ከመስከረም ወር ጀምሮ ታሳቢ የሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን የገንዘብ ሚኒስትሩ ገለጹ

ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ለሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ከመስከረም ወር ጀምሮ ታሳቢ የሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ፤ ከትላንት በስቲያ በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ መጽደቁን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ። የደመወዝ ጭማሪው 92 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መጠየቁንም የገንዘብ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት፤ ከሁለት ወራት በፊት መተግበር የጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት ለመንግስት ቅርበት ላለው ፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው። ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ይፋ የተደረገውን ይህን የፖሊሲ ማሻሻያ ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ “በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርዓት” ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም አካል የሆነውን የእዚህን የፖሊሲ ለውጥ አፈጻጸም የሚገመግም ስብሰባ በትላንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተካሄዶ ነበር። በስብሰባው የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ “ፖሊሲው በስኬታማ አፈጻጸም ላይ መሆኑን ያለፉት ሁለት ወራት አሳይተዋል” ሲሉ በይፋዊ የማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። 

የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው ተፈጻሚ በሆነባቸው ወራት “የተረጋጋ የውጭ ምንዛሬ ከባቢን መመልከት ችለናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የገቢ ግባችንም የተቀመጠለትን ግብ በመምታት በታለመለት መንገድ ላይ ይገኛል” ሲሉ የአፈጻጸም ግምገማ ውጤቱን አብራርተዋል። በትላንቱ ስብሰባ ላይ የተሳተፉት እና የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ አህመድ በበኩላቸው፤ የፖሊሲ ማሻሻያው “በጎላ መልኩ ማህበራዊ ጫና እንዳያስከትል” በወጣው እቅድ መሰረት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ለፋና ቴሌቪዥን ተናግረዋል። 

የፌደራል መንግስት “በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ የመደገፉ ወይም የመደጎሙን ስራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት” የሚለው ከእቅዱ መካከል አንዱ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው ይፋ በተደረገበት ወቅት፤ ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች “አስፈላጊ የደመወዝ ድጎማ እና ማሻሻያዎች” “ለተወሰኑ ጊዜያት” እንደሚደረግ መገለጹ ይታወሳል።

ይህ የደመወዝ ጭማሪ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ መስከረም 21፤ 2017 ዓ.ም በተካሄደው “የካቢኔ” ስብሰባ ላይ መጽደቁን አቶ አህመድ ተናግረዋል። ከመስከረም ወር ጀምሮ ታሳቢ የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ፤ “ለኑሮ ድጎማ ጭምር እንዲሆን” በማሰብ የተተገበረ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።  

“ይሄኛው የደመወዝ ጭማሪ ከ 91 እስከ 92 ቢሊዮን [ብር] መካከል ተጨማሪ በጀት የሚጠይቅ ይሆናል። ይሄም በነባሩ በጀት በተወሰነ ደረጃ የገባ አለ። ተጨማሪ ደግሞ በተጨማሪ በጀትነት የሚታወጅ ይሆናል። ይሄኛው አጠቃላይ የመንግስት ሰራተኛው፤ በሁሉም፣ በጸጥታም በሌሎችም ዘርፍ ያሉትን የኑሮ ጫና ለመቋቋም የሚያስችለውን ድጋፍ ለማድረግ፤ መንግስት በከፍተኛ ቁርጠኝነት የገባበት ነው” ሲሉ አቶ አህመድ ለፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል።

የተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ ወር ባካሄደው ስብስባ፤ ለፌደራል መንግስት የ2017 በጀት ያጸደቀው የገንዘብ መጠን 971.2 ቢሊዮን ብር ነበር። አንድ ትሪሊዮን ብር የሚጠጋው ይህ በጀት ከዚህ ቀደም በፓርላማው ከጸደቁት ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራምን አስመልክቶ ባለፈው በሐምሌ ወር በተደረገ ስብሰባ ላይ፤ የሚመሩት መንግስት ለደመወዝ ጭማሪ ከ90 ቢሊዮን ብር በላይ እንደመደበ አስታውቀው ነበር። የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት እና የግል ባንኮች ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት በዚሁ ስብሰባ፤ በወር 1,500 ብር ለሚከፈላቸው የመንግስት ሰራተኞች 300 ፐርሰንት የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)