በኢትዮጵያ “ምንም አይነት ክትባት ያልወሰዱ” እና “ጀምረው ያቋረጡ” ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህጻናት እንዳሉ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

በናሆም አየለ

በኢትዮጵያ በተለያዩ የሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት “ምንም አይነት ክትባት ያልወሰዱ” እና “ጀምረው ያቋረጡ” ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህጻናት መኖራቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። እነዚህ ህጻናት ክትባት እንዲያገኙ፤ ሚኒስቴሩ ለአስር ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የክትባት ዘመቻ መጀመሩን ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 25፣ 2016 ይፋ አድርጓል።

በዘመቻው ዕድሜያቸው ከአምስት አመት በታች ለሆኑ ህጻናት፤ የሳምባ ምች፣ የኩፍኝ  እና የፖሊዮ ክትባት ለመስጠት መታቀዱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ተናግረዋል። ክትባቱ ከጤና ተቋማት በተጨማሪ በተንቀሳቃሽ ወይንም በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች እንደሚሰጥ ያመለከቱት ዶ/ር ደረጀ፤ ለዚህ ተብሎ በተዘጋጁ ቡድኖች ተደራሽ እንደሚደረግም ጠቁመዋል። 

ፎቶ፦ ጤና ሚኒስቴር

የአሁኑ የክትባት ዘመቻ በተለይ ትኩረት ያደረገው፤ በግጭት እና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች በሚኖሩ ህጻናት ላይ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታ ገልጸዋል። በዘመቻው አርብቶ አደር አካባቢ የሚኖሩ ህጻናትን  ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም አክለዋል።

“በጸጥታ ምክንያት አገልግሎት ያቋረጡ ጤና ኬላዎች የነበሩበት ቦታ ላይ ቅድሚያ እንሰጣለን። ብዙ ህጻናት ክትባት ያልወሰዱበት ስለሆነ፤ ለእነርሱ ቅድሚያ የሚሰጥ ይሆናል። በጤና ሴክተሩ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ራቅ ያሉ ወረዳዎች በተለይም አርብቶ አደር አካባቢዎችም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል” ሲሉ ዶ/ር ደረጀ አብራርተዋል። 

ከእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በተጨማሪ በመጠለያዎች ውስጥ ላሉ እና ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ ለሚገኙ ተፈናቃዮች፤ የክትባት አገልግሎቱን ለማዳረስ መታቀዱንም ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል። የኮሌራ፣ ኩፍኝ፣ ወባ እና ሌሎችም ወረርሽኞች ያሉባቸው ወረዳዎች፤ በተመሳሳይ መልኩ በክትባት ዘመቻው ቅድሚያ እንደሚሰጣቸውም ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)