በሙሉጌታ በላይ
ከስድስት ወራት በፊት “ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታፍነው” መወሰዳቸው የተነገረላቸው የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል አቶ ሀብታሙ በላይነህ፤ ትላንት ማክሰኞ ነሐሴ 7፤ 2016 መለቀቃቸውን ቤተሰቦቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የአቶ ሀብታሙን ጉዳይ ሲከታተል የቆየው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ የግለሰቡን መለቀቅ አረጋግጧል።
አቶ ሀብታሙ የአማራ ክልል ምክር ቤትን የተቀላቀሉት፤ በምዕራብ ጎጃም ዞን ከምትገኘው ቋሪት ወረዳ ተመርጠው ነው። በሰኔ 2013 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ፤ እንደ እርሳቸው ሁሉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) የወከሉ ሌሎች ሁለት ተወዳዳሪዎች ከቋሪት የምርጫ ክልል ተመርጠው የምክር ቤቱ አባል ሆነዋል።
አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞውን የአብን አመራር አቶ ክርስቲያን ታደለም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡት፤ ከቋሪት የምርጫ ክልል ነው። የአብን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ሀብታሙ፤ ደብዛቸው የጠፋው ከየካቲት 22፤ 2016 ጀምሮ እንደሆነ ለእርሳቸው ቅርበት ያላቸው አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በዕለቱ በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ አካባቢ “ሰው ላግኝ ብሎ ከቤት እንደወጣ አልተመለሰም” የሚሉት እኚሁ ምንጭ፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ለስድስት ወራት ያህል አቶ ሀብታሙ ያሉበት ሳይታወቅ መቆየቱን አስረድተዋል። ብሔራዊው የሰብአዊ መብቶች ተቋም ኢሰመኮ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ባወጣው አንድ መግለጫ፤ አቶ ሀብታሙ ከየካቲት ወር መጨረሻ ጀምሮ “የት እንዳሉ እንደማይታወቅ” በተመሳሳይ አስታውቆ ነበር።
ኢሰመኮ የግለሰቡን ጉዳይ ያካተተው “በግጭት አውድ ውስጥ እና ውጭ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን” በዘረዘረበት መግለጫ ነው። አቶ ሀብታሙ ከአዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ “ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ታፍነው የተወሰዱ” መሆኑን ኢሰመኮ በዚሁ መግለጫው አመልክቷል።
ግለሰቡ የደረሱበትን ለማወቅ፤ ኢሰመኮ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የአዲስ አበባ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎችን አነጋግሮ ነበር። ሆኖም አቶ ሀብታሙ በሁለቱም የፖሊስ ማቆያዎች ውስጥ እንደማይገኙ እንደተገለጸለት ኮሚሽኑ በግንቦቱ መግለጫው ጠቅሷል።
ከአማራ ክልል ምክር ቤት ተመርጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል ጭምር የሆኑት የአቶ ሀብታሙ ጉዳይ፤ ባለፈው ሰኔ መጨረሻ በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይም ተነስቶ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ላይ እንደ አቶ ሀብታሙ ሁሉ የአብን የምክር ቤት ተመራጭ የሆኑት አቶ አበባው ደሳለው፤ ጉዳዩን በጥያቄ መልክ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቅርበዋል።
አቶ ሀብታሙ ያሉበት ቦታ ያለመታወቁን በተመለከተ፤ እርሳቸውም ሆነ ቤተሰቦቻቸው ለተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎች አቤቱታ ማቅረባቸውን የፓርላማ አባሉ አስታውሰዋል። ከኃላፊዎቹ ምላሽ አለማግኘታቸውን የጠቀሱት አቶ አበባው፤ “ዛሬ ምላሽ ይሰጡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ በወቅቱ ተማጽነው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አቶ አበባው ላቀረቧቸው ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ቢሰጡም፤ የአቶ ሀብታሙን ጉዳይ ግን ዘለልውታል። ይህ የፓርላማ ስብሰባ ከተደረገ ከአንድ ወር ከ10 ቀን በኋላ አቶ ሀብታሙ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተቀላቅለዋል። የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ በአዲስ አበባ ከተማ አያት አካባቢ ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው የገቡት ትላንት ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ መሆኑን ቤተሰቦቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አቶ ሀብታሙ እስካሁን የት እንደቆዩ እና የነበሩበትን ሁኔታ በተመለከተ፤ በዚህ ጊዜ መናገር እንደማይፈልጉ ቤተሰቦቻቸው ጨምረው ገልጸዋል። በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ስራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር የሆኑት ሰላማዊት ግርማይ የአቶ ሀብታሙን መለቀቅ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢያረጋግጡም፤ ሆኖም ግለሰቡ የቆዩበት እና ሌሎችንም ዝርዝር ጉዳዮች በተመለከተ “ገና ቃላቸውን እንዳልሰጧቸው” አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)