያቀርበው ማመልከቻ በተጨማሪ ሌሎች ሰነዶች እና መረጃዎች ማካተት እንደሚኖርበት ማሻሻያው ይደነግጋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን የማከናወን ስልጣን በአዋጅ ለተሰጠው ምርጫ ቦርድ ከሚቀርቡት ሰነዶች ውስጥ፤ የፖለቲካ ፓርቲው “ፕሮግራም” እና “የመተዳደሪያ ደንብ” ይገኝበታል። የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች “በኃላፊነት ለመስራት መስማማታቸውን” የሚያስረዳ ሰነድም “በፊርማቸው ተረጋግጦ” መቅረብ እንዳለበት የአዋጅ ማሻሻያው ያዝዛል። የፖለቲካ ፓርቲው ኃላፊዎች ስም እና አድራሻም እንዲሁ በምዝገባ መስፈርትነት ተቀምጧል።

ምርጫ ቦርድ ምዝገባውን የሚያከናውነው፤ የፓለቲካ ቡድኖቹ “በሰላማዊ እና ህጋዊ አግባብ ለመንቀሳቀስ” መስማማታቸውን ከሚመለከተው የመንግስት ተቋም የሚሰጠውን ማረጋገጫ መነሻ በማድረግ እንደሆነም የአዋጅ ማሻሻያው ደንግጓል። እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟላ የፖለቲካ ፓርቲ፤ “ማመልከቻውን እና አባሪ ሰነዶችን ባቀረበ 15 የስራ ቀናት ውስጥ ቦርዱ ምዝገባውን መፈጸም እንዳለበት” የአዋጅ ማሻሻያው ያዝዛል።

ቦርዱ በዚህ መልኩ የቀረበለትን ማመልከቻ “ውድቅ የማድረግ አማራጭ” እንዳልተቀመጠለት በአዋጅ ማሻሻያ ማብራሪያው ላይ ተመልክቷል። ሆኖም “ቦርዱ አመልካቹን በቀጥታ ያለምንም ማጣራት የሚመዘግበው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ በቀጣይ ክትትል እና ቁጥጥር የሚያደርግበት ስርዓት” መደንገጉን ማብራሪያው ያስገነዝባል። በማብራሪያው የተጠቀሰው ይህ ድንጋጌ፤ ምርጫ ቦርድ “በልዩ ሁኔታ” በመዘገበው የፖለቲካ ፓርቲ ላይ “ለሁለት ዓመታት” “ልዩ ክትትል” እንደሚያደርግ ያስቀምጣል።

በዚህ መሰረት በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል፤ “የተመዘገበው ፓርቲ የፖለቲካ ሰነዶች ከአዋጅ ማሻሻያው ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑ” ማድረግ የሚለው ይገኝበታል። ምርጫ ቦርድ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲው “ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ” ወይም “ሌሎች መሰል የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ” ለፓርቲው አስፈላጊውን ትዕዛዝ እንደሚሰጥም በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ሰፍሯል።

የፖለቲካ ፓርቲው “በቀሪዎቹ ጊዜያት ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆኑ” ቦርዱ “ክትትል ያደርጋል፤ ግብረ መልስ ይሰጣል” ሲልም አዋጁ ያትታል። ፓርቲው “በተሰጠው ግብረ መልስ መሰረት መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች ካላስተካከለ እና ጉልህ የህግ ጥሰት የፈጸመ ከሆነ” ግን ቦርዱ “የተለየ አካሄድ ሳይከተል” የፓርቲውን ምዝገባ የመሰረዝ ስልጣን እንዳለው በአዋጅ ማሻሻያው ተደንግጓል።

“የፖለቲካ ፓርቲው በተሰጠው ግብረ መልስ መሰረት መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች ካላስተካከለ እና ጉልህ የህግ ጥሰት የፈጸመ ከሆነ፤ ቦርዱ የተለየ አካሄድ ሳይከተል የፓርቲውን ምዝገባ የመሰረዝ ስልጣን አለው”

– የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ማሻሻያ

በነገው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ አዋጅ፤ በፓርላማ አባላት ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንደሚመራ በስብሰባው አጀንዳ ማሳወቂያ ላይ ቀደም ብሎ ተገልጾ ነበር። ይሁንና ፓርላማው አዋጁን በነገው መደበኛ ስብሰባው መርምሮ እንድሚያጸድቀው፤ የተወካዮች ምክር ቤት ምሽቱን ለመገናኛ ብዙሃን በላከው “የተስተካከለ አጀንዳ” አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]