በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተጣለበት እገዳ ባለፈው ሳምንት ተነስቶለት የነበረው የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በድጋሚ ታገደ። ሀገር በቀሉ የሰብአዊ መብት ድርጅት የታገደው፤ በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሰረት “አሰራሩን ባለማስተካከሉ” እና “ከዚህ ቀደም የፈጸማቸውን ጥፋቶች በመቀጠሉ ነው” ሲል ባለስልጣኑ ወንጅሏል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ እነዚህን እና ሌሎችን ውንጀላዎችን ለድርጅቱ በጻፈው ደብዳቤ ላይ መግለጹን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ፊርማ ያረፈበት ይህ ደብዳቤ የተጻፈው በትላንትናው ዕለት ቢሆንም፤ ለካርድ አመራሮች የደረሰው ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 8፤ 2017 መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ገልጸዋል።
ደብዳቤው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በካርድ ላይ ባደረገው “የክትትል እና “የግምገማ ስራዎች”፤ ድርጅቱ ፈጽሟቸዋል ያላቸውን “የህግ ጥሰቶች” በመዘርዝር ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ እንደነበር አስታውሷል። በዚህ መሰረት ድርጅቱ “በተቋቋመበት ዓላማ መሰረት”፤ “ህጋዊ ሂደትን ጠብቆ እንዲሰራ” “በጥብቅ ማሳሰቡንም” ጠቅሷል።
ባለስልጣኑ የጠቀሰው ማስጠንቀቂያ ለካርድ የተሰጠው፤ በድርጅቱ ላይ ለአንድ ወር ያህል ጸንቶ የቆየው እግድ በደብዳቤ መሻሩን በገለጸበት በተመሳሳይ ዕለት ነው። ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ታህሳስ 2፤ 2017 ዓ.ም. በባለስልጣኑ የተጻፈው ይኸው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፤ ካርድ ለመጀመሪያ ጊዜ በታገደበት ወቅት ከተጠቀሱበት ምክንያቶች በተጨማሪ ፈጽሟቸዋል የተባሉ ሌሎች ሶስት የህግ ጥሰቶችን ዘርዝሯል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሰረት ስራቸውን ማከናወናቸውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ ካርድን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገደው በህዳር ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። ባለስልጣኑ ድርጅቱን ያገደው ከተቋቋመበት “ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሷል” በሚል ምክንያት ነበር።
ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ከአንድ ወር በፊት ህዳር 3 ለካርድ በጻፈው ደብዳቤ፤ “ድርጅቱ ከፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ መስራት ሲገባው ከዓላማው ውጭ በመንቀሳቀስ የሀገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት ላይ መሰማራቱን” እንዳረጋገጠ ገልጾ ነበር። ይህንን ተከትሎ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ባወጣው መግለጫ፤ “ለእግድ የተሰጠው ምክንያት ከእውነታው የራቀ ነው” ሲል አስተባብሏል።
“ግልጽነት”፣ “ገለልተኝት” እና “ዴሞክራሲያዊነት” የማያወላውል መርሆዎቹ መሆናቸውን በመግለጫው የጠቀሰው ካርድ፤ ድርጅቱ “ከዓላማው ውጪ ምንም ዓይነት ተግባራት ላይ እንደማይሳተፍ” እና “በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ፍጹም ገለልተኛ ተቋም መሆኑን” በአጽንኦት ገልጿል። ድርጅቱ ይህን ቢልም፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፈው ሳምንት በጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ላይ እነዚህን ውንጀላዎች በድጋሚ ጠቅሷቸዋል።
በዚሁ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ፤ ካርድ “ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በመንቀሳቀሱ የአገራዊ አብሮነትና መግባባት ጥረቶችን ለማደናቀፍ ሞክሯል” ሲል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ወንጅሎታል። ድርጅቱ “ከሚመለከተው የመንግስት አካላት ጋር ፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርሞ እየሰራ አለመሆኑ” እና “ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እውቅና ውጪ የባንክ አካውንቶችን ከፍቷል” መባሉ በማስጠንቀቂያ ደብዳቤው የተጠቀሱ ቀሪዎቹ ጥሰቶች ናቸው።
ካርድ ማስጠንቀቂያው በደረሰው በማግስቱ ባወጣው መግለጫ፤ በደብዳቤው “ጥሰት ናቸው” ተብለው የተቀመጡትን ነጥቦች አስመልክቶ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት እንደሚቀጥል አስታውቆ ነበር። ድርጅቱ በእነዚህ ውይይቶች “ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎቹን” ለመፍታት እንደሚጥር ቢገልጽም፤ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በድጋሚ “ከማንኛውም የስራ እንቅስቃሴ” ታግዷል።
ካርድ “ለባለስልጣኑ ህግ እና ውሳኔ ባለመገዛት”፣ “ለመማር ዝግጁ ባለመሆን” “ከዚህ ቀደም የፈጸማቸውን ጥፋቶች በመቀጠል” በተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ተጨማሪ ውንጀላዎች ቀርቦበታል።
ድርጅቱ ከታገደባቸው ምክንያቶች አንዱ “በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሰረት አሰራሩን ያላስተካከለ” በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በትላንትናው ዕለት በጻፈው ደብዳቤ ላይ አስፍሯል። ካርድ “ለባለስልጣኑ ህግ እና ውሳኔ ባለመገዛት”፣ “ለመማር ዝግጁ ባለመሆን” “ከዚህ ቀደም የፈጸማቸውን ጥፋቶች በመቀጠል” በተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ተጨማሪ ውንጀላዎች ቀርቦበታል።
“በሰብዓዊ መብቶች እሴቶች ላይ የቆመ ዲሞክራሲያዊ ባሕል ያበበባት ኢትዮጵያን ማየት” ራዕይ ያደረገው የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፤ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ህጋዊ ሰውነት ያገኘው በ2011 ዓ.ም ነበር። ለትርፍ ያልተቋቋመው ይህ ሀገር በቀል ድርጅት፤ የኢትዮጵያ ዜጎች እና የዜጎች ማህበራት “ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በመሟገት፤ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲያሰፍኑ” የሚያስችላቸውን የአቅም ግንባታ የማድረግ ተልዕኮ ያለው ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)