በሙሉጌታ በላይ
በባህር ዳር ከተማ ከትላንት በስቲያ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል አቶ ዘመነ ኃይሉ እና በአማራ ክልል ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ መልካሙ ተሾመ ከእስር ተለቀቁ። ሁለቱ የምክር ቤት አባላት ዛሬ ሐሙስ እኩለ ቀን ገደማ መፈታታቸውን አቶ ዘመነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
አቶ ዘመነ እና አቶ መልካሙ ከመስሪያ ቤታቸው በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱት ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ መስከረም 21፤ 2017 ነበር። የፓርላማ አባሉ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት አንድ ቀን አስቀድሞ፤ በሚኖሩበት ቀበሌ ያሉ ኃላፊ እና ሰራተኛ ወደ ቤታቸው በመምጣት አድራሻቸውን እና በመታወቂያቸው ያሉ መረጃዎችን አጣርተው መሄዳቸውን ተናግረዋል።
ይህ የተደረገበት ምክንያት ለምን እንደሆነ ለቀበሌ ሰራተኞቹ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር አቶ ዘመነ ገልጸዋል። በባህር ዳር ከተማ የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የጠይማ ቀበሌ ኃላፊ “አንዳንድ ነገር ማጣራት ፈልገን ነው። ስንፈልግ እንደውላለን” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸውም አብራርተዋል።
ከዚህ ሁነት ማግስት “የታጠቁ የአማራ ክልል አድማ በታኝ አባላት” ከመስሪያ ቤታቸው እንደወሰዷቸው የፓርላማ አባሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። አቶ ዘመነ በአማራ መልሶ መቋቋም እና ልማት ድርጅት (አመልድ) ስር ባለው ዓባይ ኮንስትራክሽን ውስጥ የእቅድ ክትትል እና ህዝብ ግንኙነት ኬዝ ቲም አስተባባሪ በመሆን እየሰሩ ይገኛሉ።
የአብን የፓርላማ ተወካዩ በትላንትናው ዕለት አምስት ሰዓት ገደማ በስራ ገበታቸው ላይ እያሉ፤ በቁጥር ስምንት ገደማ የሚሆኑ የአማራ ክልል አድማ በታኝ አባላት ወደ ቢሯቸው መምጣታቸውን ተናግረዋል። “ቢሮ እንዳይረበሽ ወደ ውጭ ወጣሁ። እኔ ነኝ አልኳቸው። ‘ለኢንተርቪው ፈልገንህ’ ነው አሉኝ። እሺ ብዬ [ሄድኩ]” ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል።
አቶ ዘመነ መጀመሪያ በባህር ዳር ከተማ ወደሚገኘው ሙሉአለም የባህል ማዕከል መወሰዳቸውን እና ወደ አመሻሽ አካባቢ በከተማይቱ ወዳለው ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ መዘዋወራቸውን አብራርተዋል። እንደ እርሳቸው ሁሉ ከሚሰሩበት መስሪያ ቤት የዚያኑ ዕለት በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የአማራ ክልል የምክር ቤት አባል አቶ መልካሙ ተበጀም በተመሳሳይ መልኩ ወደ ፖሊስ ጣቢያ መወሰዳቸውን አክለዋል።
ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ለአማራ ክልል ምክር ቤት የተመረጡት አቶ መልካሙ፤ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የምዕራብ ጎጃም ዞን አስተዳዳሪ ሆነው ሰርተዋል። በአማራ ክልል የጸጥታ ችግር ከተከሰተ በኋላ ከኃላፊነታቸው የተነሱት አቶ መልካሙ፤ በክልሉ የህንጻ ኮንስትራክሽን ድርጅት በህግ አማካሪነት ሲሰሩ ቆይተዋል።
በዚሁ ድርጅት በስራ ላይ ባሉበት ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱት አቶ መልካሙ፤ በዛሬው ዕለት ተፈትተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው መግባታቸውን ቤተሰቦቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሆኖም አቶ መልካሙም ሆነ ቤተሰቦቻቸው ስለ ትላንቱ እስርም እና ስለ ዛሬው ፍቺ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
አቶ ዘመነ በበኩላቸው ሁለቱ የምክር ቤት አባላት በታሰሩበት በባህር ዳር ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ “ያናገራቸው አካል” እንደሌለ። ከእስር ሲፈቱም “ቀጥታ ውጡ” ከመባል ውጭ “የተባልነው ነገር የለም” ሲሉ የፓርላማ አባሉ የተለቀቁበት ሂደት አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)