በአፋር ክልል በመሬት መንቀጥቀጥ ለተፈናቀሉ ሰዎች እርዳታ እየተከፋፈለ ነው

በአፋር ክልል፣ ገቢ ረሱ ዞን፣ ዱለሳ ወረዳ በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ለተፈናቀሉ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች፤ ከትላንት በስቲያ እሁድ ታህሳስ 27 ጀምሮ እርዳታ እየተከፋፈለ መሆኑን በወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ መሐመድ አስኪር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የምግብ እና የቁሳቁስ እርዳታው እየተሰጠ የሚገኘው፤ በሶስት ጣቢያዎች እንዲሰፍሩ ለተደረጉ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መሆኑንም ገልጸዋል። 

የፌደራል የአደጋ ስጋት እና አመራር ኮሚሽን ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ፤ የዱለሳ ወረዳ 20 ሺህ ነዋሪዎች ለርዕደ መሬት አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጾ ነበር። በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ከሚኖሩት ከእነዚህ ዜጎች ውስጥ ስድስት ሺህ ገደማ የሚሆኑቱ፤ ከስጋት ቀጠና ውጭ ወዳሉ ስፍራዎች እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውንም ኮሚሽኑ በወቅቱ አስታውቋል። 

አካባቢያቸውን ከለቀቁ የዱለሳ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑቱ የሰፈሩት፤ ከዶሆ ሎጅ አቅራቢያ በሚገኝ “ዳይኢዶ” ተብሎ በሚጠራ ሜዳማ ቦታ ላይ ነው። በዚህ ገለጣ ስፍራ ላይ እንዲሰባሰቡ የተደረጉ ተፈናቃዮች ምዝገባ ከተከናወነ በኋላ፤ ትላንት ሰኞ ታህሳስ 28 የምግብ እና የቁሳቁስ እርዳታ ሲሰጣቸው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል።

የእርዳታ ስርጭቱ እየተከናወነ ያለው፤ የክልሉ መንግስት ለአደጋው ምላሽ ለመስጠት ባቋቋመው ኮማንድ ፖስት አማካኝነት መሆኑን አቶ መሐመድ ገልጸዋል። ኮማንድ ፖስቱ፤ የአደጋ መከላከል ባለሙያዎች፣ የፌደራል መንግስት ተቋማት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያከናውኗቸውን ስራዎች የሚያስተባብር ነው። 

በዳይኢዶ የተፈናቃዮች ማቆያ ጣቢያ ከሰፈሩት ውስጥ አንዷ የሆነችው መዲና ገነቶ፤ ከክልሉ መንግስት 50 ኪሎ ግራም ስንዴ ዱቄት እርዳታ ማግኘቷን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። የስንዴ ዱቄቱ የሚሰጠው በሁለት ሰው ኮታ መሆኑን አመልክታለች። 

“ለአንዳንዱ ተሰጥቶ ለአንዳንዱ ደግሞ አልተሰጠም።  ግማሹ አግኝቷል፤ ግማሹ አላገኘም። ብዙ ያላገኘ አለ። ይሄ የቀበሌ ችግር ይመስለኛል።  “እኛ የምንጠይቀው ቢኖር እርዳታ ያመጡልን ሰዎች፤ ራሳቸው ቢሰጡን ደስ ይለናል። ምክንያቱም በቀበሌ የምናገኘው ነገር ለሁሉም እየተዳረሰ አይደለም” ስትል የእርዳታ ማከፋፈል ሂደቱ ላይ ሊስተካከል ይገባል ያለችውን ጠቁማለች።

በእርዳታ አቅርቦት በኩል ለጊዜው ችግር እንደሌለ የሚናገሩት የዱለሳ ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ የእርዳታ አሰጣጡ በቀበሌ አመራሮች እንዲከናወን የተደረገው ከከተማ የሚመጡ “ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠር” እንደሆነ አስረድተዋል። “[ተፈናቃዮችን] የቀበሌ አመራር፣ የጎሳ መሪ እየለያቸው፣ ያቋቋምነው ኮሚቴ አለ በእርሱ እየተለዩ [እርዳታ] የሚሰጥበት ሁኔታ ነው ያለው። እያጠራን ነው የምንመጣው። ያው ተግዳሮቱን እየተጋፈጥን ነው” ሲሉ አቶ መሐመድ አሁን ያለውን ሁኔታ አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)