በቀበና ከተማ የቀሩ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች መንግስት በአፋጣኝ እንዲደርስላቸው ተማጸኑ 

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በአፋር ክልል ያለ ማቋረጥ የቀጠለው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ብርቱ ሆኖ ከሚሰማባቸው ስፍራዎች አንዱ የቀበና ከተማ ናት። የቀበና ከተማ አብዛኞቹ ነዋሪዎች የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች ናቸው። 

አርባ ሁለት ሺህ ገደማ ለሆኑ ሰራተኞች የስራ ዕድል የፈጠረው የከሰም ስኳር ፋብሪካ፤ ባለፉት ቀናት በአካባቢው በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሞታል። የመሬት መንቀጥቀጡ ከፋብሪካው በተጨማሪ በቀበና ከተማ ያሉ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን አፈራርሷል። 

ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሰጉ የተወሰኑ የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ የጭነት መኪናዎችን በመከራየት በአቅራቢያው ወደሚገኙ ከተሞች ሲሸሹ ቆይተዋል። ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ በርካታ የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ የመከላከያ ሰራዊት ባቀረባቸው ወታደራዊ ካሚዮኖች ተጓጉዘዋል። 

የከሰም ስኳር ፋብሪካ የመደበው አንድ ግዙፍ የጭነት ተሽከርካሪም፤ የፋብሪካውን ሰራተኞች ከአደጋ ወደ ራቁ ቦታዎች ዛሬን ጨምሮ በየቀኑ እያጓጓዘ ነው። እንዲያም ሆኖ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፋብሪካው ሰራተኞች፤ አሁንም በቀበና ከተማ ሆነው የሚደርስላቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። 

ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 28 በስፍራው የተገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ የተወሰኑ የፋብሪካው ሰራተኞች ንብረቶቻቸውን አስፋልት ዳር ኮልኩለው የሚያጓጉዛቸውን ሲጠባበቁ ተመልክቷል። በየመኖሪያ ቤቶቻቸው ጓዛቸውን ሸክፈው የተቀመጡትም፤ ከተማይቱን ለቅቀው የመውጣት ፍላጎት እንዳላቸው ሲናገሩ አድምጧል። 

ከዕለት ወደ ዕለት ጥንካሬው እየጨመረ የመጣው የመሬት መንቀጥቀጥ የሚያስከትለው ንዝረት፤ ከቤት ውጭ እንኳ ለመተኛት የማያስችል እንደሆነ ሰራተኞቹ ይናገራሉ። አብዛኛው የከተማይቱ ነዋሪ ስፍራውን ለቅቆ በመሄዱ፤ የሚበላ እና የሚጠጣ ለማግኘት መቸገራቸውንም ያስረዳሉ። መንግስት ችግራቸውን ተመልክቶ በአፋጣኝ እንዲደርስላቸውም እነኚሁ ሰራተኞች ተማጽኗቸውን አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)