በሙሉጌታ በላይ
በአማራ ክልል እና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተፈጻሚ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የ10 ወራት ቆይታ ወቅት፤ “በሀገር እና በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን” ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ ገለጸ። በእነዚህ ወራት የደረሱ ጉዳቶች፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “በማወጅ እና በማራዘም የፖለቲካ ችግሮቻችንን መፍታት እንደማይቻል በጉልህ ያሳዩ ናቸው” ብሏል ፓርቲው።
ተቃዋሚው ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ አዋጁ ተግባራዊ ሆኖ በቆየባቸው ጊዜያት ተፈጽመዋል ያላቸውን “የሰብአዊ መብት ጥሰቶች” ዘርዝሯል። በእነዚህ ጊዜያት ሰላማዊ ዜጎች “መገደላቸውን” እና “ለከባድ የአካል ጉዳት፣ ለአፈና፣ ለመፈናቀል” መዳረጋቸውን ፓርቲው ገልጿል። በአዋጁ ሳቢያ በርካቶች መታሰራቸውንም አስታውቋል።
ፓርቲው በዚሁ መግለጫው፤ ባለፉት 10 ወራት በበርካታ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ የሚያደርጉት እቅስቃሴ “እጅጉን ተገትቷል” ሲል ጠቁሟል። ይህ በተለይ ጎልቶ የሚስተዋለው በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች መሆኑንም አመልክቷል። በዚህም ሳቢያ በአካባቢዎቹ ያለው “ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ክፉኛ ተጎድተዋል” ሲልም አክሏል።

“ወትሮም በአስከፊ ድህነት፣ ስራ አጥነት፣ በድርቅ እና ረሃብ ምክንያት በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙት በርካታ የሀገራችን አካባቢዎች በተለይም የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች ለተወሳሰበ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የደህንነት እጦት ችግር ተዳርገዋል” ሲልም ፓርቲው በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል።
የተፈጻሚነት የጊዜ ወሰኑ ከአንድ ሳምንት በፊት በተጠናቀቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት፤ በበይነ መረብ (internet) እና ሌሎች የመገናኛ አውታሮች ላይ የተጣለው “ገደብ” ያስከተለው ችግርም በፓርቲው መግለጫ ተነስቷል። ገደቡ “በንግድ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማሳደሩን”፣ “ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ጫናዎችን ማስከተሉን” ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ አመልክቷል።
ተቃዋሚ ፓርቲው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከአራት ወራት በፊት በተራዘመበት ወቅት፤ “በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚያሳድረውን ጉዳት” በማንሳት ስጋቱን ገልጾ እንደነበር አስታውሷል። በአማራ ክልል የነበረውን የጸጥታ መደፍረስ ተከትሎ፤ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው ባለፈው ነሐሴ አጋማሽ ነበር። ፓርላማው ይህንኑ አዋጅ፤ ባለፈው ጥር ወር ለተጨማሪ አራት ወራት አራዝሞታል።
“ባለፉት አራት ወራት የሰላማዊ ዜጎች ሞት እና አካል ጉዳት፣ የዜጎች መፈናቀል፣ እስር እና እንግልት እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በግልጽ ተስተውለዋል”
– ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ
“ባለፉት አራት ወራት የሰላማዊ ዜጎች ሞት እና አካል ጉዳት፣ የዜጎች መፈናቀል፣ እስር እና እንግልት እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በግልጽ ተስተውለዋል። ይህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስከተለውን ተጨባጭ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ፍንትው አድርጎ አሳይቷል” ሲል ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ በዛሬ መግለጫው አስገንዝቧል።
“እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላም የሚሰፍነው” የፖለቲካ ልዩነቶችን “በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ብቻ ነው” ብሎ የሚያምነው ፓርቲው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “በማወጅ እና በማራዘም” የፖለቲካ ችግሮችን መፍታት እንደማይቻል ያለፉት 10 ወራት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሷል። ፓርቲው “ወስብስብ” ሲል የጠራውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ለመፍታት፤ መንግስት እና ታጣቂ ኃይሎች “ከጦርነት መለስ” ያሉ “የልዩነት መፍቻ መንገዶችን እንዲጠቀሙ” መክሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)