በደምሰው ሺፈራው
የወባ ወረርሽኝ ስርጭት፤ ተፈናቃይ ዜጎች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች እንዲሁም የመስኖ ስራ እና የስንዴ ልማት ባሉባቸው ቦታዎች ላይ “በእጅጉ መጨመሩን” የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ድጉማ ገለጹ። በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ባለፈው ስድስት ወራት የተከሰተው የወባ ወረርሽኝ፤ ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር “በሁለት እጥፍ” መጨመሩም ተነግሯል።
ይህ የተገለጸው ዛሬ ረቡዕ ጥር 28፤ 2017 በተካሄደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነው። የፓርላማው የጤና፤ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዛሬውን መድረክ ያዘጋጀው፤ የጤና ሚኒስቴርን የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ለማዳመጥ ቢሆንም በስብሰባው የቀረበው ግን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሪፖርት ብቻ ነው።
የኢንስቲትዩቱ የመንፈቅ ዓመት ሪፖርት በዋነኛነት ያተኮረው፤ በኢትዮጵያ ከ2016 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በወረርሽኝ ደረጃ በተከሰተው በወባ በሽታ ስርጭት ላይ ነው። በተቋሙ ሪፖርት መሰረት፤ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 658 ሰዎች በወባ ወረርሽኝ ህይወታቸው አልፏል።

በዚሁ ጊዜ ውስጥ በወባ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ብዛት ሰባት ሚሊዮን ገደማ እንደሆነም በሪፖርቱ ላይ ሰፍሯል። በመንፈቅ ዓመቱ ከፍተኛው የወባ ህመምተኞች የተመዘገቡበት ክልል ኦሮሚያ ነው። ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች ብዛት 3.2 ሚሊዮን መድረሱን የኢንስቲትዩቱ ሪፖርት አመልክቷል።
በተከታይነት ከፍተኛ የወባ ህመምተኞች በተመዘገቡበት የአማራ ክልል ያሉ የወረርሽኙ ተጠቂዎች ብዛት 1.3 ሚሊዮን እንደሆነ በኢንስቲትዩቱ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል። የተወካዮች ምክር ቤት የጤና፤ ማህበራዊ ልማት፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተስፋሁን ቦጋለ፤ የወባ ወረርሽኝ ስርጭት “ከአምናው ተመሳሳይ ስድስት ወር አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር ከሁለት እጥፍ በላይ” መጨመሩን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም ወባ በማይከሰትባቸው አካባቢዎች ላይ ስርጭቱ እየተስተዋለ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ተስፋሁን፤ ለዚህም በማሳያነት የአዲስ አበባ ከተማን ጠቅሰዋል። በመዲናዋ አዲስ አበባ የወባ በሽታ “ከ17ሺ በላይ ሰዎችን አጥቅቷል” ያሉት የቋሚ ኮሚቴው አባል፤ ወረርሽኙን “ለምን መቀነስ አልተቻለም?” ሲሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ሪፖርት ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ፤ የወባ ወረርሽኝ ስርጭት በጣም ጨምሮ የታየው “በልማት ኮሪደሮች አካባቢ” እንደሆነ ተናግረዋል። “በተለይ የመስኖ ስራ ያለበት ቦታ ላይ በጣም በእጅጉ ጨምሯል” ያሉት ዶ/ር ደረጀ፤ ለዚህም በማሳያነት የስንዴ ልማት የሚካሄድባቸውን አካባቢዎች አንስተዋል።
“የስንዴ ልማት በጣም ትልቅ ልማት ነው። ውሀን አመቱን ሙሉ የሚጠቀም ስለሆነ በዚያ አካባቢ ላይ ጨምሯል” ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው። ከቀያቸውን የተፈናቀሉ ዜጎች በሰፈሩባቸው አካባቢዎችም በተመሳሳይ መልኩ የወባ ወረረሽኝ ጨምሮ መታየቱንም አስረድተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ “ከሌሎች የተለያዩ ሴክተሮች ጋር እየተነጋገርን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የወባ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በጤና ሚኒስቴር የተሰሩ ስራዎች “በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳይሆኑ” አድርገዋል ያሏቸውን ምክንያቶችን በቋሚ ኮሚቴው የጥያቄ እና መልስ ጊዜ ላይ አንስተዋል። በአንዳንድ ክልሎች ያሉ የጤና ባለሙያዎች ደመወዛቸውን በአግባቡ እያገኙ አለመሆኑ፤ ለወረርሽኙ መስፋፋት በምክንያትነት ሊጠቀስ እንደሚችል ዶ/ር ደረጀ ተናግረዋል።

“በተለይ ቅርብ ጊዜ የተመሰረቱ ክልሎች ከፍተኛ የበጀት እጥረት አለባቸው። በእነዚህ ክልሎች ላይ ለጤና ሙያተኞች በጊዜ ደመወዝ አለመክፈል፣ ጥቅማ ጥቅሞችን በጊዜ አለመስጠት፤ ለወባ መጨመር እንደ አንድ መንስኤ ሊወሰድ ይችላል” ሲሉ ሚኒስትር ዲኤታው ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል። ችግሩን ለመፍታት ወደ ክልሎች ተጉዘው ከክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር ጭምር መነጋገራቸውን የገለጹት ዶ/ር ደረጀ፤ በዚህም ጥረት “የተስተካከሉ ቦታዎች” እንዳሉ አመልክተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ሌላው በችግርነት የጠቀሱት ጉዳይ የጸጥታ መድፍረስን ነው። “መድኃኒቶችን እና ሌሎች የህክምና ግብአቶችን በጸጥታ ችግር ምክንያት ሁሉም ቦታ ላይ ማድረስ ላይ ክፍተቶች አሉ” ያሉት ዶ/ር ደረጀ፤ “ያም ሆኖ ግን በካርጎ የወሰድንባቸው ብዙ ቦታዎች አሉ። የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ተጠቅመናል” ሲሉ ችግሩን ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ያደረጋቸውን ጥረቶች አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ፤ የጤና ባለሙያዎች “መስዋዕትነት የሚከፍሉበት ሁኔታ አጋጥሞናል” ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው የሁኔታውን አሳሳቢነት ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)