በደምሰው ሽፈራው
የአማራ እና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ከሚያነሱባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ጠለምት ወረዳ በመሬት መንሸራተት የተፈናቀሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች፤ ከአራት ወራት በኋላም “በጊዜያዊ መጠለያ እንዲቆዩ በመገደዳቸው” ለችግር መጋለጣቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የአካባቢው ባለስልጣናት ለተፈናቃዮቹ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ቢያመቻቹም፤ በበጀት እጥረት ምክንያት ለግንባታ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወዲህ በአማራ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ጎንደር ዞን ስር እየተዳደረ የሚገኘው የጠለምት ወረዳ፤ የመሬት መንሸራተት አደጋ ያጋጠመው ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ገደማ ነበር። በአደጋው 10 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ፤ 35 የቤት እንስሳት ሞተዋል። የመሬት መንሸራተቱ ከ30 ሄክታር በላይ በሰብል የተሸፈነ መሬት ላይም ጉዳት አድርሷል።
በአደጋው ከቀያቸው የተፈናቀሉ 2,400 የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች፤ በመጀመሪያ በትምህርት ቤት በስተኋላ ደግሞ በወረዳው ጽህፈት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ቆይተዋል። ከእነዚህ ተፈናቃዮች አንዱ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ፍስሃ፤ እርሳቸውን ጨምሮ 100 የሚሆኑ አባወራዎች በአሁኑ ወቅት ተጠልለው የሚገኙት የጠለምት ወረዳ አስተዳደር እና የወረዳው የግብርና ቢሮ በጽህፈት ቤትነት ይገለገሉባቸው በነበሩ ክፍሎች ውስጥ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በመሬት መንሸራተት አደጋው መኖሪያ ቤታቸው እና የእርሻ ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ እንደወደመባቸው የሚገልጹት አቶ ተስፋዬ፤ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኙት ከሰባት ልጆቻቸው ጋር ነው። “አራቱ ልጆቼ ተማሪዎች ነበሩ። አሁን ግን ከአደጋው በኋላ ትምህርታቸውን አቁመዋል” ይላሉ። አቶ አዲጎሊ መስፍን የተባሉ ሌላ ተፈናቃይ በበኩላቸው በግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና በግል ባለሃብቶች ይቀርቡላቸው የነበረው የምግብ እርዳታ እና ሌሎች መሰረታዊ ድጋፎች ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በመቋረጡ መቸገራቸውን ይገልጻሉ።
“እስከ ጥቅምት መጀመሪያ ድረስ ጥሩ ነበር። አሁን ግን ምንም የለንም። የእለት ምግብ ያስፈልገናል” ሲሉ አቶ አዲጎሊ ያሉበትን አሳሳቢ ሁኔታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። “የግል በጎ አድራጎቶች ድጋፍ ሲያደርጉልን ቆይተዋል። መንግስት ግን አልደረሰልንም” የሚሉት ተፈናቃዩ፤ የአማራ ክልል እና የሰሜን ጎንደር ዞን አመራሮች ቢሆኑ የጎበኟቸው አደጋው በተከሰተ ሰሞን “ለአንድ ጊዜ ብቻ” እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህንኑ የተፈናቃዮች አቤቱታ፤ በጠለምት ወረዳ የአብና ቀበሌ የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጄጃው ብርሃኔ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። “እስካሁን አንድ ጊዜ ብቻ ከመንግስት የ300 ኩንታል እህል ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ከዚያ ውጪ የክልሉ መንግስት ድጋፍ አላደረገም” ሲሉ የጽህፈት ቤት ኃላፊው አክለዋል።

የጠለምት ወረዳ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛው ዘነበ ግን በመሬት መንሸራተት ሳቢያ ለተፈናቀሉ የወረዳው ነዋሪዎች ከክልል እና ከፌደራል መንግስት እንዲሁም ከተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች “በርካታ ድጋፍ ቀርቧል” ባይ ናቸው። ድጋፉ በአሁኑ ወቅት ላይ “እየቀነሰ መምጣቱን” የሚገልጹት የቢሮ ኃላፊው፤ ይህም ተፈናቃዮቹን ብቻ ሳይሆን የወረዳው አመራሮችንን ስጋት ውስጥ እንደከተታቸው አመልክተዋል።
ተፈናቃዮቹ ከእርዳታ በተጨማሪም የጊዜያዊ መጠለያ እና ዘላቂ የሆነ መኖሪያ ቤት የማግኘት ጉዳይ ያሳስባቸዋል። የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች የመሬት መንሸራተ አደጋ ከተከሰተበት ቀን ጀምሮ በትምህርት ቤት ውስጥ እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን በስተኋላ ላይ የወረዳው አስተዳደር ሲጠቀምባቸው ወደነበሩ ቢሮዎች ተዘዋውረዋል።
ከወረዳው አስተዳደር በተጨማሪ የወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ይጠቀምባቸው የነበሩ 10 ክፍሎች በጊዜያዊ መጠለያነት እያገለገሉ ቢሆንም፤ በክፍሎቹ መጨናነቅ ምክንያት ተፈናቃዮቹ ለተለያዩ የጤና እክሎች እየተዳረጉ መሆኑን ይገልጻሉ። “በወረዳው ቢሮዎች ውስጥ በአንድ ክፍል ከስድስት እስከ ስምንት አባወራዎች [ተጠልለዋል]። በግብርና ቢሮዎች ውስጥ ደግሞ 30 አባወራ ተጠልሎ ይገኛል” ሲሉ ከተፈናቃዮቹ አንዱ የሆኑት አቶ አዲጎሊ ያስረዳሉ።

“አብዛኛው ተፈናቃይ በሜዳ ላይ ነው ያለው” የሚሉት አቶ አዲጎሊ፤ የተወሰኑት በሜዳው ላይ ዳስ ጥለው መጠለያ ለመስራት መሞከራቸውን ይናገራሉ። ተፈናቃዮቹ ከጊዜያዊ መጠለያ ወጥተው መኖሪያ ቤቶች ወደሚሰሩበት ቦታ እንዲዛወሩ ከሰሜን ጎንደር ዞን እና የጠለምት ወረዳ ቃል ቢገባላቸውም፤ እስካሁን ግን በተግባር የተደረገላቸው ነገር እንደሌለም ያስረዳሉ።
የጠለምት ወረዳ ከሰሜን ጎንደር ዞን አመራሮች ጋር በመነጋገር ለ350 አባወራዎች የሚሆን መኖሪያ ቦታ ማመቻቸቱን በወረዳው የአብና ቀበሌ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ሆኖም የወረዳው አስተዳደር “ቤቶቹን ለመገንባት የሚሆን ሃብት ስሌለው”፤ ተፈናቃዮቹን “ወደተዘጋጀላቸው ቦታ ማዘዋወር አልተቻለም” ብለዋል።
የጠለምት ወረዳ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛው፤ በአካባቢው የእርሻ መሬት ጥበት ስላለ፤ የፌደራል መንግስት እና የክልሉ መንግስት በሰፈራ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲወስዳቸው ተፈናቃዮቹ ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ይገልጻሉ። “እነሱም እኛም እየጠየቅን ያለው ሰፈራ ነው። ለክልልም ለበላይ አካልም፣ ለዞንም አሳውቀናል። እስካሁን ግን ምላሽ አልተሰጠንም” ሲሉ ጉዳዩ እስካሁንም ዘላቂ መፍትሔ እንዳላገኘ አብራርተዋል።

የሰፈራ እና የእርዳታ ጉዳይን በተመለከተ ከአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን እንዲሁም ከፌደራል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። የጠለምት ወረዳ ግብርና ቢሮ ኃላፊ፤ ጥያቄ እየቀረበበት ያለው ሰፈራ የማይሳካ ከሆነ ያለው ብቸኛ አማራጭ ተፈናቃዮችን “በአጎራባች ቀበሌዎች እና ከተማ አካባቢ ማስፈር” እንደሆነ ያስረዳሉ።
በዚህም መሰረት የጠለምት ወረዳ ተፈናቃዮቹ አሁን ባሉበት አካባቢ በሚገኙ ከተሞች ውስጥ የመኖሪያ ቦታ በአማራጭነት እንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን አቶ ግዛው ጠቁመዋል። ሆኖም ተፈናቃዮቹ መተዳደሪያቸው ለሆነው የግብርና ስራ ሰፊ መሬት የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ፤ የመኖሪያ ቦታ መስጠት ብቻ “ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አይችልም” ባይ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)