የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ እና የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ በፍርድ ቤት ብይን ተሰጠ

በቤርሳቤህ ገብረ

የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል በመፈጸም እና በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ የተከሰሱት የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ቱኬ፤ በቀረቡባቸው ሁለት ክሶች ላይ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ። በቀድሞው ከንቲባ እና አብረዋቸው በተከሰሱ ሁለት ተከሳሾች ላይ ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 19፣ 2017 ብይኑን የሰጠው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል ነው።

የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ፤ በአቶ ጸጋዬ እና ሁለት ተከሳሾች ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ የመሰረተው፤ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። በአንድ መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል፤ የሲዳማ ክልል የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አበራ አሬራ ይገኙበታል። 

የክልሉ ዐቃቤ ህግ በአቶ አበራ እና በአቶ ጸጋዬ ላይ የመሰረተው የመጀመሪያ ክስ፤ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ የተቀመጠን ድንጋጌ በመተላለፍ “የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” የሚል ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የመጀመሪያው ክስ፤ በሀዋሳ ከተማ ሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል ጎን የተወሰደ ቦታ ምትክ መሬት እንዲሰጥ ከቀረበ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው።

የምትክ ቦታ ጥያቄ ቀርቦ የነበረው፤ ከአቶ ጸጋዬ አስቀድሞ በነበሩት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ የአመራር ጊዜ እንደነበር በክሱ ተመላክቷል። አቶ ጥራቱ የምትክ ቦታ እንዲሰጥ ውሳኔ ቢያስተላልፉም፤ የመሬት ርክክብ ከመፈጸሙ በፊት ከኃላፊነታቸው በመነሳታቸው ጉዳዩ እርሳቸውን ለተኳቸው አቶ ጸጋዬ ተላልፏል። 

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባነትን በጥቅምት 2013 ዓ.ም. የተረከቡት አቶ ጸጋዬ፤ በቀድሞ ከንቲባ ውሳኔው መሰረት ምትክ ቦታ እንዲሰጡ “ተደጋጋሚ” ጥያቄ ቢቀርብላቸውም “እምቢተኛ ሆነው መቆየታቸውን” የክስ መዝገቡ ላይ ያትታል። በዚህ ምክንያት የቦታው ባለጉዳይ የሆኑት አቶ ታረቀኝ ተክሉ የተባሉት ግለሰብ፤ ጉዳዩን በወቅቱ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ለነበሩት ተከሳሽ መናገራቸውን በክስ መዘገቡ ላይ ሰፍሯል። 

የቀድሞው ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አበራ፤ የምትክ ቦታ ጥያቄውን በተመለከተ “ከንቲባው እንዲጨርስልህ አደርጋለሁ” ማለታቸው በክስ መዝገቡ ላይ ተቀምጧል። አቶ አበራ ከወቅቱ የሀዋሳ ከንቲባ ጋር በመነጋገር፤ የምትክ ቦታ ጠያቂው ግለሰብ 516,024 ብር በሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የባንክ የሂሳብ ቁጥር ገቢ እንዲያደርጉ አስደርገዋል በሚል ተወንጅለዋል።

ይህ ገንዘብ ወደ ከተማይቱ ማዘጋጃ ቤት እንዲገባ የተደረገው የአቶ ጸጋዬ የእህት ልጅ በሆኑት አቶ አብርሃም አመሎ በተባሉ ግለሰብ ስም መሆኑም በክሱ ላይ ተጠቅሷል። ይህ ክፍያ አቶ ጸጋዬ፤ “በእህታቸው ልጅ ስም” በሀዋሳ ከተማ በጨረታ ላሸነፉት ቦታ ክፍያ የሚውል መሆኑም በክሱ ተመልክቷል።

የሲዳማ ክልል ዐቃቤ ህግ የመሰረተው ሌላኛው ክስ፤ ከቀድሞው ከንቲባ እና የፖሊስ ኮሚሽነር በተጨማሪነት አቶ አብርሃምንም ያካተተ ነው። አቶ አብርሃም የተከሰሱት፤ ከሁለቱ ተከሳሾች “የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ፈጽመውታል” በተባለው የሙስና ወንጀል ላይ “በመመሳጠር” እና በአቶ ጸጋዬ ስም የመሬት ጨረታ በመወዳደር ነው። 

እኚሁ ተከሳሽ ለአቶ ጸጋዬ ጥቅም ተወዳድረው ላሸነፉት መሬት፤ አቶ ታረቀኝ ተክሉ የተባሉ ሌላ ባለጉዳይ ለሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ክፍያ እንዲፈጽሙ ማድረጋቸው በወንጀልነት ተጠቅሶባቸዋል። የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባ፤ አቶ አብርሃም ያሸነፉት መሬት “በሙስና ወንጀል የተገኘ” የከተማ ይዞታ መሆኑን እያወቁ፤ በስማቸው 200 ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ የሊዝ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት (ሳይት ኦፕላን) አሰርተው፤ ህጋዊ አስመስለው በማቅረብም ተወንጅለዋል። 

“በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ” በሚለው በዚህ ክስ፤ አቶ አበራ እና አቶ አብርሃም ተጠያቂ ተደርገዋል። በዚህ እና የሙስና ወንጀልን በመፈጸም ክስ የመሰረተው የሲዳማ ክልል ዐቃቤ ህግ፤ ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በነበሩ የችሎት ውሎዎች ክሱን ሲያስረዳ፣ ምስክሮችን እና ማስረጃዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። 

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የሀዋሳ ማአከል፤ ተከሳሾች የቀረቡባቸውን ሁለት ክሶች እንዲከላከሉ ብይን በመስጠት ለህዳር 13፤ 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ብይኑን የሰጠው፤ በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረበውን ማስረጃ ከመረመረ በኋላ ጉዳዩን ለማስረዳት “በቂ ሆኖ” በማግኘቱ እንደሆነ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሲዳማ ክልል የፍትህ ቢሮ ከፍተኛ ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የአቶ ጸጋዬ የቅርብ የቤተሰብ አባል፤ ተከሳሾች ክሱን እንዲከላከሉ ብይን ስለመስጠቱ አረጋግጠዋል። የቀድሞው ከንቲባ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የተያዘ ቢሆንም፤ የቤተሰብ አባሎቻቸው በየጊዜው እንግልት እየደረሰባቸው መሆኑንም ተናግረዋል። የአቶ ጸጋዬን ክስ በተመለከተ ጠበቆቻቸው ያላቸውን መረጃ ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

የሀዋሳ ከተማን ለሶስት ዓመታት የመሩት አቶ ጸጋዬ ቱኬ፤ በብልሹ አሰራር እና የአፈጻጸም ድክመት ተገምግመው ከኃላፊነታቸው የተነሱት በነሐሴ 2015 ዓ.ም ነበር። በዚሁ ወቅት በተካሄደው ግምገማ አቶ ጸጋዬ “በህግ እንዲጠየቁ ውሳኔ ተላልፎባቸው” የነበረ ቢሆንም፤ ውሳኔው ለሁለት ወራት ያህል ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል።

የቀድሞው ከንቲባ በጸጥታ ኃይሎች አማካኝነት በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በጥቅምት 2016 ዓ.ም. ከአሜሪካ ሲመለሱ በቦሌ አየር ማረፊያ እንደነበር ይታወሳል። የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ፤ በአቶ ጸጋዬ ላይ የመጀመሪያውን የክስ መዝገብ የከፈተው በጥር 2016 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ነበር። 

በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ ባለው በዚህ መዝገብ፤ አቶ ጸጋዬን ጨምሮ ሰባት ተከሳሾች “በህገ ወጥ መንገድ ሰነድ ማዘጋጀት፣ ጉቦ መቀባበል እና ስልጣንን አላግባብ መጠቀም” የሚሉትን ጨምሮ አምስት ክሶች ቀርበውባቸዋል። የከተማይቱ ፍርድ ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት ባስቻለው ችሎት፤ “በዐቃቤ ህግ ማስረጃ አልተረጋገጠም” በሚል ከአምስቱ ክሶች አንዱን ውድቅ አድርገውታል።

ጥቅምት 8፣ 2017 በነበረው በዚሁ ችሎት፤ አቶ ጸጋዬ እና ስድስት ተከሳሾች፤ በቀረቡባቸው አራት ክሶች ላይ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል። የተከሳሾችን መከላከያ ለመስማትም ለመጪው ረቡዕ ጥቅምት 27 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)