የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዲስ ፕሬዝዳንት ተሾመለት

በቤርሳቤህ ገብረ

በባንክ ኢንዱስትሪው ከ20 ዓመታት በላይ ያገለገሉት ዶ/ር እመቤት መለሰ፤ መንግስታዊውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ ተሾሙ። ዶ/ር እመቤት የፖሊሲ ባንክ የሆነውን የፋይናንስ ተቋም እንዲመሩ ከመሾማቸው አስቀድሞ፤ ላለፉት አራት ወራት የንብ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ሰርተዋል።

አዲሷ ተሿሚ ልማት ባንክን የመምራት ኃላፊነታቸውን የሚረከቡት ከቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ ጥቅምት 1፤ 2017 ጀምሮ መሆኑ ተገልጿል። ይህንኑ የሚገልጽ እና በገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ የተፈረመ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በዛሬው ዕለት መድረሱን አንድ የባንኩ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

ባንኩ ይህንኑ ለተቋሙ ማኔጅመንት አባላት እና ሰራተኞች በኢሜይል እና በውስጥ ማስታወቂያ ይፋ ማድረጉንም ኃላፊው አስረድተዋል። የሹመት ደብዳቤው ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተጨማሪ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በግልባጭ ተልኳል። 

የ116 ዓመት ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፤ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ልማት ውጤታማ ለሆኑ ፕሮጀክቶች የኢንቨስትመንት እና የአጭር ጊዜ ብድርን የመስጠት ኃላፊነት የተጣለበት ነው። ባንኩ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ምንጭ ለልማት የሚውል ገንዘብ ማሰባሰብ፣ የአደራ ገንዘብ ማስተዳደር፣ የአክሲዮን ድርሻ በመያዝ በኢንቨስትመንት የመሳተፍ፣ ቦንድ የማውጣት እና የመሸጥ ተጨማሪ ኃላፊነቶችም በተቋቋመበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ተሰጥቶታል። 

ባንኩ እስካለፈው ጷጉሜ ወር መጀመሪያ ድረስ ሲመራ የቆየው፤ በቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ነበር። ዶ/ር ዮሐንስ ባንኩን ለአራት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ካገለገሉ በኋላ “በግል ምክንያት” ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ፤ የፋይናንስ ተቋሙ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ተሰይሞለታል። 

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የስራ አመራር ቦርድ ባንኩን በጊዜያዊነት እንዲመሩ የመደባቸው፤ የዶ/ር ዮሐንስ ምክትል የነበሩት አቶ ጌታቸው ዋቄን ነው። በመጪው ሳምንት ከእርሳቸው ኃላፊነቱን የሚረከቡት ዶ/ር እመቤት፤ ረጅሙን የስራ ጊዜያቸውን ያሳለፉት በመንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ነው። 

ዶ/ር እመቤት ወደ ንብ ባንክ ከማምራታቸው በፊት፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስትራቴጂ ፕላኒንግ እና ትራንስፎርሜሽን ፕሮጀክት ቢሮን ለሁለት ዓመት በምክትል ፕሬዝዳንትነት መርተዋል። ዶ/ር እመቤት ከዚህ አስቀድሞ፤ በባንኩ የብድር ትንተና እና በኮርፖሬት ጥራት ማረጋገጥ ተመሳሳይ የኃላፊነት ደረጃ በመያዝ አገልግለዋል።

አዲሷ የልማት ባንክ ፕሬዝዳንት፤ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአካውንቲንግ እንዲሁም በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል። ዶ/ር እመቤት ከዚሁ ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ ሊደርሺፕ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ይዘዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)