በቤርሳቤህ ገብረ
የፌደራል የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን፤ 84 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እስከ መጪው ጥር ወር መጀመሪያ ድረስ ተማሪዎቻቸውን ፈቃድ ወዳላቸው ተቋማት እንዲያዘዋውሩ ትዕዛዝ አስተላለፈ። ባለስልጣኑ ይህንን ትዕዛዝ የሰጠው፤ በድጋሚ ሳይመዘገቡ ለቀሩ እና በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን ለማቋረጥ ለወሰኑ ኮሌጆች ነው።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባወጣው “አዲስ ስታንዳርድ” መሰረት፤ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳግም እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርቦ የነበረው ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ነበር። በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚንቀሳቀስ ማንኛውም የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፈቃድ የመስጠት፣ የማደስ እና ቁጥጥር የማድረግ ስልጣን ለመስሪያ ቤቱ የሰጠው በ2014 ዓ.ም. የተሻሻለው የባለስልጣኑ ማቋቋሚያ ደንብ ነው።
መስሪያ ቤቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ፈቃድ ወይም እድሳት የመሰረዝ ስልጣንም በዚሁ ደንብ አግኝቷል። በዚሁ መሰረት 84 የሚሆኑ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት “ከከፍተኛ ትምህርት የፈቃድ ስርአት እንዲወጡ” የሚያደርጋቸውን ውሳኔ ባለስልጣኑ ከሁለት ሳምንት በፊት አስተላልፏል። ዘጠኝ በሚሆኑ የትምህርት ተቋማት ላይም ተመሳሳይ ውሳኔ በቅርቡ እንደሚተላለፍ ከባለስልጣኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
በባለልጣን በመስሪያ ቤቱ የፈቃድ አሰጣጥ እና ጥራት ኦዲት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ታደለ ፊርማ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ለ84ቱ የትምህርት ተቋማት የተላከ ደብዳቤ፤ ውሳኔው የተላለፈው በተሰጣቸው የጊዜ ሰሌዳ ቀርበው ባለመመዝገባቸው እንደሆነ ይጠቅሳል። የዳግም ምዝገባው ካስፈለገባቸው ምክንያቶች አንዱ “ያልጠራ መረጃ” ያላቸው እና “ባለቤትነታቸው የማይታወቁ ተቋማት” በመኖራቸው” ምክንያት እንደሆነ አቶ ውብሸት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የትምህርት ተቋማቱ በዳግም ምዝገባ እንዲያሟሉ ከተጠየቋቸው ጉዳዮች መካከል፤ የ500 ሺህ ብር ተመጣጣኝ ዋስትና፣ የታደሰ የንግድ ፈቃድ እና በአምሮአዊ ንብረት የተመዘገበ የንግድ ሎጎ ይገኙባቸዋል። የጤና ትምህርት ለሚሰጡ የትምህርት ተቋማት ከእነዚህ ጉዳዮች ተጨማሪ መስፈርት ተቀምጦላቸዋል።
እነዚህ የትምህርት ተቋማት ለህክምና ትምህርት እና ስፔሻሊቲ ትምህርት መስኮች የማስተማሪያ ሆስፒታል ያላቸው ስለመሆኑ አሊያም ከጤና ተቋማት ጋር የፈጸሙትን ስምምነት የሚያረጋግጥ ሰነድ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚጠይቃቸው እነዚህን ሰነዶችን ካስገቡ ተቋማት መካከል “የተጓደለ” ወይም “የተሳሳተ ሰነድ” ያስገቡ ካሉ ይህንን የሚያስተካክሉበት እድል እንደሚሰጣቸው አቶ ውብሸት አስረድተዋል።
ሰነድ ያስገቡ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ “የመስክ ምልከታ” እንደሚደረግባቸው ምክትል ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልጸዋል። በመስክ ምልከታው ውጤት መሰረት፤ ተቋማቱ “እንዲቀጥሉ ወይም እንዲሰረዙ” ሊደረግ እንደሚችልም አቶ ውብሸት አመልክተዋል። ዳግም ምዘገባ ባለማካሄዳቸው ከከፍተኛ የትምህርት ፈቃድ ስርአት ውጭ እንዲሆኑ የተደረጉ የትምህርት ተቋማት በበኩላቸው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተማሪዎቻቸውን ፈቃድ ወዳላቸው ተቋማት እንዲያዘዋውሩ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸዋል።
ይህ ቀነ ገደብ ከባለስልጣኑ የማስተማር ፈቃድ ወስደው በገዛ ፈቃዳቸው ለማቋረጥ ደብዳቤ ያስገቡ ተቋማትን ይመለከታል። የትምህርት ተቋማቱ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ፤ የመውጫ ሰነድ በመሙላት፣ ክሊራንስ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያስቀመጠውን ሂደት የማይተገብሩ ተቋማት “በሀገሪቱ የወንጀል እና የፍትሐ ብሔር ህግ” መሰረት እንደሚጠየቁ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስጠንቅቋል።
ባለስልጣኑ የሰጠው ቀነ ገደብ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሲጠናቀቅ፤ ትዕዛዙን ተግባራዊ ባላደረጉ የትምህርት ተቋማት ላይ በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ክስ እንደሚመሰርት አቶ ውብሸት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። መስሪያ ቤቱ ደብዳቤ ከላከላቸው 84 የትምህርት ተቋማት መካከል እስካሁን ድረስ ሂደቱን አጠናቅቀው ከፈቃድ ስርአቱ መውጣታቸው የተረጋገጠው አምስት ብቻ ናቸው።
ባለስልጣኑ የሰጠው ቀነ ገደብ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሲጠናቀቅ፤ ትዕዛዙን ተግባራዊ ባላደረጉ የትምህርት ተቋማት ላይ በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ክስ ይመሰርታል ተብሏል።
ተማሪዎቻቸውን ወደ ሌሎች ተቋማት እንዲያዘዋውሩ በደብዳቤ ትዕዛዝ ከደረሳቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአንዱ ውስጥ በኃላፊነት የሚሰሩ ግለሰብ፤ ኮሌጃቸው ዳግም ምዝገባ ያላደረገው ባለፉት አምስት ዓመታት የሚመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር በመቀነሱ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት ኮሌጁ የሚያገኘው ገቢ የአስተዳደር ወጪ መሸፈን የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)