ከሶማሌላንድ ጋር በተፈረመ የመግባቢያ ስምምነት ሳቢያ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለመፍታት የተጀመረው “የአንካራ ንግግር” ያለ ውጤት ተጠናቀቀ። በቱርክ አሸማጋይነት የተጀመረው ውይይት፤ በመጪው መስከረም ወር መጀመሪያ እንደሚቀጥል የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚመሯቸው ልዑካን ቡድኖች የተሳተፉበት ሁለተኛ ዙር ውይይት፤ ቱርክ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተፈጠረውን መቃቃር ለማስታረቅ የሞከረችበት ነው። ወደ ቱርክ ባቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ ውስጥ፤ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ተካተውበታል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የሶማሊያ አቻቸው አህመድ ሙዓሊም ፊቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት በተገናኙበት በዚህ ውይይት፤ “ሊታዩ የሚችሉ መሻሻሎች” የታዩበት እንደሆነ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ ምሽት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ሐካን ፊዳን “ልዩነቶችን ሊፈቱ” እና “ሁለቱን ወገኖች ወደፊት ሊያስማሙ የሚችሉ” መንገዶችን ለመፈለግ ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል።
ከመጀመሪያው ዙር የሁለቱ ሀገራት ውይይት አንጻር፤ ንግግር “የተደረገባቸው ጉዳዮች ብዛት እና ጥልቀት” በሁለተኛው ዙር “በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን” የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስረድተዋል። በአሁኑ ውይይት “በዝርዝር እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች” ላይ ትኩረት መደረጉንም ጠቁመዋል።
የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል “በተወሰኑ ዋና ዋና መርሆዎች” እና “በተመረጡ አቋሞች ረገድ“ መቀራረብ መታየቱን ጠቅሰዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ በበኩላቸው ቱርክ የጀመረችው ጥረት “ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ያላትን ህጋዊ ፍላጎት ያሳካል” የሚል እምነት እንዳላቸው በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ “ውጥረቱን ለማርገብ እና በአካባቢው ያለውን ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ“ ጥረት ማድረጓን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አስታውሰዋል። ኢትዮጵያ “ወቅታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት“ እና ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኑኘነት ወደ ነበረበት ለመመለስ “ቀጣይ ውይይት ለማድረግ” ዝግጁ መሆኗንም አስታውቀዋል።
“ሶማሊያ ሉዓላዊነቷን፣ የግዛት ምሉዕነቷን እና አንድነቷን ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነች” ያሉት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ “የተጀመረው ጥረት ወደ መጨረሻ መፍትሔ ይመራል“ የሚል ተስፋቸው በጋዜጣዊ መግለጫው አጋርተዋል። ሶማሊያ “ለሁሉም ወገኖች የሚጠቅም ሰላማዊ መፍትሔ ላይ መድረስ እንደምትፈልግም” አህመድ ሙዓሊም ፊቅ አስረድተዋል።
ሁለተኛው ዙር ውይይት የተካሔደው የቱርክ ፕሬዝደንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶጋን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼይክ ሙሐሙድ ጋር በስልክ ካደረጓቸው ንግግሮች በኋላ ነው። ፕሬዝደንቱ ከሶማሊያው አቻቸው ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር ከሁለተኛው ዙር ውይይት ተጨባጭ ውጤት እንደሚጠብቁ ገልጸው ነበር።
ትላንት ሰኞ ነሐሴ 6፤ 2016 የተጀመረው እና በዛሬው ዕለት የተጠናቀቀው ሁለተኛው ዙር “የአንካራ ንግግር” የተካሄደው፤ የቱርክ ፕሬዝዳንት ረቺብ ጣይብ ኤርዶኻን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሙሐሙድ ጋር በስልክ ካደረጓቸው ውይይቶች በኋላ ነው። ፕሬዝዳንቱ ከሶማሊያው አቻቸው ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር፤ ከሁለተኛው ዙር ውይይት ተጨባጭ ውጤት እንደሚጠብቁ ገልጸው ነበር።
ቱርክ “የሶማሊያን የግዛት አንድነት እና ፖለቲካዊ ሉዓላዊነት አክብራ፤ በሶማሊያ በኩል የባህር በር ማግኘት የምትችልበት” ምክረ ሐሳብ ማቅረቧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተናግረው ነበር። ሚኒስትሩ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው፤ “የጋራ እና ገንቢ መፍትሔ” ላይ ይደረሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። የሁለቱ ሀገራት ሶስተኛ ዙር ድርድር ከአንድ ወር ገደማ በኋላ መስከረም 7፤ 2017 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቀጠሮ መያዙንም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)