ኢትዮጵያ ከተነካች “ለማንም የማትመለስ” መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስጠነቀቁ

ኢትዮጵያ ጦርነት ባትፈልግም፤ ከተነካች ግን “ለማንም የማትመለስ” መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስጠነቀቁ። በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣን ወረራ ለመመከት የሚያስችል “በቂ አቅም አለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገሪቱ በውጊያ ላይ የገጠሟትን ክፍተቶች የሚያሟሉ “ነገሮች” ማምረት መጀመሯን ገልጸዋል።

ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 21፤ 2017 በተካሄደው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስደመጡት ማብራሪያ፤ “ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወደ ጦርነት ልትገባ ትችላለች” በሚል “አልፎ አልፎ” ስለሚቀርቡ ስጋቶች ምላሽ ሰጥተዋል። አንዳንድ ሰዎች ይህን ጉዳይ ከኤርትራ ጋር እንደሚያያዙት፤ ሌሎች ደግሞ “ሀገራት ኢትዮጵያን ሊወሩ ይችላሉ” የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል። 

ከኤርትራም ይሁን ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያም ይሁን ከኬንያ፤ ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት “ሰላማዊ ጉርብትና” እንደሆነ አብይ በማብራሪያቸው አስገንዘበዋል። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስም ላልጠቀሷቸው ሀገራት፤ ከእንግዲህ ወዲያ ኢትዮጵያን “እየመዘበሩ” እና “በሰፈር እያባሉ መኖር” እንደማይቻል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።  

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

“እኛ ቅጥረኞች አይደለንም። ለሆነ ቡድን ተቀጥረን፣ በስሙ ተገዝተን፣ የሆነ ቡድን አጀንዳ የምናራግብ ቅጥረኞች ሳንሆን፤ አርበኞች ነን። ይሄን አምኖ ካከበረ ማንኛውም ሀገር [ጋር] በከፍተኛ ደስታ አብረን መስራት እንፈልጋለን” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የፓርላማ አባላት በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የምትፈልገው “ሰላም” መሆኑን የተናገሩት አብይ፤ “ከዚያ የከፋ ነገር ካልመጣ በስተቀር በኤርትራ ወንድሞቻችን ላይ ምንም ነገር አይፈጸምም” ሲሉ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማስተማመኛ ሰጥተዋል። “ጅቡቲን እንኳን እኛ ልንረብሽ እና ልንነካቸው ቀርቶ፣ የሚነካቸው ካለ፤ አንቀመጠም” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል።

ከዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ የገቢ እና የወጪ ንግድ የሚከናወነው በጅቡቲ ወደቦች በኩል ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ይህንኑ ባመላከተ ንግግራቸው፤ “እነርሱ ከተነኩ እኛ የለንም” ብለዋል። ኢትዮጵያ እንደ ኤርትራ እና ጅቡቲ ሁሉ፤ ከሶማሊያ ጋር ያላት ግኙነትም ሰላማዊ እንዲሆን እንደምትፈልግም አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) 

ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሌላንድ ጋር የባህር ወደብ ለማልማት እና የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላት የመግባቢያ ስምምነት ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ከተፈራረመች ወዲህ ከሶማሊያ ጋር ላይ ያላት ግኙነት እንዳሻከረ ነው። ሶማሌላንድ “የግዛቴ አካል ነች” የምትለው ሶማሊያ፤ የመግባቢያ ስምምነቱ “ሉዓላዊነቷን የጣሰ” መሆኑን በመግለጽ አጥብቃ ስትቃወም ቆይታለች።  

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው የፓርላማ ማብራሪያቸው “ሶማሊያ አካባቢ መስከን፣ መረጋጋት፣ ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደም እንዲችሉ ጊዜ ሰጥተናል። እንታገሳለን። ቀልብ እንዲገዙ፤ ሰብር እንዲያደርጉ እንታገሳለን። ግን ኢትዮጵያ የማይናወጥ ብሔራዊ ጥቅም አላት። አለም ዛሬ ይስማ። የቀይ ባህር access ሰላማዊ በሆነ መንገድ ኢትዮጵያ ያስፈልጋታል” ሲሉ ጠንከር ባሉ ቃላት የሀገራቸውን አቋም አስታውቀዋል። ይህ ንግግራቸው በድጋሚ ከፓርላማ አባላት ጭብጨባ ተችሮታል።

“በዚህ ጉዳይ shy የምናደርግ፣ የምንደብቅ የሚመስለው ካለው ተሳስቷል። በጦርነት አንፈልግም፣ በኃይል አንፈልግም። [ቀይ ባሕር] በቂ resource ነው። በማንኛውም ህግ፣ በማንኛውም የሀገር ልምምድ፣ ኢትዮጵያ ይገባታል። ብዙዎች እኮ ‘ነውር ነው’ ይላሉ። ‘120 ሚሊዮን ህዝብ መቆለፍ፤ ነውር ነው’ ይላሉ” ሲሉም ኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጽንኦት አንስተዋል። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ይህንን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም “ወይ እኛ፣ ወይ ልጆቻችን ያሳኩታል” ሲሉ የተደመጡት አብይ፤ ሆኖም ይህን አስታክኮ “ውጊያ ይነሳል” በሚል ለሚሰጉ ሰዎች፤ በኢትዮጵያ በኩል “የመዋጋት ፍላጎት” እንደሌለ አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሀገራት ኢትዮጵያን ሊወሩ ይችላሉ” የሚል ስጋት ላለባቸው ወገኖችም፤ የማስተማመኛ ምላሽ ሰጥተዋል። 

“ኢትዮጵያን ማንም ሰው ዛሬ በኃይል መውረር አይችልም። ማንም። ለመመከት የሚያስችል በቂ አቅም አለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “ስንገዛ፣ ስንሸምት የነበረንባቸውን፤ በውጊያ ክፍተት የገጠሙንን ነገሮች ማምረት ጀምረናል። እናመርታለን፣ ሰው አለን፣ ጀግኖች ነን። ሰው አንነካም፣ ከነኩን ግን ለማንም አንመለስም። ስጋት የለብንም” ሲሉ ማስጠንቀቂያ የቀላቀለ ንግግር አድርገውል። 

ማብራሪያቸውን ሲከታተሉ የነበሩ የፓርላማ አባላት፤ ይህንን ተከትሎ ሞቅ ያለ የድጋፍ ጭብጨባ አስምተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም “ስጋት አይግባችሁ። ማንም ቢመጣ አሳፍረን እንመልሳለን” ሲሉም ለፓርላማ አባላቱ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

“ማንም ላይ ጦር የመስበቅ ፍላጎት የለንም። ማንም ኢትዮጵያን እንዲደፍር ግን አንፈቅድም”

– ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

“የምንፈልገውን ነገር ልክ እንደ ህዳሴ፣ በእኛ አቅም፣ በእኛ ጉልበት በሰላማዊ መንገድ እንሳካለን። ማንም ላይ ጦር የመስበቅ ፍላጎት የለንም። ማንም ኢትዮጵያን እንዲደፍር ግን አንፈቅድም” በሚል ንግግርም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የዛሬ የፓርላማ ማብራሪያቸውን ቋጭተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)