አዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ያካተታቸው ተጨማሪ ድንጋጌዎች የትኞቹ ናቸው?

በቤርሳቤህ ገብረ

ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 8፤ 2017 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የባንክ ስራ አዋጅ፤ በረቂቅ ደረጃ ከነበረው ይዘት የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርገውበታል። በሶስት የፓርላማ አባላት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው ይህ አዋጅ፤ በረቅቁ ላይ ተካትተው በነበሩ ትርጓሜዎች እና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ አድርጓል። 

ማሻሻያ ከተደረገባቸው ድንጋጌዎች መካከል የባንክ ቅርንጫፎች እና የውጭ ባንኮችን የተመለከቱት ይገኙበታል። የውጭ ዜጎች በባንክ ስራ የሚሳተፉበትን አካሄድ በሚዘረዝረው የአዋጅ ክፍል ላይ አዲስ አንቀጽ እንዲካተት ተደርጓል። በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ ዜጋ በባንክ ስራ ስለሚሰማራበት ሁኔታ በረቂቁ ላይ ከተቀመጠው በተጨማሪም አዲስ ድንጋጌ በጸደቀው አዋጅ ላይ ተካትቷል። 

ከማሻሻያዎቹ እና ከአዳዲስ አንቀጾች ውስጥ በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠናቀሩትን፤ ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል፦

ትርጓሜዎች

ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት፦ ባለፈው ሰኔ ወር ለፓርላማ የቀረበው የአዋጅ ረቂቅ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትን ትርጓሜ ሲያብራራ “ወለድ ያለመቀበልን ጨምሮ ከሸሪዓ መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ የሚሰጥ የባንክ አገልግሎት ነው” በሚል ነበር ያስቀመጠው። ይህ ድንጋጌ በጸደቀው አዋጅ እንደ አዲስ እንዲሻሻል ተደርጓል።

በአዲሱ ድንጋጌ “ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት” ማለት “ወለድ ያለመቀበልን ጨምሮ ከሸሪዓ መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መልኩ በወለድ ነጻ ባንኮች እና ከወለድ ነጻ አገልግሎት መስኮት በሚሰጡ ባንኮች የሚሰጥ እንደሆነ” ተቀምጧል። ይህ ማሻሻያ የተደረገው፤ አገልግሎቱ በወለድ ነጻ ባንኮች እና ከወለድ ነጻ አገልግሎት መስኮት በሚሰጡ ባንኮች የሚሰጥ መሆኑን “በማያሻማ መልኩ” መደንገግ አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ለፓርላማ በቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተብራርቷል።  

ቋሚ ንብረቶች፦ የአዋጅ ረቂቁ የትርጓሜ ክፍል፤ ቋሚ ንብረቶች “የረጅም ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ንብረቶች ሆነው በመመሪያ ይወሰናሉ” በማለት የተሰጠው ትርጓሜም እንደዚሁ ተሻሽሏል። ዛሬ በጸደቀው አዋጅ “ቋሚ ንብረት” ማለት “ግዙፋዊ ሀልዎት ያለው እና ገቢ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጥ ንብረት እና ዝርዝሩ በብሔራዊ ባንክ መመሪያ የሚወሰን ነው” የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል። 

ሀብት እና እዳ ማስተላለፍ፦ የአንድ ባንክን የባንክ ስራ ኢትዮጵያ ውስጥ ለተሰማራ ሌላ ባንክ ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ማስተላለፍ የሚመለከተው የ“ሀብት እና እዳ ማስተላለፍ” ትርጓሜ፤ ፋይናንስ ነክ የሆኑ እና ያልሆኑ ሀብቶችን የሚጨምር እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተቀምጧል። በጸደቀው አዋጅ ላይ “ዕዳዎች” በተመሳሳይ መልኩ እንደሚተላለፉ ተደንግጓል።

የባንኮችን ቅርንጫፍ በተመለከተ

የባንክ ቅርንጫፍ ወይም ንዑስ ቅርንጫፍ ለመክፈት መሟላት ያለባቸው “ዝቅተኛ ሁኔታዎች እና መስፈርቶች በብሔራዊ ባንክ መመሪያ” እንደሚወሰኑ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተቀምጦ ነበር። በጸደቀው አዋጅ ከዚህ በተጨማሪ የባንክ ቅርንጫፎችን ለመዝጋት መሟላት ያለባቸው “ዝቅተኛ ሁኔታዎች እና መስፈርቶች” በብሔራዊ ባንክ መመሪያ እንዲወሰን ተደርጓል።   

የውጭ ባንክ እንደራሴ ቢሮ በተመለከተ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማንኛውም የውጭ ባንክ እንደራሴ ቢሮ ፈቃድ ለማግኘት ሊያሟላቸው የሚገቡ ዝቅተኛ ሁኔታዎች እና መስፈርቶችን በተመለከተ በመመሪያ እንደሚወስን በረቂቅ አዋጁ ስልጣን ተሰጥቶት ነበር። በጸደቀው አዋጅ ላይ ባንኩ ከዚህ ስልጣን በተጨማሪ “ቁጥጥር የማድረግ” ኃላፊነትም ተደርቦለታል።   

በአዋጅ ረቂቁ ላይ “ማንኛውም ባንክ ከብሔራዊ ባንክ አስቀድሞ የጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ቅርንጫፍ ወይም ንዑስ ቅርንጫፍ መክፈት አይችልም” የሚል ድንጋጌ ሰፍሮ ነበር። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ማንኛውም ባንክ ከብሔራዊ ባንክ አስቀድሞ የጽሁፍ ፈቃድ ሳያገኝ  “የተከፈተ ቅርንጫፍ መዝጋት አይችልም” የሚል ተጨማሪ ድንጋጌ ታክሎበታል።   

የውጭ ባንኮችን በተመለከተ

የአዋጅ ረቂቁ “ማንኛውም ተቀማጭ ገንዘብ የሚቀበል ወይም የማይቀበል የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ ወይም የውጭ ባንክ ተቀጥላ፤ ተቆጣጣሪው ያወጣቸውን ማንኛውም የጤናማነት መለኪያ መስፈርቶች እንደአግባብነቱ ከሀገር ውስጥ ባንኮች እኩል ማክበር አለበት” ይላል። የውጭ ባንክ ቅርንጫፉ ወይም የውጭ ባንክ ተቀጥላው ከዚህ በተጨማሪ “ሌሎች አግባብነት ያላቸው ተቆጣጣሪ አካላት ያወጡትን ህጎች ማክበር” እንደሚጠበቅበት በጸደቀው አዋጅ ላይ ሰፍሯል። 

ይህ ማሻሻያ የተደረገው “የውጭ ባንኮች የብሔራዊ ባንክን ብቻ ሳይሆን የሌሎች አግባብነት ያላቸውን ተቆጣጣሪ አካላት ህጎችን ከሀገር ውስጥ ባንኮች እኩል አክብረው መስራት እንዳለባቸው ለማመላከት” እንደሆነ በማሻሻያው ላይ ሰፍሯል።

የውጭ ዜጎች በባንክ ስራ ስለሚሳተፉበት ሁኔታ

አዲስ ድንጋጌ፦ የውጭ ዜጎች በተለያዩ ዘዴዎች የሚያደርጉት ኢንቨስትመንት በባንክ ስራ አዋጅ የተደነገገውን ገደብ በጠበቀ መልኩ መሆኑን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ ያልነበረ አዲስ ድንጋጌ በጸደቀው አዋጅ እንዲካተት ተደርጓል። ይህ ድንጋጌ “በውጭ ዜጎች እና ኢትዮጵያዊያን ወይም እንደ አገር ውስጥ ባለሀብት በሚቆጠር የውጭ ሀገር ዜግነት ባለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በጋራ ባለቤትነት የተያዘ ድርጅት፤ አንድ ባንክ ላይ አክስዮን ሲይዝ፤ ባንኩ ላይ የተደረገው የውጭ ኢንቨስትመንት መጠን የሚሰላው፤ አክስዮን በገዛው ደርጅት ላይ የውጭ ዜጎች ያላቸውን የባለቤትነት ድርሻ መጠን መሰረት በማድረግ ይሆናል” ይላል። 

የተሰረዘ ድንጋጌ፦ “ተቀማጭ የማይቀበል የውጭ ባንክ ቅርንጫፍን” በተመለከተ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተካትቶ የነበረው ድንጋጌ በጸደቀው አዋጅ እንዲሰረዝ ተደርጓል። የተሰረዘው ድንጋጌ “ማንኛውም ተቀማጭ የማይቀበል የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ መሰማራት የሚፈቀድለት፤ በማበደር፣ የብድር ክፍያዎችን በመቀበል እና ብድር የመስጠት ሂደቱን ለማቀላጠፍ የተከፈቱ የተበዳሪዎች የተቀማጭ ሂሳቦችን በማስተዳደር ላይ ብቻ ነው” የሚል ነበር። 

የውጭ ባንኩ “ብድሮችን እና ሌሎች ፋይናንሶችን ከውጭ ሀገር ምንጮች ሊያገኝ እና በብሔራዊ ባንክ መመሪያ እና አግባብነት ባላቸው ሌሎች ሕጎች መሰረት መጀመሪያ ላይ በተመዘገበው አግባብ መልሶ ሊከፍል” እንደሚችልም በዚህ ድንጋጌ ላይ ተካትቶ ነበር። ይህ ድንጋጌ በጸደቀው አዋጅ ላይ ሳይካተት የቀረው“ ማንኛውም የውጭ ባንክ ቅርንጫፍ በኢትዮጵያ ውስጥ ስራ በሚሰራበት ወቅት የሚፈቀዱለትን እንቅስቃሴዎች በግልጽ የሚያስቀምጥ መመሪያ ብሔራዊ ባንክ እንደሚያወጣ የተደነገገ” በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ለፓርላማ አባላት የተሰራጨው ማብራሪያ ያስረዳል። 

በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ ዜጋ በባንክ ስራ ስለሚሰማራበት ሁኔታ

በፓርላማ የጸደቀው አዋጅ በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ ዜጋ በባንክ ስራ የሚሰማራበትን ሁኔታ የተመለከተ አዲስ አንቀጽ፤ በረቂቁ ከተቀመጡ ድንጋጌዎች በተጨማሪነት እንዲያካትት ተደርጓል። አዲሱ አንቀጽ የተካተተው “በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ የውጭ ዜጎች በባንክ ሥራ ላይ ስለሚኖራቸው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ስርዓት በግልጽ በሕግ መደንገግ በማስፈለጉ” ምክንያት እንደሆነ በማብራሪያው ላይ ተቀምጧል።

ይህ አንቀጽ “አግባብነት ባለው ሕግ የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ስለመሆኑ የተረጋገጠ ሰው ወይም በእነዚህ ሰዎች ሙሉ በሙሉ የተያዘ እና የተቋቋመ ድርጅት እና እንደ አገር ውስጥ ባለሀብት መቆጠር የፈለገ፤ በብር የባንክ አክሲዮን ስለሚገዛበት አግባብ ወይም ባንክ ስለሚያቋቁምበት አግባብ ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ የሚወሰን ነው” ይላል። ሆኖም ትውልደ ኢትዮጵያዊው ከዚሁ ኢንቨስትመንት የሚያገኘውን ማንኛውንም ክፍያ ወይም ገቢ “በውጭ ምንዛሬ ከኢትዮጵያ ውጭ ማዛወር እንደማይችል” በአዲሱ አንቀጽ ላይ ተደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)