አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአማራ ክልል እየተካሄደ ነው ያለውን “የዘፈቀደ የጅምላ እስር” በአፋጣኝ እንዲቆም ጠየቀ 

የክልሉ መንግስት በበኩሉ በሰሞኑ “የህግ ማስከበር” እርምጃ፤ በህግ ተጠያቂ የሚደረጉ “በርካታ ኃይሎች አሉ” ብሏል

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት፤ በአማራ ክልል እየተፈጸመ የሚገኘውን “የዘፈቀደ የጅምላ እስር” በአፋጣኝ እንዲያቆሙ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ። በክልሉ ባሉ ትልልቅ ከተሞች የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ እያካሄዱት ባለው ዘመቻ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸውንም ተቋሙ አስታውቋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ትላንት ማክሰኞ ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ በሰሞኑ ዘመቻ ለእስራት ከተዳረጉት ሰዎች መካከል በክልሉ ባሉ የፌደራል ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስተምሩ ምሁራን እንደሚገኙበት አመልክቷል። የዓይን እማኞች ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደተናገሩት፤ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ሲቪል ሰዎች የታሰሩት ባለስልጣናት ይዘው የመጡትን “የስም ዝርዝር” መሰረት በማድረግ ነው። 

ሆኖም እነዚህ ባለስልጣናት የብርበራም ሆነ የእስር ትዕዛዝ እንዳላቀረቡ ድርጅቱ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ በትላንቱ መግለጫው አስፍሯል። የተወሰኑት እስራት የተከናወኑት በምሽት እንደነበር እማኞቹ መግለጻቸውንም ድርጅቱ አክሏል። በእነዚህ እስራት ከፖሊስ አባላት ሌላ ወታደሮች ጭምር መሳተፋቸውንም የዓይን እማኞቹን ዋቢ አድርጎ ድርጅቱ ገልጿል።     

በዚህ መልኩ ከታሰሩት ውስጥ አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት እና በሌሎችም ህጎች በተደነገገው መሰረት “በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን” በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዋና ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ ተናግረዋል። ዋና ዳይሬክትሩ በአማራ ክልል እየተፈጸመ የሚገኘው “የዘፈቀደ የጅምላ እስር”፤ የኢትዮጵያ መንግስት “በህግ መገዛትን ሙሉ ለሙሉ ቸል ለማለቱ ተጨማሪ ማሳያ ነው” ሲሉ እርምጃውን ተችተዋል። 

ቻጉታህ የመንግስት ባለስልጣናት “የዘፈቀደ እስርን” እንደ “መጨቆኚያ መሳሪያ” መጠቀማቸውን ሊያቆሙ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። “የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እነዚህን የዘፈቀደ እስራት በአፋጣኝ ማቆም አለባቸው። በእስር ላይ ያሉ ሰዎች፤ ህግን በተከተለ መልኩ፣ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ወንጀሎች ክስ ሊመሰረትባቸው አሊያም ያለምንም ተጨማሪ መዘግየት ሊለቀቁ ይገባል” ሲሉም አሳስበዋል። 

የአማራ ክልል እና የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት በትላንትናው ዕለት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ በክልሉ ከሰሞኑ የተካሄደው እርምጃ “ህግ ማስከበር” መሆኑን አስታውቀዋል። “የኦፕሬሽኑ ዓላማ ሁከትን እና ብጥብጥን አስወግዶ ለክልሉ መንግስት እና ህዝብ ሰላምን ማስፈን” መሆኑን የሀገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ መናገራቸውን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ) ዘግቧል።

የአማራ ክልል የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መንገሻ ፈንታው በበኩላቸው፤ በሰሞኑ እርምጃ “በህግ ተጠያቂ” ከተደረጉት ውስጥ “በእገታ እና ዘረፋ የተሰማሩ” እንዲሁም በከተማ ሆነው “የማስተባበር” ስራ የሚያከናወኑ ኃይሎች እንደሚገኙበት ገልጸዋል። ዶ/ር መንገሻ “ጽንፈኛ” ሲሉ ለጠሯቸው ኃይሎች “የሎጀስቲክ እና የመረጃ ምንጮች” በመሆን ሲያገለግሉ ነበሩ ያሏቸው ግለሰቦችም “በተለያየ መንገድ ተጠያቂ እንዲሆኑ ስራ እየተሰራ” እንደሚገኝም አስረድተዋል። 

የህግ ተጠያቂነቱ “በመንግስት መዋቅር” ውስጥ ባሉ፣ “በንግዱ ዘርፍ” እና “በግላቸው በተሰማሩ” ሰዎች ላይ ጭምር ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል። ዶ/ር መንገሻ በትላንቱ መግለጫቸው፤ በህግ የሚጠየቁ ሰዎችን “በርካታ” መሆናቸውን የገለጹ ቢሆንም ብዛታቸውን በአሃዝ ከመግለጽ ተቆጥበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)