በተስፋለም ወልደየስ
የፌደራል መንግስት ለ2017 ከያዘው 971.2 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ 39 ቢሊዮን ብር ያህሉ ከመንግስት ግምጃ ቤት ወጪ ሆኖ ለመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እንዲከፋፈል ተመደበ። ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የተመደበላቸው ዩኒቨርሲቲዎች 13 እንደሆኑ ለፓርላማ በቀረበ የበጀት ረቂቅ ሰነድ ላይ ተመልክቷል።
ባለፈው ዓመት በአዋጅ የመጀመሪያው ራስ ገዝ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲሆን የተደረገው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ከመንግስት መደበኛ በጀት ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ተመድቦለታል። በክፍፍሉ ትልቁን ድርሻ ከያዘው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመከተል በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው፤ 1.8 ቢሊዮን ብር የተመደበለት ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ነው።
ከመንግስት ግምጃ ቤት 1.7 ቢሊዮን ብር የሚሰጠው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ ሶስተኛውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን የሚያገኝ ይሆናል። ጅማ እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች በአራተኛ እና በአምስተኛነት ይከተላሉ። በጦርነት ውስጥ በቆየው ትግራይ ክልል የሚገኘው መቐለ ዩኒቨርስቲ፤ 1.1 ቢሊዮን ብር ከፌደራል መንግስት እንደተመደበለት በረቂቅ የበጀት ሰነድ ላይ ሰፍሯል።
የፌደራል መንግስት በጀትን የሚያዘጋጀው የገንዘብ ሚኒስቴር፤ ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ባካሄደው የበጀት ስሚ መርሃ ግብር ወቅት፤ ዩኒቨርሲቲዎች “በተቀመጠላቸው ጣሪያ መሰረት” የበጀት እቅዳቸውን አስተካክለው እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። የ22 ዩኒቨርስቲዎች እቅድ በተገመገመበት በዚሁ መርሃ ግብር ላይ፤ የበጀት ዝግጅቱ ዋና ትኩረት “የሀገሪቱን ሀብት እና የመንግስትን በጀት በእቅድ ለተያዘለት አላማ ብቻ በአግባቡና በቁጠባ መጠቀም” መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረው ነበር።
የገንዘብ ሚኒስትሩ የፌደራል መንግስትን የ2017 በጀት ለማቅረብ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ፓርላማ በተገኙበት ወቅትም፤ የዩኒቨርሲቲዎች ጉዳይ ተነስቶ ነበር። አቶ አህመድ ለዩኒቨርሲቲዎች የሚመደብ ገንዘብን በተመለከተ ከአንድ የፓርላማ አባል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በዘንድሮው የበጀት ስሚ መርሃ ግብር “ከሌላው ጊዜ በተለየ” የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ እቅድ “በዝርዝር መታየቱን” አስረድተዋል።
“[ዩኒቨርሲቲዎች]በፊት በጥቅል አንድ ላይ ነበር በጀት ዴፌንስ የሚያካሄዱት። ዘንድሮ በጀት ዴፌንስ ያካሄድነው፤ መጀመሪያ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፕላን ሚኒስቴር አንድ ላይ ሆነን፤ በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ፕሮጅከቶች በሙሉ በሚገባ እንዲጠኑ ነው የተደረገው” ሲሉ አቶ አህመድ ሂደቱን ለፓርላማ አባላት አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ስር ብቻ “ከአንድ ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች” እንዳሉ የጠቀሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ “በአንድ በኩል አዳዲስ ዩኒቨርስቲ እንዳይከፈት ብለን ገድበናል። ግን ነባር ዩኒቨርስቲዎቹ ደግሞ በተለያየ ስም ፕሮጀክቶች ፈጥረዋል” ሲሉ በበጀት ላይ የተፈጠረውን ጫና አስረድተዋል። ፕሮጀክቶቹ በበጀት ተይዘው በፓርላማው ሲጸድቁ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
“ዘንድሮ ግን የጸደቁት ፕሮጀክቶችም ቢሆንም ‘rationalize መደረግ አለባቸው’ ተብሎ፤ በተለይ ከመማር እና ማስተማር ጋር፣ ከትምህርት ጥራት ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ፕሮጀክቶች፤ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር በመወያየት እንዲዘገዩ እያደረግን ነው። ስለዚህ በቀጣይ ይህንኑ ትኩረት የምናደርግ ይሆናል ማለት ነው” ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትሩ የመጪውን ጊዜ አካሄድ አመልክተዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር፤ በሚቀጥለው ዓመት ለዩኒቨርስቲዎች “ምንም አይነት አዳዲስ ፕሮጀክቶች” እንደማይኖር በግንቦት ወር ባካሄደው የበጀት ስሚ መርሃ ግብር ወቅት አስታውቆ ነበር።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በፌደራል መንግስት ስር እየተዳደሩ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ብዛት 46 ነው። ከእነዚህ ውስጥ “የመጀመሪያው ትውልድ” ተብለው የሚታወቁት እና በእድሜም አንጋፋ የሆኑት የአዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሐረማያ፣ አርባ ምንጭ፣ ባህርዳር፣ መቐለ እና ሀዋሳ እና ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)