በቤርሳቤህ ገብረ
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ነገ ሐሙስ ነሐሴ 9፤ 2016 በሚያካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፤ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ምክትላቸው ምትክ አዲስ አመራሮችን ሊሾም ነው። ልሉን እንዲመሩ በዕጩነት የቀረቡት፤ ላለፉት ስምንት ዓመታት በፌደራል የሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ወ/ሮ አለሚቱ ኦሞድ ናቸው።
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት የነገውን አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው፤ መደበኛ ጉባኤውን ካካሄደ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው። የክልሉ ምክር ቤት ሐምሌ 19 ባደረገው ጉባኤ፤ በጋምቤላ ክልል መንግስት ካቢኔ የተደረገውን “የአመራር ሽግሽግ” አጽድቆ ነበር።
ምክር ቤቱ በነገው አስቸኳይ ስብሰባው፤ ክልሉን በርዕሰ መስተዳድርነት እና በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት የሚመሩ ተሿሚዎችን ሹመት እንደሚያጸድቅ የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ባንቺአየሁ ድንገታ ለ“ኢትዮጵያ አንሳይደር” ተናግረዋል። በነገው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ስልጣናቸውን በይፋ ያስረክባሉ ተብለው የሚጠበቁት አቶ ኡሞድ ኡጁሉ፤ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት በህዳር 2011 ዓ.ም ነበር።
አቶ ኡሞድ ከዚህ ሹመታቸው አስቀድሞ የጋምቤላ ክልል የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል። በሰኔ 2013 ዓ.ም የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ፤ የጋምቤላ ክልል መንግስት ምስረታውን ሲያከናውን፤ አቶ ኡሞድ ለሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በቆዩበት የርዕሰ መስተዳድር ስልጣናቸው እንዲቀጥሉ ተደርጓል።
የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት የአቶ ኡሞድን ሹመት በመስከረም 2014 ዓ.ም ባጸደቀበት ወቅት፤ ርዕሰ መስተዳድሩ ለቀጣዩ አምስት ዓመታት ክልሉን እንደሚመሩ ተገልጾ ነበር። አቶ ኡሞድ የስልጣን ጊዜያቸውን ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ገደማ ቢቀራቸውም፤ እርሳቸው እና ምክትላቸው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ውሳኔ መተላለፉን የጋምቤላ ክልል ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ውሳኔውን በተመለከተ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኡሞድ፤ የክልል ምክር ቤት “ጉባኤ አልተደረገም። ርዕሰ መስተዳድር የሚነሳው በጉባኤ ነው። ግን አስካሁን ስራ አየሰራሁ ነው። ስብሰባ አየመራሁ ነው። ነገ ምን እንደሚፈጠር፤ በዚህ ሰዓት አይገለጽም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በታደሙበት መርሃ ግብር ላይ ተሳታፊ ነበሩ። የሀገር መከላከያ ሰራዊት ባዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር ላይ የሌሎች ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች እና ሚኒስትሮችም ተገኝተዋል።
አቶ ኡሞድ ከስልጣን ስለመነሳታቸው ማረጋገጫ ባይሰጡም፤ በነገው የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት እርሳቸውን በመተካት ሹመታቸው ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው ወ/ሮ አለሚቱ ግን ውሳኔው የደረሳቸው ሰኞ ዕለት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። “የፌደራል መንግስት አሳይመንቱን ሰጥቶናል። እሱ ነገ ይፋ ይሆናል። ከትላንት ወዲያ አሳይመንት ተሰጥቶን፤ ዛሬ ወደዚህ መጥተናል” ሲሉም በአሁኑ ወቅት ጋምቤላ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።
ላለፉት 30 ዓመታት በመንግስት ስራ ላይ የቆዩት ወ/ሮ አለሚቱ፤ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ በክልል እና በፌደራል መስሪያ ቤቶች በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ተመድበው ሰርተዋል። አዲሷ ተሿሚ፤ በጋምቤላ ክልል ምክር ቤት በምክትል አፈ ጉባኤነት ለ10 ወራት፣ በክልሉ የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ደግሞ ለስድስት ዓመታት አገልግለዋል።
ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ፌደራል መንግስት መስሪያ ቤት የተዘዋወሩት ወ/ሮ አለሚቱ፤ በቀድሞ የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታነት ለስድስት ዓመታት ሰርተዋል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የነበራቸው የኃላፊነት ድርሻ፤ የህጻናት ዘርፍን መምራት ነበር።
ወ/ሮ አለሚቱ ከጥቅምት 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁኑ ሹመታቸው ድረስ በተመሳሳይ የኃላፊነት ደረጃ ሲሰሩ የቆዩት፤ በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው። በሚኒስቴሩ የሴቶች እና የህጻናት ዘርፍን አራት አመት ለሚጠጋ ጊዜ የመሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ወደ ትውልድ ቦታቸው ጋምቤላ በመመለስ ክልሉን የመምራት ኃላፊነት ለመረከብ አንድ ቀን ብቻ ቀርቷቸዋል።
አዲሲቷ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ በሰው ኃይል አስተዳደር ዲፕሎማ፣ በኮሚኒቲ ዴቨሎፕመት ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው። የእርሳቸው ምክትል በመሆን በነገው የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ሹመታቸው ይጸድቃል ተብሎ የሚጠበቀው፤ ዶ/ር ጋትሉክ ሮውን ናቸው። ዶ/ር ጋትሉክ፤ ላለፉት ስድስት ዓመታት በዚሁ የኃላፊነት ቦታ ላይ የቆዩትን አቶ ተንኳት ጆክን ይተካሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)