በኢትዮጵያ የታገዱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቁጥር አራት ደረሰ 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሰዋል” ያላቸውን፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን (EHRDC) ከማንኛውም የስራ እንቅስቃሴ አገደ። ባለስልጣኑ ባለፈው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ያገዳቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቁጥር አራት ደርሰዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሁለቱን ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያገደው፤ ከትላንት ረቡዕ ታህሳስ 16፤ 2017 ጀምሮ እንደሆነ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሰረት ስራቸውን ማከናወናቸውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ ለድርጅቶቹ በትላንትናው ዕለት በላከው ደብዳቤ ለእግድ ያበቃቸውን ምክንያት ዘርዝሯል። 

ሁለቱም ድርጅቶች “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ” እና “ኃላፊነት በጎደለው መልኩ” በመንቀሳቀስ እንዲሁም “ገለልተኛ ባለመሆን” በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ውንጀላ ቀርቦባቸዋል። እነዚህ ውንጀላዎች ባለፈው ሳምንት በድጋሚ እንዲታገዱ በተደረጉት፤ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች (LHR) በተባሉት ድርጅቶች ላይም በምክንያትነት ተጠቅሷል።

በትላንቱ የእግድ ደብዳቤ ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል “ግልጽ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር የለውም” የሚል ተጨማሪ የእግድ ምክንያት እንደቀረበበት ምንጮች ተናግረዋል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የትላንቶቹን ጨምሮ በአራቱም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ የእገዳ ውሳኔ ያስተላለፈው፤ የክትትል እና የግምገማ ስራዎችን ካከናወነ በኋላ መሆኑን ለየድርጅቶቹ በላካቸው ደብዳቤዎች ላይ ገልጿል።

ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ይህን ቢልም እገዳ የተላለፈባቸው ድርጅቶች ግን “ህግን በተከተለ መልኩ የተካሄደ የክትትልም ሆነ የግምገማ ስራ አልነበረም” ሲሉ ይሟገታሉ። በ2011 ዓ.ም. የተሻሻለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ፤ ለተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ “ምርመራ የማድረግ ስልጣን” ሰጥቶታል። 

አዋጁ በጸደቀበት ወቅት “ኤጀንሲ” የነበረውን በስተኋላ ላይ “ባለስልጣን” የሆነው ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ፤ “ከመንግስት አካላት፣ ከለጋሽ ድርጅቶች ወይም ከህዝብ ከሚቀርቡ ጥቆማዎች” በመነሳት ምርመራ ሊያደርግ እንደሚችል ደንግጓል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ “ስራውን በሚያከናውንበት ወቅት የሚገኙ መረጃዎችን” መነሻ በማድረግም ምርመራ ሊያከናውን እንደሚችልም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። 

ባለስልጣኑ የድርጅቶችን እንቅስቃሴ የሚያግደው፤ “ከባድ የህግ ጥሰት መፈጸሙን ሲያረጋግጥ” እንደሆነም አዋጁ ላይ ተቀምጧል። በመስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አማካኝነት የሚተላለፈው እገዳ “ከሶስት ወር ላልበለጠ ጊዜ” የሚደረግ ነው። በዚህ መልኩ እገዳ የተላለፈባቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ ቅሬታቸውን በ30 ቀናት ውስጥ ለተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ቦርድ የማቅረብ ዕድል አላቸው።

ትላንት የእግድ ውሳኔው የደረሰው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፤ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በዛሬው ዕለት የማብራሪያ መጠየቂያ ደብዳቤ ማስገባቱን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ድርጅቱ በዚሁ ደብዳቤው፤ በባለስልጣኑ ተደረገ የተባለው ምርመራ ስለመከናወኑ እንደማያውቅ፣ በእግድ ደብዳቤው የተጠቀሱት ውንጀላዎች “በጥቅል የቀረቡ” እና ማዕከሉንም የማይመለከቱ እንደሆኑ ማስረዳቱን ምንጮች አብራርተዋል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በዛሬው ዕለት ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫም፤ ስራዎቹን “በፍጹም ገለልተኝነት”፣ “ኃላፊነት በተሞላበት ጥንቃቄ” እና “የድርጅቱን መርሆዎች በተከተለ መልኩ ብቻ ሲያከናወን” መቆየቱን አስታውቋል። “ድርጅታችን ከተመሰረተበት ጊዜ አስንስቶ ከተቋቋመበት አላማ ውጪ በየትኛውም ያልተገባ ወይም ከህግ የሚጻረር እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የማያውቅ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን” ብሏል ማዕከሉ በመግለጫው። 

“ድርጅታችን ቦርድ መር የሆነ ድርጅት እና ግልጽ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር ኖሮት ለአመታት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ያለ መሆኑ እሙን ነው። ይሄንንም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሰጠን የእውቅና መረጋገጫ ላይ በግልጽ የተቀመጠ መሆኑ እየታወቀ ‘ግልጽ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር የሌለው የሚለው አስተያየት ለእኛም ግልጽ ስላሆነልን ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባቀረብነው የማብራሪያ መጠየቂያ ደብዳቤ ላይ መግለጻችንን ለማሳወቅ እንወዳለን” ሲልም ማዕከሉ አክሏል።       

ከተቋቋመ አምስት ዓመት የሞላው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፤ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በይፋ የተመዘገበው በህዳር 2013 ዓ.ም. ነው። ማዕከሉ ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች “ጥበቃ ለማድረግ”፣ “ሙያዊ ክህሎታቸውን ለማዳበር” እና “መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው” የሚሰራ ተቋም ነው። 

በዚህም መሰረት ማዕከሉ ባለፉት አራት ዓመታት ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የተለያዩ ስልጠናዎችን የሰጠ ሲሆን የውትወታ (advocacy) ስራዎችንም ሲያከናወን ቆይቷል። ድርጅቱ በመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች ላይ የተወሰደውን የእገዳ እርምጃ በተመለከተ የውትወታ ስራው አካል የሆኑ መግለጫዎችን አውጥቷል።

የትላንቱ የእግድ ውሳኔ ሰለባ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤም፤ በሁለቱ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ላይ የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ አቋሙን በመግለጫ አንጸባርቋል። ኢሰመጉ ከሁለት ሳምንት በፊት ባወጣው በዚሁ መግለጫው፤ በድርጅቶች ላይ ከተወሰደው የማገድ እርምጃ በተጓዳኝ በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ “ከፍተኛ ጫና” እየደረሰ መሆኑን አስታውቆ ነበር። 

“የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን የማዋከብ እና በነጻነት ተንቀሳቅሰው ስራቸውን እንዳይከውኑ እንቅፋት በመፈጠሩ፤ ሀገራቸውን ትተው እንዲሰደዱ መገደዳቸው የሲቪል ምህዳሩን የሚያጠብ እና በመደራጀት መብት ላይ ጥላውን የሚጥል መሆኑ ግልጽ ነው” ሲል ኢሰመጉ በዚሁ መግለጫው ላይ አስፍሯል። የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ዳን ይርጋ፤ በተመሳሳይ ምክንያቶች ሀገር ለቅቀው እንዲሰደዱ መደረጋቸውን ኢሰመጉ ለዚህ በማሳያነት ጠቅሷል። 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል የቦርድ አባል ጭምር የነበሩት አቶ ዳን ከሀገር ለመውጣት የተገደዱት፤ ይደርሱባቸው ነበር የተባሉ “ተከታታይ እና ዘርፈ ብዙ ጫናዎች፣ ዛቻና እንግልቶች” “ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው” መሆኑን ኢሰመጉ በመግለጫው አመልክቶ ነበር። “ለህይወታቸው በመስጋት” መሰደዳቸው ከተገለጸው ከቀድሞው የኢሰመጉ ዋና ዳይሬክተር በተጨማሪ በርካታ ሰራተኞች “በሚደርስባቸው የተለያዩ ጫናዎች ምክንያት” ስራቸውን ለመልቀቅ መገደዳቸውን ድርጅቱ በዚሁ መግለጫው አስታውቋል።  

በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማጋለጥ እና በመሰነድ የሚታወቀው ኢሰመጉ፤ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም አማካኝነት የተመሰረተው በ1984 ዓ.ም ነበር። የዲሞክራሲ፣ የህግ የበላይነት እና የሰብዓዊ መብት መከበርን ዓላማው ያደረገው ኢሰመጉ፤ በኢህአዴግ የስልጣን ዘመን የገጠሙት እና ህልውናውን ጭምር የተፈታተኑ ችግሮችን በማለፍ እስካሁን በስራ ላይ የቆየ ድርጅት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)