በቤርሳቤህ ገብረ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ጥር 6፤ 2017 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ የንብረት ታክስ አዋጅን በአራት ተቃውሞ እና በ10 ድምጸ ተዐቅቦ አጽድቆታል። የአስረጂ እና ይፋዊ የህዝብ መድረክን ጨምሮ ለአራት ጊዜ ያህል ውይይት የተደረገበት ይህ አዋጅ፤ በፓርላማ አባላት እና በሌሎች ተሳታፊዎች ብዙ አከራካሪ ነጥቦች የተነሱበት ነበር።
የአዋጅ ረቂቁ ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ለዝርዝር እይታ የተመራለት የተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በዛሬው ዕለት የውሳኔ ሃሳቡን ባቀረበበት ወቅትም ተመሳሳይ ሃሳቦች ተደምጠዋል። በማክሰኞው መደበኛ ስብሰባ አስተያየታቸውን ያቀረቡ አንድ የፓርላማ አባል፤ የንብረት ታክስ መጣሉ የዋጋ ንረትን ሊያባብስ እና ተደራራቢ ጫና ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው የንብረት ታክስ አዋጅ፤ በረቂቅ ደረጃ ከነበረበት ጥቂት ማሻሻያዎች ተደርገውበታል። ማሻሻያ ከተደረገባቸው ድንጋጌዎች መካከል የንብረት ታክስ በመቶኛ የሚከፈልበት ዋጋ መሰረት፣ በየዓመቱ የሚደረገው የንብረት ታክስ ጭማሪ እና በታክስ ነጻ ስለተደረጉ የቦታ እና የህንጻ አገልግሎቶች የሚመለከቱት ይገኙበታል።

በአዋጁ ከተካተቱ ማሻሻያዎች እና አዳዲስ አንቀጾች መካከል በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠናቀሩትን ከዚህ በታች አቅርበናቸዋል፦
የንብረት ታክስ የሚከፈልበት ዋጋ መሰረት ከንብረቱ በመቶኛ
በረቂቅ ደረጃ የነበረው አዋጅ፤ “ታክስ የሚከፈልበት ዋጋን” በተመለከተ ያስቀመጠው ትርጓሜ ላይ ተጨማሪ አዲስ ንዑስ አንቀጽ እንዲጨምር ተደርጓል። የአዋጅ ረቂቁ “ታክስ የሚከፈልበት ዋጋ” ማለት “ከአንድ ንብረት የገበያ ዋጋ ውስጥ ለንብረት ታክስ መሰረት የሚሆነው መቶኛ” እንደሆነ አስቀምጦ ነበር። ይህ የሚወሰነውም የገንዘብ ሚኒስቴር ከከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመመካከር በሚያወጣው መመሪያ እንደሆነ የአዋጅ ረቂቁ አመልክቷል።
ዛሬ በጸደቀው አዋጅ ደግሞ “ከአንድ ንብረት የገበያ ዋጋ ውስጥ ለንብረት ታክስ መሰረት የሚሆነው የንብረቱ ዋጋ 25 በመቶ ነው” የሚል ተጨማሪ ንዑስ አንቀጽ ተካትቷል። ማሻሻያው የተደረገው “ከንብረት ወቅታዊ ጠቅላላ ዋጋ ውስጥ” ለታክሱ መሰረት የሚሆነውን መቶኛ “በግልጽ ማመላከት አስፈላጊ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ ለፓርላማው የቀረበ ማብራሪያ አስገንዝቧል።
“ከአንድ ንብረት የገበያ ዋጋ ውስጥ ለንብረት ታክስ መሰረት የሚሆነው የንብረቱ ዋጋ 25 በመቶ ነው”
– የንብረት ታክስ አዋጅ
በየዓመቱ የሚደረግ የንብረት ታክስ ጭማሪ
በአዋጅ ረቂቅ ሰነዱ ላይ የንብረት ታክስን ምጣኔ ዝቅተኛ ወለል እና ከፍተኛ ጣሪያ የሚወሰነው በሚኒስትሮች ምክርቤት በሚወጣ ደንብ እንደሆነ ተመልክቷል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት በንብረት ታክስ ምጣኔ ላይ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ ግን በመነሻነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ምጣኔዎችን የአዋጅ ረቂቁ ዘርዝሯል።
ከእነዚህ ዝርዝሮች መካከል አንዱ የሆነው እና በየአመቱ የሚደረግን የንብረት ታክስ ጭማሪን የሚመለከተው ንዑስ አንቀጽ በጸደቀው አዋጅ ላይ እንዳይካተት ተደርጓል። ከአዋጁ እንዲወጣ የተደረገው ንዑስ አንቀጽ “የዋጋ ንረትን ሳይጨምር በየአመቱ የሚደረገው የንብረት ታክስ ጭማሪ፤ ከንብረቱ ታክስ የሚከፈልበት ዋጋ ግምት 0.5 በመቶ መብለጥ የለበትም” የሚል ነበር።
ይህ ንዑስ አንቀጽ ከአዋጁ ውጭ እንዲሆን የተደረገበት ምክንያት “በየዓመቱ የሚደረገው የጭማሪ መጠን፤ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባትና በጥናት ላይ በመመስረት የሚወሰን በመሆኑ፤ በአንቀጽ ወስኖ ማስቀመጥ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ስለሚሆን ነው” ሲል ለፓርላማ የቀረበው ማብራሪያ አስረድቷል።

በታክስ ነጻ ስለተደረጉ የከተማ ህንጻ እና ቦታ
በረቂቅ ደረጃ የነበረው አዋጅ ከታክስ ነጻ የሚደረጉ “የከተማ ህንጻ እና ቦታ” ምንነት በዝርዝር ያስቀመጠ ነበር። ዛሬ በጸደቀው አዋጅ ሌሎች ተጨማሪ ሁለት አንቀጾች በዝርዝሩ እንዲካተቱ ተደርጓል። የመጀመሪያው ተጨማሪ አንቀጽ የሚመለከተው “ለህብረተሰቡ ነጻ የማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ” በሚል የተጠቀሱ ድርጅቶችን ነው።
እነዚሁ ድርጅቶች ለነጻ አገልግሎታቸው የሚጠቀሙበት “ቦታ እና ህንፃ” ከታክስ ነጻ እንደሚደረጉ በጸደቀው አዋጅ ላይ ሰፍሯል። ይህ የተደረገው ለህብረተሰቡ ነጻ የማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችን “ለመደገፍ እና ለማበረታታት” መሆኑ በማብራሪያው ላይ ተቀምጧል።
በረቂቅ ደረጃ የነበረው አዋጅ “ለአንድ ቤተሰብ በመኖሪያነት አገልግሎት እየሰጠ ያለ ህንጻ” ከንብረት ታክስ ነጻ እንደሚደረግ ደንግጎ ነበር። ሆኖም አዋጁ ሲጸድቅ፤ “ከንብረት ታክሱ ነጻ እንዲሆን የሚፈለገውን የህብረተሰብ ክፍል በትክክል በሚገልጽ” አረፍተ ነገር እንዲሻሻል ተደርጓል። በዚህ መሰረት ከንብረት ታክስ ነጻ የሚደረገው፤ “ዝቅተኛ ገቢ ላለው አንድ ቤተሰብ በመኖሪያነት አገልግሎት እየሰጠ ያለ የመኖሪያ ህንጻ” ነው።

ያልተከፈለ የንብረት ታክስ የሚከፈልበት መጠን
በረቂቅ ደረጃ የነበረውም ሆነ ዛሬ የጸደቀው አዋጅ “የንብረት ታክስ በአንድ ጊዜ ወይም ተከፋፍሎ ሊከፈል እና ሊሰበሰብ” እንደሚችል ይደነግጋል። የንብረት ታክሱ በክልል ህግ በሚወሰነው መሰረት ከሐምሌ እስከ ሰኔ ባለው የኢትዮጵያ በጀት ዓመት፤ በየሩብ ዓመቱ አሊያም በየዓመቱ ሊከፈል እና ሊሰበሰብ እንደሚገባም በአዋጁ ላይ ተቀምጧል።
አዋጁ “በመኖሪያነት በሚገለገሉበት ህንጻ ላይ የሚፈለገውን የንብረት ታክስ ለመክፈል የሚያስችል የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው” ግለሰቦችም ያስቀመጠው ድንጋጌ አለ። እነዚህ ግለሰቦች “የመኖሪያ ቤቱን በሽያጭ ወይም በሌላ ማናቸውም መንገድ ለሶስተኛ ወገን በሚያስተላልፉበት ጊዜ”፤ ሊከፍሉት ይገባ የነበረውን የንብረት ታክስ ከሽያጩ ላይ ለመክፈል “የግዴታ ስምምነት” እንዲፈርሙ እንደሚደረግም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።
በዚህ አይነት አካሄድ “ክፍያው እንዲዘገይ” የተደረገን የንብረት ታክስ ግለሰቦች እንዲከፍሉ ሲደረግ፤ የሚጠየቁት የመጨረሻውን አምስት ዓመታት መጠን ብቻ እንደሆነ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተቀምጦ ነበር። ከአምስት አመት በላይ የሆነው “ውዝፍ” የንብረት ታክስ “ዕዳ”፤ ቀሪ እንዲሆን እንደሚደረግም የአዋጁ ረቂቁ አመልክቶ ነበር።
ዛሬ በፓርላማ የጸደቀው አዋጅ ግን የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው የንብረት ታክስ ሳይከፍሉ ቀርተው፤ የመኖሪያ ቤታቸውን በሽያጭም ሆነ በሌላ መልኩ የሚያስተላልፉ ግለሰቦች መክፈል የሚጠበቅባቸው የሁለት ዓመት የታክስ መጠን ብቻ እንዲሆን አድርጓል። ግለሰቦቹ የሚከፍሉት ውዝፍ የንብረት ታክስ መጠን ከአምስት ወደ ሁለት ዓመት ዝቅ እንዲል የተደረገው “የከፋዩን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ” መሆኑን ለፓርላማ የቀረበው ማብራሪያ ያስረዳል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ስልጣን እና ኃላፊነት
የገንዘብ ሚኒስቴር፤ የንብረት ታክስ ህግ ማሻሻያዎችን የማዘጋጀት እና በተወካዮች ምክር ቤት እንዲጻድቅ ማድረግን ጨምሮ ስድስት ስልጣን እና ተግባራትን በአዋጅ ረቂቁ ተሰጥቶት ነበር። ዛሬ በጸደቀው አዋጅ ላይ ደግሞ “በኢኮኖሚ ጥናት ላይ በመመስረት ታክስ የሚከፈልበትን ዋጋ ከፍ ወይም ዝቅ ማድረግ ይችላል” የሚል ተጨማሪ ስልጣን ተሰጥቶታል።
ይህ የተደረገው “የንብረት ግመታ እና የኢኮኖሚ ጥናትን መሰረት በማድረግ መቶኛውን ከፍ ወይም ዝቅ በማድረግ ተግባራዊ እንዲሆን በማስፈለጉ” ምክንያት መሆኑ ለፓርላማ በቀረበ ማብራሪያ ላይ ሰፍሯል።
የተሻሩ እና ተፈጻሚነት ስለማይኖራቸው ህጎች
በስድስት ክፍሎች እና በ43 አንቀጾች የተከፋፈለው የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ፤ በመጨረሻ ያስቀመጣቸው “የተሻሩ እና ተፈጻሚነት የማይኖራቸው ህጎችን” ነው። የአዋጅ ረቂቁ በ1968 ዓ.ም የወጣውን የከተማ ቦታ ኪራይና የቤት ታክስ አዋጅ እንዲሁም በ1971 ዓ.ም. የወጣውን የእዚህኑ ማሻሻያ የሻረ ነበር።
በዛሬው ዕለት በጸደቀው አዋጅ ላይ ግን በ1986ቱ አዋጅ “የከተማ ቦታ ኪራይን የሚመለከቱት ድንጋጌዎች” ባሉበት እንደሚቀጥሉ ሰፍሯል። የከተማ ቦታ ኪራይን የሚመለከቱት ድንጋጌዎች እንዲሻሩ ያልተደረገው፤ “ከተሞች ከሊዝ ውጪ ባለ ነባር ይዞታ ላይ የከተማ ቦታ ኪራይ የሚሰበስቡት በዚህ አዋጅ መሰረት በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ ለፓርላማ የቀረበው ማብራሪያ ያስረዳል። “አዋጁን ሙሉ በሙሉ መሻር ከተሞች የከተማ ቦታ ኪራይ እንዳይሰበስቡ” የሚያደርግ እንደሆነም ማብራሪያው አክሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)